TG Telegram Group Link
Channel: የሆሄያት ህብር📝📝
Back to Bottom
#ከጥበብ በላይ !!
(ሚካኤል አስጨናቂ)
።።።።።።።።።።።።።።።
አጃኢብ ያረቢ!
አጃኢብ ያ ጎፍታ !
መገን ያንቺ ውበት
መገን ያንቺ ዝና...
የገላሽ ፍምነት ፥ የቁንጅናሽ ፋና
ደግሞ ተለኮሰ!
ጠዳል ብርሀንሽ ፥ ባገር ተዳረሰ።
ይኸው መጣን ደግሞ!
ጠበብት ተሰብስበን
ብዕር ተሸክመን...
ቀለማት በጥብጠን..
አንደኛው ሊፅፍሽ
ሌላኛው ሊስልሽ
ውበት ቃኙ ብለን ፥ ልናውጅ ለ'ዓለሙ
ነጋሪት ልንጎስም ፥ ስላንቺ ላልሰሙ።
እንችል ይመስል.. .
በብራና ጥራዝ ፥ በቅርፆች ማህደር
ስላንቺ መናገር!
እንችል ይመስል.. .
በሸራ ላይ ስዕል ፥ በሙዚቃ ቃና
መንገር ያንቺን ዝና!
እንዲያው ለሙከራ
እንዲያው ስለደንቡ
እንያዝ ብለን ወጉን
የገጣሚ ልኩን...
ስንኝ ልንቋጥር ፥ ሆሄያት ልንመታ
እንገልፅሽ ይመስል ፥ በቃላት ጋጋታ
እንዲያው ለሙከራ
እንይ ብለን ወጉን
የአዝማሪ ልኩን...
"ቀይ የወደደና ፥ እባብ የነደፈው"
እያልን በዜማ ፥ ውበትሽን ልንገልፀው
እንዲያው ለሙከራ
እንዲያው ስለደንቡ
እንያዝ ብለን ወጉን
የሰዓሊ ልኩን...
በውድር ሸራ ላይ ፥ ስለናታል ልንል
ገፅታሽ በቀለም ፥ ይገለፅ ይመስል
ይኸው መጣን ጠበብት!
ይኸው መጣን ሊቃን !
ሞልቶልን ባንገልፅሽ...
ሞከሯት ለመባል ፥ የፈጠረሽ ያብቃን ።
አሜን 🙏
@gGetem
@leoyri
ሐረግ የወረረው የህንፃ ቅሪት ሳይ

(በእውቀቱ ስዩም)

ሐረግ የወረረው የህንፃ ቅሪት ሳይ
አንቺን አስባለሁ
የረገፈ ቅጠል፤ ከትልልቅ ዛፍ ላይ
አንቺን ያሳስባል
እኮ ለምን ቢባል
ምናቃለሁ እንጃ
ያለ ሰበብ ማሰብ ፤ የመለከፍ ፍርጃ

ግን ብፈልግ አጣሁ ያለ ሰበብ መርሻ
ትዝታሽ ወጌሻ
ሳይጠሩት የመጣ
ያለ ማደንዘዣ ራስ የሚበጣ
ልብን እንደ ሙዳይ  ከፍቶ የሚገጥም
ብቻ
ላያስችል አይሰጥም!

ግንቡን አስረጅቶ ለሀረግ አውርሶ
ከትልቁ ዛፍ ላይ ቅጠሉን አፍልሶ
የሰጠውን ወስዶ ዘመኑ፤ ይነጉዳል
ብቻ
ባይድን ወይ ባይገድል ፤ ህመም ይለመዳል
@gGetem
@gGetem
ብቸኝነት  (በድሉ ዋቅጅራ)

እልፍኝህ እንዳʽብርሀም ቤት፣
አደባባይህ እንደጥምቀት፤
የሰው አሸን ቢወረው፣ ጠጠር መጣያ ቢገድም፤
ለመሀላህ ካስማ ʽሚሆን፣ ሲያነቅፍህ የምʽጠራው ስም፤
ከልቦናህ ሲነጥፍ፣ አንደበትህን ሲያንቀው፤
ብቻህን ነህ፣ ያኔ እወቀው፡፡

-----------
@gGetem
@leoyri
መጅ ደባቂ
(ሚካኤል አስጨናቂ)
.
መንገድ ለማበጀት መሬት ለሚንዱ
በሚንዱት መሬት ፍጥረት ለማገዱ
ፍጥረቱ ሲማገድ ታዝበው የሚያልፉ
ከመታዘብ ልቀው ለጩኸት ሰነፉ።
።።
እነርሱ.. .
ለጩኸት ሲሰንፉ
ዘመንን ሲገፉ
በሚገፉት ዘመን
ተስፋን እየቋጩ
ራዕይ ሲያጠፉ
በዝምታ ለምድ ውስጥ
አብዮት ሲጠልፉ
.
ተመልክተን ነበር ዓይናችን ተገልጦ
ከገቢረ ስጋ.. .
የነፍሳችን ቆቡ ከፍ እንዲል ተመርጦ።
።።።
እኛም.. .
ለጩኸት ስንከንፍ
የተገፋን ዘመን
ጎትተን ልናቀርብ
በጊዜ ባህር ላይ
ልንሻገር ስንቀዝፍ
.
ከሰውኛ ላንሸሽ
ላንመስል ቀንዳውጣ
ሲጮህ ተሸሽገን
ሲበርድ ላንወጣ
.
ለመከነ ራዕይ
ለከሰመ ተስፋ
ሲበርድ አጉረምርሞ
ሲጮህ ለሚጠፋ
.
ቀድሞውኑ ለራደ
ሙቁ ለበረደ
ታሪክን ሊገርፍ
እብለት ለገመደ
.
ያንን ሀሞት አልባ ፥ ደርሰን ለማታከት
በቀደደው ሱሪ.. .
ዙሪያ እየጠቀምን ልጣፍ ስንጥልበት
።።።
ሌሎች!
ከሚምሱት ምድር ፍጥረት ሊማግዱ
መንገድ ለማበጀት መሬት ስለናዱ
ቦላሌ ተርትረው እርቃን ስለሄዱ
.
የእነርሱን ቀዳዳ ለመጥቀም ስንታትር
ቱባ እያፍታቱ እንደማቀበር ክር
ፋሽን ናቁ ብለው.. .
ቁልቁል ወረወሩን ከሚምሱት ምድር ።
@gGetem
@leoyri
እሱ ነው - እሱ!
(ደበበ ሰይፉ)
።።።
እሱ ነው ~ እሱ
ዐይን ባይኖረው
ለምን ብርሀን ኖረ? የሚለው
እግር ባይኖረው
ለምን መንገድ ኖረ? የሚለው
.
እሱ ነው ~ እሱ
ከቀናቴ
ፀሀይቱን የሰረቀ
በመንገዴ
አሜኬላ ያፀደቀ።
@gGetem
@leoyri
ያለ ጥላ ልቁም!!!
ገጣሚ፦ ሚካኤል አስጨናቂ
አንባቢ፦ ሊዮ ማክ
የሆሄያት ህብር
#የጥበብ_ማዕድ
#ማጀቢያ፦ ቤርሳቤህ 👩
😍በየቀኑ አዳዲስ የግጥም ስራዎችን ለማግኘት ቤተሰብ ይሁኑ!!!
@gGetem
Comment_
@sirak6
#እኔ_አክሱምን_ልሁን !!!!
#ሰንበታት😍
#ከድንቅ አቀራረብ ጋር...
ከወደዱት ያንሸራሽሩት (Share)
ከአምስት አራት ኪሎ አንድ ሺህ እርምጃ ነው
(ሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ)

ሁሌም ቀኑ ሲመሽ እንዲህ ወደ ማታ
ስካርን አግብቼ
ባገኘሁት መጠጥ ራሴን ሞልቼ
በቀዝቃዛው ሌሊት እራፊ ለብሼ
ብርድ ያስጥል ይመስል ሲጋራ ለኩሼ
በአምስት ኪሎ መንገድ
አራት ኪሎድረስ
እመላለሳለሁ
እርምጃ ‘ቆጥራለሁ
ደ‘ሞ ቆም እላለሁ
እሷን አስባለሁ

"አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ
አንቺ ልጅ አንቺዬ
ሰመመን የሆነን ናፍቆትሽን አዝዬ
ከአምስት አራትኪሎ እመላለሳለሁ
መፍትሄው ምን ይሆን ይሄን ካንቺ እሻለሁ"
ደግሞ እንዲህ እልና እሷን አስባለሁ

በቀደም ሶስት ሆነው ትናንት አራት ሆነው
የምወዳትን ልጅ ከመሃል አጅበው
በዚህ ነው ያለፉ
አሁን እዚህ የሉም…
ጭር ብሏል ጎዳናው…
በረንዳ አዳሪዎች
የጎዳና ውሾች
ማጅራት መቺዎች ሁሉም እዚህ የሉም
እምጥ ይግቡ ስምጥ ይግቡ ማንም አላወቀም
ማንም አልጠየቀም

ጭር ብሏል ጎዳናው…
ጭርር ብሏል ጎዳናው!
እንጀራ ፈላጊ ሹፌር የሚነዳው
ላዳ ታክሲ ብቻ ሽውው ይላል እንዳሻው
የሹፌሩም የኔ የሁለታችን መንገድ ትርጉሙ ልዩ ነው

እርሱ እንጀራ ብሎ እኔ ፍቅሬን ብዬ
እመላለሳለሁ
የሄደችበትን መንገድ ተከትዬ

ይመስክር ጎዳናው
የስካር እርምጃን ስንት‘ግዜ እንደቆጠርኩ
ይመስክር ጎዳናው
የቆመችበት ጋር ስንት ቀን እንደቆምኩ

እዚህ ቦታ ነበር
ድህረ— ምረቃ ውቅያኖስ ፊትለፊት
ሳቂ ጓደኛዋ አንድ ቀልድ ነግራት
ስትስቅ የነበረው
እዚህ ቦታ ነበር
ጥቁር ጓደኛዋ በሳቋዋ የሳቀው

ወይኔ ሳቋ ደግሞ
መለዓክት ስመውት
ስመው አውግተውት ፍልቅልቅ እንደሚል
የስድስት ወር ጨቅላ
ይህን ሳቅ እኮ ነው ያፈራ ይመስል
እልቤ ላይ ተክላ
ቀልቤን የነሳቺኝ በሳቅ እኔን ገድላ

ወይኔ ሳቋ!
አሁን በዚህ ሰዓት…
ቀጭን ጓደኛዋን በስካር ደፍሬ
ደውዬ ላናግራት?
ቀልዱን ድገሚልኝ ባክሽ እኔም ልሳቅ
ብዬ ልለምናት?

ሳቋን እያሰብኩኝ
ቆሜያለሁ በብርዱ ቆሜያለሁ በሌሊት
ድህረ— ምረቃ ውቅያኖስ ፊትለፊት

መቆሜን እንዳየ ላዳ ታክሲ መጣ
ጠየቀኝ ኮንትራት
እባክህን ሹፌር ምንድነው ኮንትራት?
ይልቅ እሱን ትተህ
የምወዳትን ልጅ የትም ቦታ ሂደህ ለኔ ብለህ አምጣት!?

ይህ የላዳ ሹፌር እንጀራ ፈላጊው
ስካሬን 'ረስቶ እብደቴን እንዳየው
ከንፈሩን መጥጦልኝ ሄደ ባለታክሲው

ውይ ከንፈሯ ደግሞ!
አንድ የዋህ አፍቃሪ በእሷ ፍቅር ታምሞ
ወድያው ነው የሚድን በከንፈር ተስሞ
ስም የለሽ ከንፈሯን ባ‘ሳቤ እየሳልኩኝ
ያለቀ ሲጋራ ጥዬ እየለኮስኩኝ
በስካር እርምጃ መንገዱን ቀጠልኩኝ

ከአምስት አራት ኪሎ አንድ ሺህ እርምጃ ነው
‘ሚወዱትን ማጣት ግን ምን የሚሉት እርግማን ነው?

በቀደም እሮብ‘ለት
ሙዚየሙ ፊትለፊት
ለአንድ የኔቢጤ መፅውታው ነበረ
ምነው እርሱን በሆንኩ
በአስማተኛ ዓይኖቿ እንደዘበት አይታ
በሳንቲሙ ፈንታ መፅውታኝ ፈገግታ
ምነው ድኜ ባደርኩ የዛኑ‘ለት ማታ!

ዓይኗ ያው ዓይን ነው ከዓይን የተለየ
ከብርሃን ጎልቶ ወግቶ ያሰቃየ
"ወይ ተዓምር!" ይላል ሰው እንደኔ ያላየ
ወይ ተዓምር!!

በዓይኗ በከንፈሯ በሳቋ ሰክሬ
በፍቅር በናፍቆት በመጠጥ ሰክሬ
ክዋክብት የፃፉት የሕይወት መስመሬ
እንዲህ ነው የሚለው ዕጣ ፈንታ ክፍሌ?
ይህ ነው ክፉ እድሌ?

ወይኔ!
ደግሞ…
እኔ እሷን እንዳልሳለም በቃል እየደለለች
በዓይኗ እያሳመመች
በሳቅ እየገደለች
እሷ ግን እዚህ ስትመጣ
ማርያምን ትሳለማለች!

እኔም እሳለማለሁ መሳለም አይበለውና
በሷ ፍቅር ተጸብዬ አገኝ እንደው ብፅዕና

እና…
የሰከረ ሰው ጸሎት ተሰማ ሲባል ባልሰማም
እኔ ግን እጸልያለሁ ተሰምቶ የማያውቅ ጸሎት
እግዜሩ ጸሎቴን ሰምቶ ለ‘ኔ ለአፍቃሪው ቢያመጣት

"አባት ሆይ...
እንድወድዳት ፈቅደህልኝ
የወደዱትን አለማግኘት እንደምን ያለ ፍትህ ነው?
ኧረ በማርያም የማርያም ልጅ
እንዲሆን እንዲሆን አርገው?
እሷንም ምንድነው በላት የ‘ኔንም ልብ አጠንክረው
በስካርና በሲጋራ ተቃጥዬ‘ኮ ልሞት ነው!
አገልጋይህ ያንተ ባርያ የምለምንህ እንዲህ ነው
ታውቃለህ የ‘ኔን ሁኔታ ታውቃለህ የልቤን ሚስጥር
ድምፅ የለኝ እንዳላወድስ ቃል የለኝ እንዳልናገር
እኔ እንደሁ ብኩን ምስኪን ነኝ በፍቅር የምቸጋገር!?"

እንዲህ እላለሁ… እንዲያ እላለሁ
ከዚያም እንደገና እሷን አስባለሁ
ያለቀ ሲጋራ ጥዬ አዲስ እለኩሳለሁ
በስካር እርምጃ ቁልቁል እወርዳለሁ
ገጣሚ
ሰዓሊ
አፍቃሪ
ቆማሪ
የሚቃጠሩበት ሮሚና ካፌን
ማለዳን አልፌ
ጆሊ ባር አጠገብ ባ‘ዘን እደርሳለሁ
ፍቅር ያሳመመው
መጠጥ ያሰከረው
ስካር ያደከመው እኔን አገኛለሁ

በዛ በውድቅት ሌሊት ሚኒባስ ታክሲ ባይኖርም
ድምፅ ግን ይሰማል
ረዳት  ይጮኻል
"ሜክሲኮ ሜክሲኮ? አንድ ሰው ሜክሲኮ?"
እያለ ይጣራል
በዛ ውድቅት ሌሊት በሌለ ሚኒባስ
እኔ ግን አያለሁ
እሷ ስትገባ እመለከታለሁ
ሚኒባስ ይሄዳል እኔ እመለሳለሁ
አንቺ ሆዬ እያልኩኝ አንጎራጉራለሁ

"አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ
አንቺ ልጅ አንቺዬ
ሰመመን የሆነ ናፍቆትሽን አዝዬ
ከአምስት አራት ኪሎ እመላለሳለሁ
መፍትሄው ምን ይሆን?
ይህን ካንቺ እሻለሁ!"
ከአምስት አራት ኪሎ
አንድ ሺህ እርምጃ ነው
የሚወዱትን አለማግኘት
ምን የሚሉት እርግማን ነው?!
@leoyri
@gGetem
እንግጫ ጎዝጉዘን
በአሪቲው ቃና ጎጆዋችንን ሞልተን
ከባንክ እንደወጣ ወርቃማ ፈራንካ
የተዋበች ጠሀይ ታዛችን ስር ሞቀን፤
በአዲስ መሻት አዲስ ተስፋ...
የህይወት ወስከንባ ጀምረን ልንሰፋ
በወስፌ ቀዳዶች አክርማ እየዶልን
በአለላ ቆለምሸሽ ሊቀርብ እንጀራችን
ጀመርን መወጠን ዛሬ በዋዜማው
"ከህልማችሁ በፊት ሀገርን አብጁ"
የሚለውን ነብይ የለም የሚሰማው !
ነብዩ ይጮሀል አደባባይ ቆሞ
ዙሪያ ገባው ሁሉ ተሞልቷል ባታሞ
ድው ነው!      ድው.. .ድው
ድም ነው!       ድም.. .ድም
ወዲያም ሲማትሩ ወደዚህም ግድም።
አንዳንዱ ሲደክር...
ለአዲሱ ተስፋ ... ትከሻውን ሰብቆ
አንዳንዱ ያለቅሳል.. .በጦር መንደር ወድቆ።
"ኸረ ይቆይ መጨፈር.. . ይቅር ይሄ እስክስታ
ሀገር ካልተሰራ ... ቅርብ ላይ ነው ዋይታ
ግዴየለም.. .
ግድየለም.. .
ይደርሳል ዘፈኑ ... ይደርሳል ጭፈራ
እርቅን አስቀድሙ.. . ይቅር አታካራ
እዚህ ደጅ ቄጠማ.. .እዛ ማዶ ጅማት
እዚህ ማዶ ውስኪ... እዛ የደም መዓት
በሆነበት ቀዬ ... በሆነበት መንደር
በለቅሶ ውስጥ ዘፈን ... እንባ ላይ መጨፈር
እንዲህ ባለ ነገር ...
ህልም አይታለምም ... ተስፋም አይሳካም "
ብሎ የሚጮህን ያ ስጉ ፈላስፋ
አልነው  'አይነፋም' !!
በአዲስ ቀን ለአዲስ ህልም
ድም.. . ድም
ነብይ አናከብርም።

@gGetem
hottg.com/gGetem
የዘመነኛው ኑዛዜ!!

(ሚካኤል አስጨናቂ)

።።።።።

እንኳን አንተ አባቴ!

ጨለማው ምናብ ላይ ~ ፋኖስን ለኩሰህ

ከመሀል እስከ ጫፍ ~ የዞርከው ጀግነህ

ሀገርን በሌማት.. .

ለመቋደሻችን ~ ዘርግተህ የሰጠህ

ስንቱ ታሪክ አባሽ

ስንቱ አዳም አስለቃሽ

ገሀዱ እውነታው ~ ሀቅታው ታብሎ

ሀውልቱ ይቆማል.. .

ኧኸተማ መሀል ~ ዠግና ነው ተብሎ።

።።።።

እምዬ ሚኒልክ

የፅናታችን ልክ

ሀላፊ አግዳሚው ~ ታሪክህን ቢሰማ

አረሙን መንግሎ...

የባርነትን ጥግ ~ የሀሳቡን ጥሻ ~ መንጥሮ ቢያለማ

ለባንዳ ህመም ሆነህ ~ መቅደሱ ፊትለፊት ~ ቁምልን በግርማ።

።።።።

ቁምልን አባቴ!

በአክሊል አጊጥህ ~ ተውበህ በካባ

ልጓምህን አንቀህ ~ ኸፈረስህ ጀርባ

ማነው? ብለው ሲሉን ~ ንጉስ ነው እንድንል

ሸማችን ሲሳሳ...

ሀገር እንዳይበርዳት ~ ታሪክ እንድንፈትል

ወኔያችን ሲላላ...

ዳግም ዘራፍ ብለን ~ በስምህ እንድንምል

በዓለም ጎዳና ላይ...

ግዞተኛ ሆነን ~ እንዳንቆርጥ ተስፋ

ለምልክት ቆመህ...

የአርነት መለከት ~ በኩራት ይነፋ ።
@leoyri
hottg.com/gGetem
#ከምኞት_ባሻገር
የምስኪን አፍቃሪዋ ተግሳፅ..
         (በሊዮሪ)

ተመልክቼህ በሸራፋ ቀኔ
ቢሰወረር እኔነቴ
ጀመርኩ
ምኞቴን እየመዘንኩ!!!!!
ላልፈታ ገባው ከፍቅርህ ሉጋም፤
አሰሳዬ እጥግ ደርሶ ብደክም።

  እንደ መንገደኛ...

በ'ይታ ሰርጌ ከባህሩ እንብርት፤
አድማስ አልፎ አይኔ አንተ ባትኖርበት።
ቀለሜን አፍስሼ ብሩሹን ሰቀልኩት!!!!!!

እንደ ሰዓሊ...

ዜማ ስደረድር ከቅኔ 'የወጣው
የግጥሜ ድምፀት ጥል ሆኖ__ ቤቴንም ቢያፈርሰው፤
ብኩን እንጉርጉሮዬ አውንታሩን በጠሰው!!!!!!

እንደ አዝማሪ....

ከሌላኛው የነብስ ዋጋ ከሚታፈስበት፤
ሰማይን ዘወትር በአይኖቼ ዳስሴ ከማማትርበት።
አንተ ካለህበት ከስምህ ጉባዬ፤
ልቤ መልስን ሽቶ ከተመ ሱባዬ።
ናፍቆት  የከለለው ከፍቅርህ ገዳሜ፤
ልታቀብ ወሰንኩኝ ሲገባኝ ከርሜ።

በዚም...

ደግሞ እንደመናኝ....
ላንተ ካልታደልኩኝ አለም ሙሉ በቃኝ።

በቃኝ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!
ሊዮሪ
21/12/2013ዓ.ም
የሆሄያት ህብር🦋🦋🦋🦋
#የጥበብ_ማዕድ
🦋🦋🦋🦋
@leoyri
@gGetem
@gGetem
#እኔ_እንጃ



«ፍቅር አይቀናም» ይላል፣
ከፈጣሪ የተሰጠን የማይሻረው ቅዱሱ ቃል፣
አንድ ልቤም ይህን ያውቃል።
እኔ ግን ...
ቆሽቴ ድብን እስኪል ድረስ ጨጓራዬም እስኪከስል፣
ፊቴም አመድ እስኪመስል፣
ሰርክ ባንቺ እቀናለሁ በማይረባ ተራ ነገር፣
ቢሆንም ግን አልታከትኩም አፈቀርኩሽ ብዬ ላንቺ ሁሌ እንዳዲስ ከመናገር።


«ፍቅር አይታበይም» ይላል፣
ፅኑ ወንጌል ቅዱሱ ቃል፣
እርግጥ ልቤም ይህን ያውቃል።
እኔ ግን ...
ባደባባይ አብረን ስንዞር እቅፌ ውስጥ አስገብቼሽ ቸርችሬያለሁ እልፍ ጉራ፣
አንቺን የኔ በማድረጌም ደረት እና ትከሻዬን ሰብቄአለሁ በየተራ፣
ሰው እንዲያየን ተመኝቼም ተጓደድኩኝ ተጎብሬ፣
አፈቅርሻለሁ ግን እላለሁ ተመልሼ ደግሞ ዞሬ።


«ፍቅር ቸርነት ያደርጋል»፣
ይላል የፈጣሪ ቅዱስ ቃል፣
ይህም እውነት ልቤ ዘልቋል።
እኔ ግን አንቺን ብቻ ስል ግራ ቀኜን ፊት ነስቼ፣
ሁሉን ላንቺ ለመስጠት ስል ወዳጅ ዘመድ ወዲያ ትቼ፣
ቸር ማድረግን እረስቼው ተቆራኝቶኝ ንፉግነት፣
ላፍታም ቢሆን አልቦዘንኩም አፈቅርሻለሁ ግን ከማለት።


«ፍቅር በ እውነት ደስ ይለዋል»፣
ቅዱሱ ቃል እንዲያ ይላል፣
ልቤም ይህን ያስተውላል።
እኔ ግን ላንቺ ደስታ ስል ያልሆንኩትን ሆኜ አውቃለሁ፣
እየከፋኝ እስቃለሁ፣
እንዳላጣሽ እየሰጋው እየዋሸው ስንቴ አለፈ፣
አፈቅርሻለሁ ግን ከማለት ልቤ ዛሬም አላረፈ።


«ፍቅር አመፅን ይጠላል» ይላል፣
የተሰጠን የ ሕይወት ቃል፣
በልቤም ውስጥ ተሰንቋል።
እኔ ግን ...
በክፉ ያዩሽ ሲመስለኝ ምኑንም ገና ሳልይዘው ጥላቻ ውስጤ እየሞላ፣
አስሼ ፀብ በደላላ፣
ባንቺም ላይ ዓይኔ እየቀላ፣
ተጋጨው ካላፊ አግዳሚ፣
ቢሆንም ነግቶ አይመሽም አፈቅርሻለሁ የሚል ቃል ከኔው አንደበት ሳትሰሚ።


ሲጋጭብኝ ብታዘበው ላንቺ ያለኝ ጥልቅ ስሜት፣
ከማይሻረው ቃለ ህይወት፣
ይጨንቀኛል ይጠበኛል ይጠፋኛል ምገባበት።
ማቅ ለብሼም ተክዛለሁ ላንቺ እስካሁን ባይታይሽም፣
ፍቅር ከቃል በላይ ነው እንዴ? ወይንስ አላፈቅርሽም?
                             እኔ እንጃ!
#ሄኖክ_ብርሃኑ
@gGetem
@gGetem
@leoyri
#በርግጥ እንደ እህት ናት
ፍቅሯ ግን ነው ሚስጥር
አይነኳት ነገር
እሾህ የሷ አጥር !
ወደድኩሽ ልበላት?
ቀልድ ነው 'ሚመስላት
እርሷ እየሳቀች
ወንዱን እየራቀች
ነፍሷ ግን ለብቻ ጮሀ ትጣራለች
ለዛ ልስልስ ገላ ከለላ ትሻለች ።
ይገርማል
ያስፈራል !
ወደድኩሽ አትባል ...
ያ ጥርሷ  ይቀድማል።

(ሚካኤል• አ)
@gGetem
@leoyri

ህብረ ቀለማት ግጥሞች
#የወፈፌው ቃላት!!
(ሚካኤል አስጨናቂ)
።።።።።።።።።።።።።።።
ደግሞ ተነሳብኝ!
የአምና ካቻምናው ፥ የፊቱ እብደቴ
አንቺን ባየው ቁጥር.. .
ወፈፈ ሚያስብለኝ ፥ ህመም ምልክቴ።
ይኸው ፌስታል ሸረብሁ !
ቡልኮዬን ቀደድሁ
ገረባዬን ሸከፍሁ
ካላፊ ካግዳሚው ...
ቅጥሬን ለይቼ ፥ በፅኑ ተኳረፍሁ።
ብልሀት በራቀው ፥ መላ በሌለበት
ህመምን የሚያብስ...
ከንፈር መጣጭ ሀኪም ፥ ደጁን በሞላበት
ከተማ ሸሽቼ ...
ብቻዬን ወጥቼ...
ለሚሰግር ፍቅር ፥ መንገድ ላበጅለት
አበድሁ ስላንቺ ...
ያለ አንዳች ከልካይ ፥ ተመላለሺበት ።
ይኸው እንኪ ሰበዙን
የልምዱ እብደቴን...
በወስፌ ለይተሽ ፥ መሶቡን አበጂ
ተቀበይ ህመሜን!
አንጀትሽ እንዲርስ...
ከዳሩ ላይ ጨልፈሽ ፥ ወይንሽን ቅጂ ።
እንኪ ንሽማሽን!
ዘርጊው መዳፍሽን ...
ጠያቂው በተርታ ፥ በሰልፍ ተሰድሮ
ምን ክፉ አጊንቶህ
ከጤናህ ተሽረህ ፥ ሆንህ እንደ ድሮ ?
ብለው ሳይጠይቁኝ ....
#እኔም በተራዬ
"አዎን እንደዚህ ነው !
ሰው ፍቅርን ሊያነግስ ፥
ልቡን ተሸክሞ ፥ ሲወርድ ከገበያ
አቅልን የመሳት ፥ የእብደት መጀመርያ
ደግሞም የእውነት ህመም ...
መላወሻ አልባው ፥ ሀቀኛው በሽታ
ሰው ልቡን አቅርቦ ፥ ዘርግቶ በፎጣ
ሸማች ሲርቀው ነው ፥ የሚገዛው ሲያጣ "
ብዬ ሳልመልስ ፥ ሳይገለጥ ምክንያቴ
ፈጥነሽ ድረሽልኝ ፥ ተሿሚ ልዕልቴ ።
@leoyri
hottg.com/gGetem
ዓለም እድሜውን
(ሊዮ ማክ®)
አንድ ፥ሁለት ...አስር
ያለ --ምንም ስሌት ቀረሽ
አበቅቴ ቢገለበጥ
የኃሊዬሽ ዘመን ቢፈተሽ
እንደ ወጣ"የወጣ"
እንደ "ቀረ " የቀረ
እንደ ታለመ የሰመረ
እንደ--ሰመረ--የዘመረ
እንዳለ --ኖሮ
እንደኖረ --የኖረ
አንዳችም ነገር የለ
አለ፥ነበረ
ተብሎ ---የተነገረ።
ጠላት :---ሆኖ ያረጀ
ወዳጅ:---ሆኖ ያፈጀ
እንደ---በጀ፥እንደ --ጎዳ
እንደ---ጎዳ እንደ--በጀ
ሣይኖር ነው የኖረ
ዓለም እድሜውን የፈጀ።
----------------------
@leoyri
hottg.com/gGetem
የይቅርታ መሐልይ👐
ገጣሚ፦ በእውቀቱ ስዩም
አንባቢ፦ ሊዮ ማክ
የሆሄያት ህብር
#የጥበብ_ማዕድ
#ማጀቢያ፦ሲታ አዳም 👩
😍በየቀኑ አዳዲስ የግጥም ስራዎችን ለማግኘት ቤተሰብ ይሁኑ!!!
@gGetem
Comment_
@sirak6
ከወደዱት ያንሸራሽሩት (Share)
📶Medium Quality🆓
እንኳን ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳቹ!!!!
@gGetem
@leoyri
💚💛
አድዋ
#ገጣሚ_ሊዮ_ማክ
የሆሄያት ህብር💙💙💙
#የጥበብ_ማዕድ
#ማጀቢያ_ኤደን_ሙላት
እንኳን ለ128ኛው የአደዋ ድል መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን!!!
#አድዋ
#አድዋ
#አድዋ
💚💛💚💛💚💛💚💛💚💛💚💛💚💛
@gGetem
@gGetem
hottg.com/leoyri
HTML Embed Code:
2024/06/07 13:17:43
Back to Top