ኦፌኮ ከተመድ የውጭ መረጃ አሰባሳቢ ልዑክ ጋር በ2018 ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ተወያየ፤ የምርጫ ቦርድ እንደገና ማዋቀርን ጨምሮ ቁልፍ ጥያቄዎችን አቀረበ!
የኦሮሞ ፌዴራላሲት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በ2018 ዓ.ም. በሚካሄደው 7ኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ዙርያ ውይይት ማድረጉን አስታወቀ።
በኦፌኮ ዋና ጽ/ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም የተገኙ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ህብረት ቢሮ (UNOAU) የምርጫ ድጋፍ ክፍል ዋና ኦፊሰር የሆኑት አኪንየሚ ኦ. አዴግባላን ጨምሮ አራት አባላትን የያዘ ልዑክ መገኘቱን ከፓርቲው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኦፌኮ በስብሰባው ላይ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተአማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲረጋገጥ መንግስት ሊያሟላቸው የሚገቡ "መሰረታዊ" ጥያቄዎችን ማቅረቡ ተጠቁሟል።
የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ኦፌኮ በ2018 ምርጫ ላይ መሳተፉ ሙሉ በሙሉ "በመሠረታዊ እና በተጨባጭ ለውጦች" ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።
"ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ድምፅ የመስጠት ቴክኒካዊ ሂደት ብቻ አይደለም፤ የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት ነው" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ "ይህ ሂደት ዛሬ በኢትዮጵያ የለም። በጦርነት እና በፖለቲካ ስደት ውስጥ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም" ሲሉ አክለዋል።
ኦፌኮ በ2018 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ መሠረታዊ ተቋማዊ እና ህጋዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የጠየቀ ሲሆን የምርጫ ቦርድን እንደገና ማዋቀርን ጨምሮ የምርጫ ስርዓት ማሻሸያ እንዲደረግ እና ከምርጫ በፊት በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ ላይ ለመስማማት የሚያስችል ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም በኦሮሚያና በመላ ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲቆም፣ የኦፌኮ አባላት፣ አመራሮችንና ደጋፊዎችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰው ማስፈራራት፣ ወከባና እስራት እንዲቆም እና የጸጥታ ሀይሎች በፖለቲካው ሂደት ውስጥ ገለልተኛ የሚሆኑበት ስምምነት እንዲፈረም ጠይቋል።
@YeneTube @FikerAssefa
>>Click here to continue<<