ዜና: "የኃይሌ ኃይሎች" የተሰኘና በአንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የስኬት ሚስጥሮች ዙርያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለምርቃት ሊበቃ ነው
"የኃይሌ ኃይሎች" ወይም 'Dissecting Haile' የተሰኘና በአንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት ስኬት ሚስጥሮች ዙርያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለምርቃት ሊበቃ መሆኑ ተገለጸ።
የመጽሐፉን ምረቃ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ መርሀግብር ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ተካሄዷል።
በመርሀግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የመጽሐፉ ደራሲ እና የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ልጅ ሜላት ኃይሌ መጽሐፉ ስለ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት ፍልስፍናዎች የሚዳስስ መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም መከራን ወደ ተጽዕኖ ለመለወጥ ለሚፈልጉ ሰዎች ምሳሌ የሚሆን እና ከሀይሌ ገብረስላሴ የህይወት ስኬቶች ጀርባ ያሉ ሚስጥሮችን ያካተተ መጽሐፍ መሆኑን ተናግረዋል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በመርሀግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን "ብቻን ሆኖ ጀግና መሆን አይቻልም: እኔም ከቤተሰብ ጀምሮ የማህበረሰቤ ውጤት ነኝ" ብለዋል።
አክለውም በመጽሐፉ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች ምስጋና አቅርበዋል።
"የኃይሌ ኃይሎች" /Dissecting Haile/ በ12 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንዲሁም በብሬል የተሰናዳ እንደሆነም ተገልጿል።
መጽሐፉ የፊታችን ነሐሴ 2017 ዓ.ም በኤሌክትሮኒክስ እና በሀርድ ኮፒ አማራጮች በይፋ ለአንባቢያን ይቀርባል ተብሏል።
>>Click here to continue<<
