ደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ባጋጠመበት በአሁኑ ወቅት ለአለምአቀፉ የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ 12,000 ሜትሪክ ቶን ሩዝ ለገሰች!
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኢትዮጵያ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ ስራ የሚውል 12,000 ሜትሪክ ቶን ሩዝ ድጋፍ ከደቡብ ኮሪያ መንግስት መቀበሉን አስታወቀ።ዕርዳታው የተገኘው በሀገሪቱ የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም ሰብአዊ ተግባራት በገንዘብ እጥረት ምክንያት እየተስተጓጎለ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ነው።
ድጋፉ በሶማሌ ክልል ለሚገኙ ከ400,000 በላይ ተጋላጭ ሰዎች እና በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ለሚኖሩ 330,000 ስደተኞች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማቅረብ ይረዳል ተብሏል።የርክክብ ስነ-ስርዓቱ ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም አዳማ ከተማ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ዋና የሎጂስቲክስ ማዕከል ተካሂዷል።
በስነስርዓቱ ላይ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ፣ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የምግብ አቅርቦትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ አመንሲሳ ቱፋ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ መንገሻ፣ እንዲሁም የአለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይና ዳይሬክተር ዝላታን ሚሊሺች ተገኝተዋል።
በርክክብ ስነስርዓቱ ወቅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተወካይ ዝላታን ሚሊሺች ለተደረገው ዕርዳታ ምስጋናቸውን ገልጸው፣ “በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወገኖች ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት ባለበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ ድጋፍ ላደረገልን ለኮሪያ መንግስት ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለዋል።አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው ደግሞ የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያን ታሪካዊ ትስስር አስታውሰው፣ “በኮሪያ ጦርነት ወቅት ደቡብ ኮሪያን ለመደገፍ ወታደሮችን ከላኩ ጥቂት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች ፈጽሞ አልረሳንም” ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአለም የምግብ ፕሮግራም በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በምትገኘው የሽሬ ከተማ የሚገኘውን ቢሮውን በሰኔ ወር መጨረሻ እንደሚዘጋ ማስታወቁ ይታወሳል።የአለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የምታስተናግደው ሽሬ የሚገኘውን ቢሮውን በሰኔ ወር ለመዝጋት የተገደደው ከበጀት እጥረት በተጨማሪ “አሰራሬን መልሼ ለማዋቀር” በሚል መሆኑን አስታወቋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ21.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ 16.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ናቸው።
Via AS
@YeneTube @FikerAssefa
>>Click here to continue<<
