አለሌ ነበርኩ ። ከህንድ እስከ እብድ የቀረኝ የለም የምል አለሌ። የተኛኋቸው ሴቶች ጠቢቡ ሰለሞን ከተኛቸው የሚያንስ አይደለም አልቆጠርኳቸውም እንጂ።
ጀንጅኜ መዳረሻዬ ማራኪ ሆቴል ነው ።ሆቴሏ ሸጎጥ ያለች ሰዋራ ስፍራ ነች ፤ ከመኖርያዬም እሩቅ ነች ።
አስተናጋጆቹም ምቹ ናቸው። በእርግጥ ጉርሻ ምቹ የማያደርገው የለም ። ፈረንጁ እና መስኪ የሚባሉ አስተናጋጆችን የበለጠ አውቃቸዋለሁ ።
ጠብ እርግፍ ብለው ያስተናግዱኛል ፤ በእርግጥ መስኪ የምትባለው ትንሽ ተለቅ ትላለች ።
ፊት ከሰጠሁት ይጎነትለኛል ብላ ይሆን ፣ ተፈጥሮዋ ሆኖ ይሆን ፣ ነፍፍ ቺክ ስለማመላልስ ይሆን ፣ ስለማጨስ ወይም ስለምጠጣ ይሆን እኔ'ንጃ ብቻ
አትስቅልኝም አትኮሳተርብኝም ።
ፊቷ አልሰጥም።።ን ቢሸኝም ውበቷ ግን እንዳለ ነው። መስኪ ምንም ያህል ቲፕ ብሰጣት አመሰጋገኗ ሆነ አስተያየቷ አይለይም ተመሳሳይ ነው ።
ክላሴ ውስጥ አጭሼ ፣ ጠጥቼ ፣ ባልጌ ሹልክ ብለን በጓሮ እንሄዳለን ። በሌላ ቀን ሌላ ቺክ ይዤ እመጣለሁ ፣ ካልጠረረብኝ ቺክ አልገርብም ።
ሁሉንም እንደሙዳቸው እና እንደፍላጎታቸው እሰክሳቸዋለሁ ።
ላጤነቴ በነፃነት ታየው አልታየው ብዬ ሳልሳቀቅ ለመባለግ አግዞኛል።
ጓደኞቼ ሁሉ ሲያገቡ ፤ ቤተሰቦቼ የአታገባም ውትወታ የበረታ ወቅት ሶልያና የምትባል ልጅ ተዋወቅኩ ።
ባገኘኋት በሁለተኛ ቀን ለመቾመስ በት በት አልኩ አልተሳካልኝም ።
በውስጤ ስንቷ እንደ አንቺ አካብዳ ጭኗን ሳትከፍት የቀረች የለችም ብዬ ፈገግ ስል ምነው አለቺኝ
እርጋታሽ ደስ ይላል አልኳት
ውስጤ እንደላዬ የተረጋጋ እንዳይመስልህ አለቺኝ ። ይሆናል ግን ውስጥም ላይም አንድ ላይ ከመንቀዥቀዥ ይሻላል አልኳት ከንፈሯን ገለጥ አድርጋ ሳቅኩኝ አይነት አለቺኝ
በነገራችን ላይ
አንተም ረጋ ያልክ ነክ አለቺኝ... ስስቅ ። ውስጥህ ወዲ ወዲያ ስለሚል ነው እርጋታህ ያልታወቀህ አለችኝ ።
ይሆናል አልኳት
ሶልያና የበዛ እርጋታ አላት ፥ እርጋታዋ ይረብሸኛል ከደስታ ይልቅ ለድብርት አጋልጦ ነው የሚሰጠኝ።
አብሪያት የምሆነው እስከምደክላት ብቻ ነበር።
ትፈልጋለች ብዬ የማስበውን እነግራታለሁ ። ሲኒማ እጋብዛታለሁ ፤ ትያትር ትጋብዘኛለች ከንፈሯ ጋ ሳልደርስ ቀናቶች ነጎዱ
በጭራሽ የወሲብ ወሬ ለማውራት አታመችም ። ወሲብ ነክ ከተወራ ለመቀጠል ፊቷ አይጋብዝም።ወሲብ ነክ ወሬ ካወራሁ ለይሉኝታ እንኳን ፈገግ አትልም።
መንፈሳዊ ጉባኤ ትጋብዘኛለች። ለእሷ ደስ እንዲላት አንዳንድ አሰልቺ ፣ አንዳንድ ማራኪ ስብከቶችን እሰማለሁ ።
ቀልቧን ለመግዛት መንፈሳዊ መፅሃፍ እያነበብኩ ፤ በጉዳዩ ላይ ሰፊ እውቀት አለኝ ወሬ ሳወራት ቀልቧ ሲሳብ ወሬው ሲጥማት አያለው።
ሳይታወቀኝ የኔን መንገድ እየተውኩ በእሷ መንገድ መመላለስ ቀጠልኩ ።
ከሌሎች ስለተለየች ይሆን ፣ እንደምፈልገው
አለመሆኗ ይሆን ፣ የምፈልገውን ስላልሰጠቺኝ ይሆን ብቻ ቀልቤን ገዝታዋለች።
ውሎዋን ስራዬ ብዬ እከታተላለሁ ። ካልተደዋወልን ይታወቀኛል ። እንቅስቃሴዋ እየገቡኝ መጡ ። ሳላገኛት የት እና ምን እያረገች እንደሆነ መገመት ቻልኩ ።
ከደወለችልኝ ስግብግብ ብዬ አነሳለሁ ። በሂደት መንገዷ ምቾት ሰጠኝ ። ከተመላለስኩበት መንገድ በተሻለ ይሄኛው መንገድ ጣፈጠኝ
የድሮ አመሌ ውል ሲለኝ የምቀመጭላቸው ቺኮች ውልብ ብዬባቸው ሲደውሉ ሳላቅማማ የድሮ ስልክ ቁጥሬን ቀየርኩ ።
የትላንት የውድቀት መንገዳችንን ካልቀየርነው ለለውጣችን ሳንካ ይሆናል ።
አሁን ፈልጌ መፅሃፍ ቅዱስ አነባለሁ፤ እፆማለሁ ጉባኤ እከታተላለሁ ።መንፈሳዊ ጉዞ እሄዳለሁ ። ከሶሊያና ጋ እንፋቀራለን። የትላንት መንገዴን አልተረኩላትም ለዛሬው ማንነቴ ግን ማሃንዲሷ እሷው ናት ።
ለአምላኬ ስንቴ በእሷ ምክንያት ምስጋና እንዳቀረብኩለት። የትላንት ህይወቴን እንዴት አሁን እንደማልወደው ። ስለ ሴት አውልነት ሲነሳ ምንም ሃሳብ አልሰጥም ያ ዘመን ያሳፍረኛል።
ሶልያና አንድ እለት ስትፍነቀነቅ መጣች ምነው ስላት እቴቴ ስራ አገኘች አለቺኝ የት ስላት ባንክ
በቀላሉ ፍንክንክ የምትል አይደለችም የእናቷ ጉዳይ ግን ስስ ጎኗ ነው። ብቻዋን ስላሳደገቻት ይሆን ሁሉ ነገሯ ስለሆነች ይሆን ብቻ ስፍስፍ ትልላታለች።
ምን እንደምትሰራ አላውቅም ። በትምህርት ብዙ ያልገፋች ስለሆነች የት እና ምን ትሰራለች ብዬ አልጠየኩም ፤ እሷም ስራ ነች አልመጣችም ፣ ስራ ቀረች ነው እንጂ የት እና ምን እንደምትሰራ ነግራኝ አታውቅም ።
በጥንጡም በግዙፉም ወሬዎቾ መሃል እቴት ሳትል አትውልም ።
የድሮ ስራዋስ ስላት ። ውይ የድሮ ስራዋን እኮ አትወደውም ግድ ሆኖባት እንጂ አለቺኝ።
ስለ እኔ እንደነገራቻት እና እንደወደደቺኝ የነገረቺኝ እለት እንዴት ደስ እንዳለኝ ።
ባሻዬ ብላ ቴክስት አደረገችልኝ ። ደስ ስላት እና ስትቀልድ ባሻዬ ነው የምትለኝ ። ከእቴት ጋ እንደምንመሳሰል ነግሬህ አውቃለሁ ኣ ስትለኝ ሁሌ ብዬ የሳቅ ስቲከር ላኩላት ።
እንደ እሷ ቆንጀ ነኝ ግን ብላ ፎቶዋን ላከችልኝ ።
ማመን አልቻልኩም
ክው
ድርቅ አልኩ
የላከችልኝ ፎቶውን አገላብጬ አየሁት ፤ አልቀየር አለ ። የማራኪ ሆቴል አስተናጋጅ መስኪ የሶሊያና እናት ናት ፤ ሁለት አብረው ሆነው እና አንድ የመስኪን ማራኪ እንግዳ መቀበያ ጋ የተነሳችውን ፎቶ ላከችልኝ ።
ውስጤ ታወከ ።
ያ ሴት አውል አብርሃም ፤ ያ በየጊዜው ለቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሴቶችን የሚያጋድመው ፣ የሚያጨሰው አብራሃም ፤ ያ በጥሩ አይን አይታው የማታውቀው አብራሃም ፤ የአንድ ልጇ ሶሊያና እጮኛ ነኝ ብሎ ፊቷ እንዴት ይቆማል??
ትላንቴ ተከተለኝ። እግዜር በተፀፀትንበት ትላንታችን ይቀጣናል እንዴ? ስንቴ ያመሰገንኩበት ጉዳይ መጨረሻው እንዴት እንደዚህ ሆነ ??
የማደርገው ጠፋኝ ። ጠፋሁ ። አንዳንድ ትላንት ትላንት ላይ ብቻ አይቆምም።
© Adhanom Mitiku
>>Click here to continue<<