ዐሹራ የሙሐረም ወር ዐስረኛው ቀን ነው። የዐሹራን ቀን መጾም ተወዳጅ ነው። በርካታ ትሩፋቶች እንዳሉት በሐዲሶች ተዘግቧል። ነገር ግን በተጨማሪነት ዘጠነኛውን ቀን ወይም/እና ዐስራ አንደኛውን ቀን ጨምሮ መጾምም ተወዳጅ ነው።
ይህንን በተመለከተ በሶሒሕ ሐዲሶች የተገኙትን ተከታዮቹ ዘገባዎች እንመልከት። በመልካም ኒያ እንጹም። ቤተሰቦቻችንንም እንቀስቅስ!
ከዐብዱላህ ኢብኑ አቢ የዚድ እንደተዘገበው፡-
"ኢብኑ ዐባስ ስለ ዐሹራ ጾም ተጠይቀው እንዲህ ሲሉ ሰምተዋቸዋል፡- "እንደዚህ ቀን የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሌሎች ቀናት አስበልጠው፣ ትሩፋቱን ከጅለው ሲጾሙት የማውቀው ቀን የለም። ከዚህ ወር (ከረመዳን) በላይ ከወራት መካከል አስበልጠውት የጾሙት ቀንም አላውቅም።"
በሌላ ዘገባ ኢብኑ ዐባስ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡-
"የዓሹራ ጾም ያለፈውን ዓመት ኃጢኣት ያሰርዛል ብዬ ከአላህ እከጅላለሁ።"
ሙስሊም ዘግበውታል።
ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው፡-
"የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መዲና ሲገቡ አይሁዶች የዓሹራን ቀን ሲጾሙ ተመለከቱና "ለምንድን ነው የምትጾሙት?" በማለት ጠየቁ። "ይህ መልካም ቀን ነው። አላህ ሙሳን (ዐ.ሰ) እና የእስራኤል ልጆችን ከጠላቶቻቸው ያዳነበት ቀን ነው። ሙሳ (ዐ.ሰ) ጾመውታል።" አሉ። የአላህ መልእክተኛ ዓሹራን ጾሙ። ሌሎች ሰዎች እንዲጾሙም አዘዙ።"
ቡኻሪ ዘግበውታል።
>>Click here to continue<<