ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ ከተማ ለዘጠኝ ዓመታት ቆይቷል። ከኢየሩሳሌም ውጭ የአሕዛብ ከተማ በነበረችው በአንጾኪያ የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፋ። ከኢየሩሳሌም የተሰደዱት ክርስቲያኖች የአንጾኪያን ሕዝብ ተግተው በማስተማራቸው ዝናው እስከ ኢየሩሳሌም ደረሰ። በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበሩት አበው በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላኩት። በርናባስ የግሪክ ቋንቋ ችሎታ ያለውን፣ ከማንኛውም ሰው ጋር መግባብ የሚችለውን፣ ደግሞም እግዚአብሔር ለአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠውን ቅዱስ ጳውሎስን ከጠርሴስ በማምጣት በአንጾኪያ ሥራቸውን ጀመሩ።
የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያው ጉዞ ያደረገው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ጥሪ በአሕዛብ ሀገር ወንጌልን ለመስበክ ከበርናባስ ጋር ወጡ። ይህም ጉዞ የተከናወነው በ፵፮ ዓ.ም.አካባቢ ነው። የተሸፈኑትም ሀገሮች ሲሊንውቂያ፣ ቆጵሮስ፣ ስልማን፣ ጳፋ፣ ጰርጌን፣ ገላትያ፣ ጵስድያ፣ ኢቆንዮን፣ ሊቃኦንያ፣ ልስጥራ፣ ደርቤን፣ ጵንፍልያ፣ አታልያና አንጾኪያ ናቸው።
ሁለተኛው ጉዞ በ፶ ዓ.ም. ገደማ የተከናወነው ነው። በመጀመሪያው ጉዞ ማርቆስ አብሮ ተጉዞ ነበር። ነገር ግን ጵንፍልያ ከተማ ሲደርስ እናቱ ስለናፈቀችው መመለስ በመፈለጉ በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞት መጣ። ስለዚህም በሁለተኛው ጉዞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ወደ ኪልቂያ ሶርያ ሲጓዝ በርናባስ ደግሞ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። በዚህ ጉዞው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ግሪክ ደርሶአል። የተጓዘባቸውና ያስተማረባቸው ከተሞችም፦ ደርብያ፣ ልስጥራ፣ፍርግያ፣ ገላትያ፣ ሚስያ፣ጢሮአዳ፣ ሳሞትራቄ፣ ናፑሊ፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄ፣ በርያ፣አቴና፣ ቆሮንቶስ፣ አንክራኦስ፣ አፌሶን፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ያገኘው በዚሁ ጉዞው በልስጥራ ከተማ ነው።
ሦስተኛው ጉዞ የተከናወነው በ፶፬ ዓ.ም. ሲሆን የተሸፈኑትም ሀገሮች ገላትያ፣ ፍርግያ፣ ኤፌሶን፣ መቄዶንያ፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆሮንቶስ፣ ጢሮአዳ፣ አሶን፣ ሚልጢኒን፣ አንጠቀከስዩ፣ ትሮጊሊዩም፣ መስጡ፣ ቆስ፣ ሩድ፣ ጳጥራ፣ ጢሮስ፣ ጵቶልማይስ፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ዕርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በመያዝ ሦስተኛውን ጉዞ አጠናቅቆ ኢየሩሳሌም ገባ። ነገር ግን ኢየሩሳሌም የገባበት ጊዜ የፋሲካ በዓል ስለነበር ከልዩ ልዩ ሀገሮች የተሰበሰቡ አይሁድ በከተማዋ ነበሩ። እነዚህ በዝርወት የሚኖሩ አይሁድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በየሀገራቸው በትምህርቱ የተነሣ ሲቃወሙት የነበሩ ናቸው።
የቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕትነት
ለሐዋርያነት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሳምኗል፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት አዘጋጅቷል (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፲፱-፳፫)፡፡ ወንጌልን በመስበኩ ምክንያትም ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡ በልብሱ ቅዳጅም ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፲፱፥፲፩)፡፡
አገልግሎቱን ሊፈጽም ሲልም የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር የክርስቲያኖች ቍጥር እየጨመረ የመጣው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በመማረካቸው ምክንያት መኾኑን ተረድቶ፤ ይልቁንም የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሳይቀር በቅዱስ ጳውሎስ በመማረካቸው ተቈጥቶ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎው አስቀረበው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ንጉሡንና ወታደሮችን ሳይፈራ የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነትና አምላካዊ ሥልጣን ይመሰክር ነበር፡፡
ንጉሡም በቍጣ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡ ወደሚገደልበት ስፍራ ሲወስዱትም በንግግሩና በአስተያየቱ ዅሉ ምንም ፍርኀት አይታይበትም ነበር፡፡ እንዳውም በጦርነት ድል አድርጎና ማርኮ እንደ ተመለሰ ወታደር ይደሰት ነበር እንጂ፡፡ ለሚገድሉትም ይቅርታን ይለምን ነበር፡፡
በመጨረሻ በ፷፬ ዓ.ም. ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ምን እንደምትመስል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት። የሮም ሕዝብ በከተማው መቃጠል በማዘኑና በማመፁ ነገሩን ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ። በዚህም የተነሣ ክርስቲያን የተባለ ሁሉ መሰደድ፣ መሠየፍ፣ መታረድ እጣ ፈንታው ሆነ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኒቆጵልዮን ከተማ ሲያስተምር በ፷፭ ዓ.ም. ተይዞ ወደ ወኅኒ ገባ። ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ ቤት ታሥሮ ከቆየ በኋላ በ፸፬ ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ አንገቱን ተሰይፎ በ፷፯ ዓ.ም. ሐምሌ ፭ ቀን በሰማዕትነት ዐረፈ።
እንደ ማጠቃለያ
>>Click here to continue<<