+ ስንናደድ ለምን እንጮሃለን? +
🔥🍂🔥🍂🔥🔥🍂🔥🍂🔥
አንድ ብልህ አረጋዊ አባት በገዳም የሚኖሩ ደቀ መዛሙርትን ሰብስበው እንዲህ ሲሉ ጠየቋቸው :-
"ስንናደድ ለምን እንጮሃለን?
ሰዎች ሲበሳጩ ስለምን እርስ በእርሳቸው ይጯጯሀሉ?"
ደቀ መዛሙርቱ ለጥቂት ደቂቃ ዝም ብለው ካሰቡ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ ተነስቶ እንዲህ ሲል መለሰ :-
"ስንናደድ መረጋጋት ስለሚያቅተን እንጮሀለን።"
አረጋዊው አባትም ቀጠል አድርገው
"አብሮህ ያለው ሰው ከአጠገብህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ስለምን ትጮህበታለህ?
በለሰለሰ ድምፅ መነጋገር የማይቻል ነገር ነውን?
ስትበሳጭ ስለምን ሌላኛው ሰው ላይ ትጮሀለህ?"
ደቀ መዛሙርቱ በየተራ እየተነሱ የመሰላቸውን ኹሉ መለሱ ።
ነገር ግን የአንዱም ደቀ መዝሙር ምላሽ እኚህን ብልህ አረጋዊ አባት ስላላረካቸው የራሳቸውን ጥያቄ እንዲህ ሲሉ መለሱ:-
"ሁለት ሰዎች በሚበሳጩበት ሰዓት ልባቸው እጅግ ይራራቃል።
ይህን ርቀት ለመቀነስ እና ለመደማመጥ ደግሞ የግድ መጮህ አለባቸው!
አምርረው በተቆጡ መጠን በመካከላቸው ሰፊ መራራቅ ስለሚፈጠር ለመደማመጥ ይበልጡን መጮህ ግድ ይላቸዋል።
ቀጠሉና አረጋዊው አባት ሌላ ጥያቄ አስከተሉ :-
"ሁለት ሰዎች ሲዋደዱስ ምን ይፈጠራል?
ከመጯጯህ ይልቅ በለሰለሰ ድምፅ ያነጋገራሉ።
ለምን ካላችሁኝ ምክንያቱ ልባቸው በጣም ስለሚቀራረብ ነው! በመካከላቸው ያለው ርቀት ጥቂት ስለሚሆን እጅጉን እየተዋደዱ በመጡ ቁጥር ቃል ማውጣቱንም ትተው በሹክሹክታ ያወራሉ።
በመጨረሻም መንሾካሾክም ሳያስፈልጋቸው ዓይን ለዓይን በመተያየት ብቻ ይግባባሉ።
እንዲህ ነው ሁለት የሚዋደዱ ሰዎች የሚቀራረቡት ።"
"በምትከራከሩ ጊዜ ልባችሁ እንዲራራቅ አትፍቀዱለት፣ይበልጥ የሚያራርቃችሁንም ቃላት አትጠቀሙ! ምክንያቱም አንድ ቀን በመካከላችሁ ያለው ርቀት እጅግ ከመርዘሙ የተነሳ ዞሮ መመለሻው መንገድ ይጠፋባችኋል!"
"ፍቅር ልብን የተረጋጋ እና ሕይወትን የሚሰጥ ሲያደርገው በአንጻሩ ጥላቻ ደግሞ የተረበሸ ያደርገዋል በዚህም ሌላውን የሚጠሉ ራሳቸውን ያሰቃያሉ! ከፍቅር በላይ ምን ጣፋጭ ነገር አለ?"
"ለእኛ ያለህ የማይቋረጥ ፍቅርህ ከአባትም፣ ከእናትም ፣ ከሚስት እና ከባልም የሚበልጥ አቤቱ ፍቅር የሌለን ባሪያዎችህን ማረን አሜን!!!"
ምንጭ :- አባ ዮሐንስ ክሮንስታት የተባሉ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባት እንደጻፉት
ትርጉም :- ዲ/ን ዶ/ር ዳዊት ከበደ
>>Click here to continue<<