+++የሕፃናት ጥምቀት+++
አዳምና ሔዋን ሕግ አፍርሰው ከተከለከሉት ዛፍ ፍሬ ከበሉባት ሰዓት ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተገፈው እርቃናቸውን ቀርተዋል፡፡ በወቅቱም የተሰማቸውን እንግዳ የሐፍረት ስሜት መቆጣጠር ስለተሳናቸው ዕርቃናቸውን የሚሸፍኑበትን ቅጠል በገነት ካሉት ዛፎች ቆርጠው በሰውነታቸው ላይ አገለደሙ፡፡ እግዚአብሔርም ከገነት ባስወጣቸው ጊዜ ያገለደሙት የቅጠል ስፌት የዚህን ዓለም ብርድ እንደማይቋቋምላቸው ስላወቀ ከእንስሳት ለምድ የተዘጋጀ የሚሞቅ የቁርበትን ልብስ አለበሳቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የሰው ልጅ ሁሉ ልብስ ያስፈልገው ጀመር፡፡ የዕድሜ ክልል ገደብ ሳይኖረው አረጋዊውም ፣ዛሬ የተወለደውም ሕፃን በጨርቅ የሚጠቀለል ሆነ፡፡
ማንኛውም ሕፃናት ልጆች ያሉት ጤናማ ወላጅ ልጆቹ የልብስን ጠቀሜታ ስላልተረዱ ‹አድገው እስኪረዱት ድረስ እርቃናቸውን ይቆዩ› በማለት እንደማይተዋቸው የታወቀ ነው፡፡ ምንም ክፉና ደጉን ባይለዩ፣ ራቁት የመሆን የሐፍረት ስሜት ባያሸንፋቸውም ፤ ከጤናቸው አንጻር በብርድ እንዳይታመሙበት ሲል ለልጆቹ በማሰብ ልብስ ያለብሷቸዋል፡፡
የሰው ልጅ ሥጋዊ ወይም ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ፍጥረት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለግዙፍ ሥጋው መጎናጸፊያ ልብስ እንደሚያስፈልገው ፤ ለረቂቅ ነፍሱም ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ በልብስ ያልተሸፈነ ሰውነት ለብርድና ለተለያዩ በሽታ አምጪ ሕዋሳት እንደሚጋለጥ ፣እንዲሁ በልብስ ያልተሸፈነች ነፍስም በኃጢአት ከሚመርዟት አጋንንት ማምለጥ አትችልም፡፡ ታዲያ ይህ የነፍሳችን ልብስ ምንድር ነው? እንዴትስ ነው የምትለብሰው?
ድንኳን ሰፊ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነፍሳችን ስለምትለብሰው ረቂቅ በፍታና ስለምትለብስበትም መንገድ ምንነት ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል› ሲል ይናገራል (ገላ 3፡27)፡፡ ከዚህም የሐዋርያው ትምህርት በመነሣት የነፍስ ልብስ የተባለው ‹ክርስቶስ› ሲሆን ፤ እርሱን የምንለብስበት መንገድ ደግሞ ‹ጥምቀት› መሆኑን እንረዳለን፡፡
በዛሬ ጽሑፋችን ምሥጢራትን በመመገብ የእናትነት ድርሻዋን የምትወጣው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ለምን በሕፃንነት ዕድሜያችን እንድንጠመቅ እንደምታደርገን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሣ በተቃራኒ የትምህርት ጎራ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ከሚያቀርቧቸው የተቃውሞ አሳቦች መካከል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛው ‹ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ› የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስን የስብከት ቃል ይዘው ‹እነዚህ የምታጠምቋቸው ሕጻናት ምን ኃጢአት አለባቸው?› ሲሉ የሚጠይቁት ሲሆን ፣ሁለተኛው ደግሞ ‹ገና ሕጻናት ሲሆኑ ምን አውቀው ነው ያለ ፈቃዳቸው የምታጠምቋቸው?› የሚል ከማወቅ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38)
የመጀመሪያው ጥያቄ የጥምቀትን ጥቅሞች ካለመረዳት የመጣ ጥያቄ ይመስላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀት ከሚፈጸምባቸው ምክንያቶች አንዱ ለኃጢአት ስርየት እንደሆነ ቢናገርም ‹ለኃጢአት ሥርየት ብቻ› ግን አይልም፡፡ ከሁሉም በላይ በጥምቀት የምናገኘው ትልቁ ጸጋ ‹ልጅነት›ን ነው፡፡ ስለዚህም ታላቅ ጸጋ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ አለቃ ለኒቆዲሞስ ‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ… › በማለት በጥምቀት ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት አስተምሮታል፡፡(ዮሐ 3፡5) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአት ፣በደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ፤ ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ ልትሰጣቸው ነው፡፡
ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስንመጣ በራሱ በጥያቄው መነሻ አሳብ ላይ የምንመለከተው እንደ ገደል የሰፋ ክፍተት አለ፡፡ ይህም ክፍተት ጥያቄውን የሚጠይቁ ሰዎች የተነሡበት ‹ሕፃናት አያውቁም› የሚለው ጭፍን መንደርደሪያ ነው፡፡ እነርሱ ‹ሕጻናት እንደማያውቁ በምን አወቁ? አንድ ሕፃን ስላልተናገረና አሳቡን በቃላት ስላልገለጸ ብቻ አያውቅም ሊባል ይችላል? ፡፡ እንዲህ ካሉ ደግሞ የጌታ እናት እመቤታችን ወደ እርሱ እንደቀረበች አውቆ በስግደት የደስታውን ስሜት ስለገለጸው የስድስት ወር ፅንስ ምን ይላሉ? ሳያውቅ ነው የዘለለው ሊሉን ይሆን? ቢቀበሉ ደግሞ ይህን የመሳሰሉ ድንቅ ማስረጃዎችን ከቅዱሳን አበው ገድላት እናቀርብላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳን የአዋልዱን ይቅርና የአሥራው መጻሕፍቱንም ምስክር ለማመን ስለሚቸገሩ ማስረጃ አናባክንም፡፡
ታዲያ እነዚህን ጥያቄዎች ስንጠይቅ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ሕጻናት ያውቃሉ ወደሚል ሌላ ጽንፍ እያመራን አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነት ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልጅነታቸው ጥምቀተ ክርስትና የተፈጸመላቸው እንዳሉ የሚያሳዩ ልዩ ልዩ የንባብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለአብነትም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተመሳሳይ ምዕራፍ ላይ የምናገኛቸውን ሐር ሸጯ ልድያንና የወኅኒ ቤተ ጠባቂውን ማቅረብ እንችላለን፡፡ መጽሐፉ ሁለቱም ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደተጠመቁ ይናገራል (ሐዋ 16፡15 ፣34)፡፡ ታዲያ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ሕፃናት ሊኖሩ አይችሉምን?
ሌላው በበዓለ ሃምሳ ከተሰጠው የቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ውስጥም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሚናገር ግልጽ ማብራሪያ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ… የተስፋው ቃል (ተጠምቆ መንፈስ ቅዱስን መቀበል) ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ነውና› የሚለው ሲሆን በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ‹ለልጆቻችሁ› የሚለው ቃል ያለ ማብራሪያ ጥምቀት ለሕፃናት እንደሚፈጸም የሚያሳይ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38-39) ጌታችንም በወንጌል ‹ሕፃናትን ተዉአቸው ፤ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው› ሲል የተናገረውን ቃል እንዴት እንረዳዋለን? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር እንዴት ይቀርባሉ? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችሉት በምሥጢራት (Sacraments) ነው፡፡ ታዲያ ከምሥጢረ ጥምቀት የበለጠ ሕፃናት እና አምላክን በአባትና ልጅነት የሚያቀራርብ ምን አለ? ሕጻናት እንዳይጠመቁ ከመከልከል የበለጠስ እነርሱን ከፈጣሪ የማራቅ ሥራ ከየት ሊገኝ ይችላል?፡፡(ማቴ 19፡14)
>>Click here to continue<<