በቤተ ክህነት መዋቅር ውስጥ ሳይቀር ገብተው መጻሕፍቱን የበለጠ እስከመቆንጸል ድረስ ሥልጣን ይዘው የቆዩ ፣ ደመወዝ ከሌላ ቦታ የሚቀበሉ ብዙ ሐሰተኛ ወንድሞችም እንደነበሩና እስካሁንም ድረስ እንዳሉ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ክፍተቶችን ቤተ ክርስቲያንዋ ‘ሆነ ብላ (ምን እንደሚጠቅማት ባይታወቅም እነርሱ እንደሚሉት ክርስቶስን ለመሸፈን ብላ) ያደረገቻቸው ናቸው’ የሚል የሴራ ትንታኔ (conspiracy theory) እየሠጡ ራሳቸውን እውነት ቆፍሮ እንደሚያወጣ ጀግና ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ እንደ ቤተ ጣዖት እየሣሉ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት የጻፏቸውና በነጻ ሳይቀር ሲያድሏቸው የኖሯቸው ንቀትን የተሞሉ መጻሕፍትና በየጓዳው አበል እየከፈሉ የሠጧቸው ሥልጠናዎች ቤተ ክርስቲያንን ቁም ስቅሏን ሲያሳያት መቆየቱ የማይዘነጋ ነው፡፡ ይህም መከረኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በመጻሕፍትዋ ላይ በሰከነ መንገድ የአርትዖት ሥራዎችን በመሥራት ፈንታ ስሙ ማሕሌትዋ ፣ ቅዳሴዋ ፣ ንባብዋና ትርጓሜዋ ፣ ሥጋው ምግብዋና ደሙ መጠጥዋ የሆነውን ክርስቶስን ‘ጨርሶ አታውቂውም’ የሚሏትን ከሳሾችዋን በማስታገሥ ሥራላይ ተጠምዳ እንድትቆይ ግድ ሆኖባት ቆይቶአል፡፡ ‘ሰይጣን አዘገየኝ’ እንዳለ ሐዋርያው፡፡
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሊቃውንትና በመጻሕፍት መምህራን በጥራት እየተሠሩ ያሉ የገድላትንና የድርሳናት ሥራዎች እጅግ ተስፋ ሠጪ ናቸው፡፡ ለዚህም የመጋቤ ምሥጢር ዶ/ር አባ ኅሩይ ኤርምያስን በከፍተኛ ጥራት እየተተረጎሙ ያሉ የገድላትና የድርሳናት ሥራዎችን እንደ ምሳሌ ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ የቅኔና የመጻሕፍት መምህር የሆኑት አባ ኅሩይ ኤርምያስ አስቀድሞ መዝገብ ታሪክ በሚል ስንክሳርን በአጭሩ የሚያስቀምጡ ተከታታይ መጻሕፍትን ያበረከቱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ላይ ይገኛሉ፡፡
በጠቀስነው የገድላትና ተአምራት ሥራ ላይ ገድለ ታዴዎስን ፣ መጽሐፈ ምሥጢርን እጅግ በተደከመበት ጥራት ከምንጩ አመሳክረው ፣ አገባቡን አጥርተው ያሳተሙ ሲሆን ይህን ጽሑፍ በምጽፈበት ጊዜ ያየሁት ‘The Vita of St. Qawstos A Fourteenth-century Ethiopian Saint and Martyr (A New Critical Edition, Translation, and Commentary የተሰኘው በ2021 የታተመ ሥራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ የቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ የራእየ ማርያም Critical review ፣ የሙኃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ‘ኢትዮጵያዊው ሱራፊ’ የገድለ ተክለ ሃይማኖት ጥናታዊ ሥራ ወዘተ ምን ያህል ችግሮችን እንደፈቱ የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሏትን የቅኔ ፣ የመጻሕፍት ፣ የሥነ ጽሑፍ ፣ የሥነ ድርሳናት ፣ የታሪክና የነገረ መለኮት ሊቃውንት አሰባስባ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የማያዳግም በቁጥር የመወሰንና የአርትዖት ሥራ የሚሠራ አካል በሊቃውንት ጉባኤ ሥር ብታቋቁም ማንም ከፊትዋ ሊቆም የማይችል ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
እስከዚያ ድረስ በቅዱስ ጎርጎርዮስ አነጋገር ‘እንደ ዝንብ ሕር እያሉ ቁስልዋን እየፈለጉ’ የሚያደሟትና በእርስዋ ማዋረድ ለመክበርና እንጀራቸውን ለመጋገር የሚጥሩ ፣ ዘመኑን እያዩ አጋጣሚውን ለጥቃት ለመጠቀም የሚሞክሩ ፣ ከወንጌል አገልግሎትዋ ፣ ከማያቋርጥ ማሕሌትዋና ቅዳሴዋ ፣ ከጾምና ጸሎትዋ የሚያናጥቧት መኖራቸው የግድ ነው፡፡ ‘ከሰደበኝ የደገመኝ’ የሚለውን ባለመረዳት ማንም ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተነሣ ባወራ ቁጥር እንዲህ ተባለ እያሉ የገዛ ልጆችዋ ማራገባቸውና ትልቅዋን ቤተ ክርስቲያን በታናናሽ ሚዛኖች ለማስመዘን መሞከራቸውም አንዱ የችግሩ ገጽታ ነው፡፡
ንጉሥ ዳዊት ሳሚ የተባለ ሰው ሲሰድበው ‘ከአብራኬ የወጣ ልጄ እየሰደበኝ እርሱ ቢሰድበኝ ምንም አይደል’ እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ካሳደገቻቸውና ከአፈር ካነሣቻቸው ሰዎችም ብዙ ስድብን ተቀብላለችና ባላሳደገቻቸው ብትሰደብ አይደንቃትም፡፡ የሌሎችን ትንኮሳ እየተከተልን የምናወራና የምንሠራ ከሆነ እንደ ቤተክርስቲያን ተቀባይ /reactors/ እንጂ አንሺዎች /actors/ መሆን አንችልም፡፡ ሆያ ሆዬ ላለ ሁሉ ሆ የምንል ከሆነ አጀንዳ ተቀባይ ሆነን የከበረች ቤተ ክርስቲያናችንን እናስንቃለን፡፡ እንደ ተቋም ሥራችንን መቀጠል ፣ እንደ ክርስቲያን የራሳችን እምነት ማጽናትና ቤተ ክርስቲያን የምትለንን ብቻ መስማት ከሁላችን ይጠበቃል፡፡
በሐዋርያቱ ቃል ልዝጋው ፦
‘ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም ፤ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ’ ‘እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ’ 2ጴጥ. 2፡9 ፣ ይሁዳ 20-24
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 13 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
>>Click here to continue<<