ተአምረ ማርያም ከዋናነት የመጣው ከግብፅ እንደመሆኑ የተተረጎመው ከዐረቢኛ ወደ ግእዝ ነው፡፡ የዐረቢኛው ትርጉም ደግሞ ከላቲን የተተረጎሙ ተአምራትን የሚያካትት ነው፡፡ በተአምረ ማርያም ላይ የተጻፉት ተአምራትም ለምሳሌ የ1525 ቅጂ ላይ ብንመለከት 71 ተአምራት የተፈጸሙት በግብፅ ፣ 60ው በአውሮጳ ፣ 16ቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ፣ 57ቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር) በ2013 ዓ.ም. በጻፉት አንድ ጥናት ላይ ደግሞ በደብረ ዘመዳ ማርያም የተገኘው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጻፈ ብራና 55 በሀገር ውስጥ ብቻ የተፈጸሙ ተአምራትን የያዘ ነው፡፡ (EMML 6835)
ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮጲካም የተአምረ ማርያም ተአምራትን መቼት ሲዘረዝር የሚበዙት ተአምራት የተፈጸሙት በስፔን ፣ ጣሊያን ፣ ፈረንሳይ ፣ ሶርያ ፣ ፍልስጤም ፣ ግብፅ /ቀልሞን (ፋዩም) ፣ ዳይራል አል ሙሃረቅ (ቁስቋም) አል ማግታስ (ደብረ ምጥማቅ)/ መሆኑን ይገልጻል፡፡ [Encyclopedia Ethiopica Vol. 4 789] ከዚህ በተጨማሪ ተአምረ ማርያም ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ተአምራትም በየጊዜው ተጨምረው ተካትተውበታል፡፡
ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ተአምረ ማርያም አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያመጣው መጽሐፍ አይደለም፡፡ በየዘመናቱ ነገሥታቱ አፄ ዳዊት ፣ አፄ በካፋ ፣ አፄ ልብነ ድንግል ፣ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፣ አፄ ቴዎድሮስ (ተአምረ ማርያም ዘቅዱስ መድኃኔ ዓለም መቅደላ ) የተአምረ ማርያምን ነባር ቅጂዎች በማስጻፍና ለትውልድ በማሻገር ፣ አዳዲስ ተአምራትን በማስጨመር ፣ ሥዕላትን በተአምራቱ ላይ በማሣል ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እንዲኖርና እንዲነበብ በማድረግ ክፍለ ዘመናትን በተሻገረው የተአምረ ማርያም ታሪክ ላይ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በተአምራቱ ላይ የሌሎች ቅዱሳን ገድላት ላይ ከድንግል ማርያም ጋር የተገናኙ ታሪኮች ፣ ከነገረ ማርያም የተውጣጡ ታሪኮች ፣ የቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ የደብረ ቁስቋም ድርሳን /Theophilus of Alexandria, Homily on mount Qusquam, Conti Rossni 1912/, ራእየ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ (መጽሐፈ ልደታ ለማርያም) ፣ የአፄ ዳዊት የስናር ዘመቻ ፣ የመጽሐፈ ሐዊ በፓትርያርክ ገብርኤል መተርጎም ፣ በቆጵሮስ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን የተደረገላቸው ተአምር ፣ በኢየሩሳሌም የትንሣኤ ቅዱስ እሳት መውረድ የተደረገለት ኢትዮጵያዊ ታሪክ በኋላ በተአምረ ማርያም የተካተቱ በሌሎች መጻሕፍት የነበሩ ታሪኮች ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ ዝርዝር መረጃ የሚያሳየው ተአምረ ማርያም የድንግል ማርያምን ተአምራት ከመመስከር ባሻገር ምን ያህል ክፍለ ዘመናትን የተሻገረ የመንፈሳዊ ሥነ ጽሑፍ ሀብት እንደሆነና እንደዋዛ ሊታዩ የማይችሉ የኢትዮጵያና የዓለም ታሪክ መረጃዎች የተቀመጡበት እጅግ ውድ መጽሐፍ መሆኑን ነው፡፡
+ በተአምራት ላይ ምን ዓይነት ክፍተት ሊኖር ይችላል? +
ይህ እንዳለ ሆኖ የቅጂዎቹ መብዛት ፣ የተተረጎመበት ቋንቋ ሰንሰለት ርዝመት ፣ ታሪኮቹ የተፈጸሙበት ዘመን መራራቅ ፣ በእጅ ጽሑፍ እየተገለበጠ ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ መሆኑ ፣ ሁሉም ቅጂዎች የሚይዙት ተአምራት ቁጥር ፣ ቅደም ተከተልና የታሪክ ይዘት መለያየቱ ተአምረ ማርያምን ሁሉም ወደተስማማበት አንድ ቅጂ ማምጣት ምን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በዚህ መካከል ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ሲሸጋገር የሚፈጠር የሃሳብ መጥፋት (Loss in translation) ፣ ጸሐፊያኑ በራሳቸው የሥነ ጽሑፍ ስልት ታሪኮቹን ሲተርኩ የሚጨምሯቸው አገላለጾች ፣ በነገሥታት ቤት ያሉ ጸሐፍት ነገሥታቱን ደስ ለማሰኘት በትርጉም ሥራ ላይ የሚጨምሯቸው አንዳንድ አንቀጾች ፣ ሆን ተብሎ ቤተ ክርስቲያንን ለማዋረድና የተአምሩን ክብር ለማቃለል ለተንኮል የሚገቡ ለማጋጨት የሚገቡ ታሪኮች ፣ ከቤተ ክርስቲያንዋ መሠረተ እምነትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚላተሙ በመንደር ማተሚያ ቤት እየታተሙ የሚሰራጩ ታሪኮች በተአምረ ማርያም ላይ ለሚሠራው የሊቃውንት የአርትዖት ሥራ እጅግ ትልቁ እንቅፋት ሆኖ ቆይቶአል፡፡
በተአምራትና ገድላት ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ ችግሮች መካከል የታወቁትን በምሳሌነት ላንሣ፡፡ የመጀመሪያው የታሪክ ተፋልሶ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አባት ኖረ የሚባልበት ዘመንና በታሪኩ ውስጥ የሚገኙ ክስተቶች ላይገጥሙ ይችላሉ፡፡ ወይንም አንድን አባት እገሌ ሾመው ተብሎ ይነገርና በሿሚና ተሿሚው መካከል የብዙ መቶ ዓመታት ልዩነት ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህም ሆን ተብሎ የሚደረግ ነገር ሳይሆን መጽሐፉ በእጅ ጽሑፍ ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የሚፈጠር የነገረ ገድል /hagiography/ አጥኚዎች ሁሉ የሚስማሙበት የተለመደ እንከን /Common error/ ነው፡፡
ወዳጄ የዛሬ መቶና ሃምሳ ዓመታት በተፈጸሙ ታሪኮች ላይ መስማማት አቅቶን እርስ በእርስ እየተጋደልን ባለንበት ሁኔታ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ በሆናቸው ታሪኮች ላይ ክፍተት ሲገኝ ‘ምን ሲደረግ?’ ብሎ መንገብገብ እንዴት ተገቢ ሊሆን ይችላል? በአንዳንድ ተአምራት ላይ ደግሞ ስለ አንድ አባት የልጅነት ታሪክ የሚተረከው ትርክት የሌላ አባት ሆኖ ሊገኝ ይችላል ፣ ወይንም ስለ አንድ አባት መጠሪያ ስም አሰያየም በእኛ ዘንድ ያለው ታሪክና ያ አባት በተወለደበት ሀገር የሚተረከው ታሪክ የተለያየ ገጽታ ሊኖረው ይችላል፡፡
ይህም እንደላይኛው ሆን ተብሎ የሚፈጠር ነገር አይደለም፡፡ ከሀገር ሀገር ከክፍለ ዘመን ወደ ሌላ መቶ ክፍለ ዘመን ይቅርና አሁን ባለንበት በዚህ 2015 ዓ.ም. ላይ ስላበቃው ጦርነት እንኳን በሀገራችን ከሰሜን እስከ ደቡብ የምንተርከው ትረካ /Side of the story/ ተመሳሳይ አይደለም፡፡
አባቶቻችን ትሑታን አንባቢዎች ስለነበሩ ያገኙትን መረጃ ጽፈው ለዚህ ትውልድ ሲያስተላልፉ ‘እኛ ዘንድ የደረሰው ይህ ብቻ ነው’ ከሚል ትሕትና ጋር ነው፡፡ ለምሳሌ የመጽሐፈ ቅዳሴ ትርጓሜ ስለ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ታሪክ ሲተርክ ‘ታሪኩ በእኛ ዘንድ የለም ፤ አቶ እገሌ ግን ሶርያ ወርደው ታሪኩን ይዘውልን መጥተዋል’ ብሎ እስከመጥቀስ የሚደርስ ትሕትና የሚታይበት አጻጻፍ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ የታሪክ ተፋልሶዎች ብዙ ከማንበብና ከማመሳከር የሚከሰቱ የቀለም ሠረገላ መደናቀፎች እንጂ የንዝህላልነት አይደሉም፡፡
በተአምራት ላይ ሆን ብለው የሚያፋጅ መልእክት ያለው ሃሳብ የሚጽፉ ቀሳጢዎችም አልጠፉም፡፡ በአንድ የተአምር ቅጂ ላይ ‘የተስፋይቱ ምድር አሜሪካ’ እንደሆነች ተደርጎ በቅንፍ ገብቶ ተጽፎ አንብቤ ነበር፡፡ ዓይኔን ለማመን ተቸግሬ ግእዙን ዞሬ ስመለከተው ግን ጨርሶ እንደዚያ የሚል ቃል የለበትም፡፡ ይህን የሚያደርገው ሰውዬ እንግዲህ የአሜሪካ ፍቅርና የቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ያለበት ነው፡፡ ከዚህም የከፉ ለማንበብ የሚያስጸይፉ ጨርሶ ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸውና የማታምናቸው ታሪኮች በቤተ ክርስቲያኒቱ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ባልተማሩ ደፋር ጸሐፍት ተጽፈው በገድል ስም ታትመው ወጥተዋል፡፡
>>Click here to continue<<