††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† መስከረም 28 †††
††† ቅዱሳን አባዲርና እህቱ ኢራኢ †††
††† በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ: ገላውዴዎስ: ፊቅጦር: መቃርስ: አባዲር: ቴዎድሮስ (ሦስቱም): አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ::
ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ:- ማርታ: ሶፍያ: ኢራኢ: ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ / ሞተ::
የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ::
በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪዻዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪዻዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው::
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች::
ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ:- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ::
ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ቅዱሳኑ አባዲርና ኢራኢም ከእነዚህ መካከል በመሆናቸው ተጋድሏቸውን ቀጠሉ:: በተለይ ቅዱስ አባዲር በሌሊት በመካነ ጸሎቱ ሲጸልይ ያድርና በቀን ነዳያንን ይጐበኛል::
አመሻሽ ላይ ደግሞ ልብሱን ለውጦ ወደ እሥር ቤት ይሔዳል:: እሱ የአንጾኪያ ሠራዊት አለቃ: ኃያል የጦር መሪ ነውና ሁሉ ይወደውና ያከብረው ነበር:: በዚህም ምክንያት የእሥር ቤት ዘበኞች ምንም ከዲዮቅልጢያኖስ ከባድ ትዕዛዝ ቢኖርባቸውም ለቅዱሱ ግን ይከፍቱለት ነበር::
እርሱም ወደ እሥር ቤት ገብቶ ቁስላቸውን ጠርጐ: እግራቸውን አጥቦ: ለረሃባቸው መደገፊያ የሚሆን ማዕድም አጉርሷቸው ይወጣ ነበር:: በእንዲህ ያለ ግብር ሳለ ስለ ክርስቶስ የሚሰዋበት ጊዜ ደረሰ::
አንድ ቀን በመካነ ጸሎቱ ለምስጋና ሲተጋ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት:: "ስምህን ለዘለዓለም አከብረዋለሁ:: በሰማያዊት ርስቴም አነግሥሃለሁና ከእህትህ ኢራኢ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳችሁ መስክሩ" ብሎት: ለእሷም በተመሳሳይ "ወንድምሽ የሚያዝሽን ሥሪ" ብሏት መድኃኒታችን ዐረገ::
ከዚያች ቀን ጀምሮ ቅዱስ አባዲርና እህቱ ኢራኢ ወደ ግብጽ የሚወርዱበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር:: እናታቸው ግን (የቅዱስ ፋሲለደስ እህት ናት) ነገሩን ስትሰማ አለቀሰችባቸው:: "ልጆቼ አትሙቱብኝ: ዲዮቅልጢያኖስንም አትናገሩት" ስትል አማለቻቸው::
ከጥቂት ቀናት በኋላም ቅዱሱ ከእህቱ ጋር ከሶርያ ጠፍቶ ግብጽ ገቡ:: በዚያ ግን ፈተና ገጠመው:: በየመንገዱ የሚያየው ሕዝቡና ሠራዊት ሁሉ "ጌታችን አባዲር" እያለ ይሰግድለት ገባ:: ቀደም ሲል እንዳልነው እርሱ ኃያል የጦር መሪ: የሠራዊቱም አለቃ ነውና::
ቅዱሱ ግን ወደ ክርስቶስ ሊሔድ ናፍቋልና ሠራዊቱን እና ሕዝቡን:- "የሚገርማችሁ ሁሉም ሰው እንዲህ ይለኛል:: ግን'ኮ እኔ አንድ ተራ ምስኪን ክርስቲያን እንጂ የምትሉት ሰው አይደለሁም" ብሎ አታለላቸው::
ቀጥሎ በክርስትናው ተከሶ ከእህቱ ጋር ለፍርድ ቀረበና ስቃይ ታዘዘባቸው:: ለሰው ዐይን የሚከብዱ ብዙ ስቃዮችን ካሳለፉ በኋላም ሞት ተፈረደባቸው:: ነገር ግን አንገታቸው ከመሰየፉ በፊት መኮንኑ አርያኖስ ትክ ብሎ ሲያየው ተጠራጥሮ "ማንነትህን እንድትነግረኝ በአምላክህ አምየሃለሁ" አለው::
ቅዱስ አባዲርም መልሶ "አንተም ማንነቴን ካወቅክ በኋላ እኔን መግደል እንዳትተው ማልልኝ" አለው:: ማለለትም "እኔ አባዲር ነኝ" አለው:: በዚያች ቅጽበት አርያኖስ ከመደንገጡ የተነሳ መሬት ጠበበችው:: በፊቱ ተደፍቶ "ወዮልኝ! ጌታየን አባዲርን ያሰቃየሁ" እያለ አለቀሰ:: ነገር ግን ምሏልና በ300 ዓ/ም አካባቢ እያዘነ በዚህች ቀን ቅዱስ አባዲርንና እህቱን ኢራኢን አሰይፏቸዋል::
††† ቅድስት ሶስና †††
††† ይህች እናት የነበረችው ቅ.ል.ክርስቶስ በ500 ዓመት አካባቢ ነው:: እሥራኤላውያን በናቡከደነጾር ተማርከው ፋርስ ባቢሎን ወርደው ሳሉ: የኬልቅዩስ ልጅ: የደጉ ኢዮአቄም ሚስት የሆነች እናት ናት::
ቅድስት ሶስና በስደት ሃገር እግዚአብሔርን የምታመልክ: ለባሏ የምትታመን: ለቤተሰቦቿም ኩራት የሆነች ወጣት: በዚያውም ላይ እጅግ የምታምር ነበረች:: በዘመኑ ሕግን እናውቃለን የሚሉ 2 ረበናት ግን ከቅድስናዋ ሊያጐድሏት ይሹ ነበርና: አልሳካላችሁ ቢላቸው በሃሰት ከሰው በወገኖቿ ፊት ሞትን አስፈረዱባት::
በፍርድ ፊት ቁማ ሳለ እርሷ በፍጹም እንባ ወደ ፈጣሪዋ ትጸልይ ነበርና እግዚአብሔር ፍርዱን ላከ:: ሊገድሏት ሲወስዷት የኋላው ነቢዩ ቅዱስ ዳንኤል ያን ጊዜ ብላቴና ነበርና "እኔ ከዚህች የተባረከች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ" ሲል ጮኸ::
ይህንን የሰሙ ዳኞችም የፍርድ ዙፋኑን ለቀቁለት:: ሁለቱን ረበናት ለየብቻቸው አድርጐ ዝሙትን ስትሠራ በየት ቦታ ላይ እንዳዩዋት ጠየቃቸው:: ጌታ ሲፈርድባቸው አንዱ በኮክ: ሌላኛው በሮማን ዛፍ ሥር አለ:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እነዚህን ሃሰተኛ ረበናት (መምሕራን) ስለ እርሷ ፈንታ ወግረው ገደሏቸው:: ቅድስት ሶስና ግን ባለ ዘመኗ ሁሉ ፈጣሪዋን አገልግላ በዚህች ቀን ዐርፋለች::
††† አምላከ ቅዱሳን ከክፉ ሰዎች ምክር: ከአጋንንትም ሴራ በቸርነቱ ይጠብቀን:: የወዳጆቹንም ጸጋ ክብራቸውን ያድለን::
††† መስከረም 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባዲር ሰማዕት
2.ቅድስት ኢራኢ እህቱ
3.ቅድስት ሶስና እናታችን
4.ቅዱስ ሉቃስ መነኮስ
5.ቅዱስ ዻውፍርና
††† "ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች:- 'ዘላለም ጸንተህ የምትኖር: የተሠወረውን የምታውቅ: የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ! በሐሰት እንደ ጣሉኝ አንተታውቃለህ:: እነዚህ መመሕራንም ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ: የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ' አለች:: እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማት::" †††
(ሶስና. ፩፥፵፩)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
>>Click here to continue<<