ሉሲፈር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
4፥171 *እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፥ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ*፡፡ يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لَا تَغْلُوا فِي دِينِكُمْ وَلَا تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ إِلَّا الْحَقَّ
"ፎስፎረስ" Φωσφόρος የሚለው የግሪክ ቃል እና "ሉሲፈር" የሚለው የላቲን ቃል ትርጉሙ "አጥቢያ ኮከብ" ወይም "የንጋት ኮከብ"morning star" ማለት ሲሆን ቬኑስ ለተባለው ፕላኔት ስም ነው። "አጥቢያ ኮከብ" ወይም "የንጋት ኮከብ" የሚለው ይህ የማዕረግ ስም ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ውሏል፦
ኢሳይያስ 14፥12 *"አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ"*!
አይሁዳውያን በሙሉ ይህንን ጥቅስ የሚናገረው ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር ነው ሲሉ፥ ዐበይት ክርስቲያኖች ስለ ዲያብሎስ ነው ይላሉ። ዐውደ-ንባቡ ላይ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን የሚል ፍንጭ የለም። ከዚያ በተቃራኒ ስለ ባቢሎን ንጉሥ እና ስለ ሰው ነው የሚናገረው፦
ኢሳይያስ 14፥4 ይህንም ምሳሌ *በባቢሎን ንጉሥ ላይ"* ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ፦ አስጨናቂ እንዴት ዐረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ!
ኢሳይያስ 14፥17 ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ ምርከኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ *ሰው* ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል።
ሙሉ ባይብል ላይ ዲያቢሎስ የባቢሎን ንጉሥ እና ሰው ነው የሚል ምንም አይነት ሽታው የለም። እዚህ ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው "እንዴት ከሰማይ ወደቅህ" የሚለው ኃይለ-ቃል ብቻ ነው። "ሰማይ" ንግሥናን ለማመልከት፥ ከሰማይ መውደቅ ከንግሥና መውረድን ለማመልከት እንጂ የባቢሎን ንጉሥ ቃል በቃል ከመንፈሳዊ ዓለም መውደቁን አያመለክትም፦
ሰቆ ኤርምያስ 2፥1 አሌፍ። ጌታ በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደ ምን አደመናት! *"የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ"*፥ በቍጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም።
የእስራኤልን ውበት የእስራኤል የመጨረሻው ንጉሥ ሴዴቂያስ ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ ማለት ከንግሥናው መውረድን ካመለከተ ሰውና የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከሰማይ ወደቀ ማለት እራሱን ከፍ ከፍ አድርጎ መዋረዱን የሚያሳይ ነው፦
ዳንኤል 4፥11 ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ *"ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ"*፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ።
ዳንኤል 4፥22 *"ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፥ እስከ ሰማይም ደርሶአል"*፥ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው።
ሲቀጥል "አጥቢያ ኮከብ" "የንጋት ኮከብ"morning star" ማለት አሉታዊ ማዕረግ ከሆነ መላእክት ሆነ ኢየሱስ አጥቢያ ኮከብ ተብለዋል፦
ኢዮብ 38፥7 *"አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ"*፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?
ራእይ 22፥16 እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ *"የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ"*።
አጥቢያ ኮከብ ዕውቀትን ለማመልከትም ጥቅም ላይ ውሏል፦
ራእይ 2፥26 ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ *"የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ*።
2 ጴጥሮስ 1፥19 ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ *"የንጋትም ኮከብ"* በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።
የንጋት ኮከብ የሚለው ለዲያቢሎስ የዋለበት ጥቅስ ባይብል ላይ የለም። ይህ ሆኖ ሳለ ጽዮናዊነትን የሚያራምደው ወሊድ ሹዒባት፦ “ኢሳይያስ ላይ ያለው አጥቢ ኮከብ አላህ ነው፥ በመሥጂድ ማማ ላይ የሚደረገው ለዛ ነው” የሚል የራሱን ዝንባሌ በመከተል የሚተረጉምበት አተረጓጎም አለው። ይህ ትርጓሜ ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለታሪክ እንግዳ ትርጓሜ ነው። ከዝንብ ማር አይጠበቅም፥ "ጠላት ይቀባል ጥላት" ይባል የለ? ግን የተሸወደው ኢሳይያስ ላይ ስለ ዲያቢሎስ ሳይሆን ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር እንደሚናገር አለማጠኑ ነው።
ሲቀጥል ጨረቃ እና ኮከብ ምልክት መሆን የተጀመረው መስቀለኞች ክርስቲያን መስቀልን አርማ አድርገው ዓለምን ከወረሩ በኃላ ነው፥ መስቀለኞች ዓለምን ለመውረር የመስቀል ጦርነት ያደረጉት ዘጠኝ ጊዜ ነው። መስቀል ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ጣዖታውን ለጣዖታቸው ምልክት ይጠቀሙበት ነበር፥ የግሪክ ባከስ፣ የጢሮስ ተሙዝ፣ የባቢሎናውያን ቤል፣ የኖርስ ኦዲን፣ የግብጻውያን አንክ ምልክታቸው መስቀል ነው። ለምሳሌ የግብፅ ሥላሴ ኦስሪስ፣ አይሲስ እና ሆረስ አርማቸው "አንክ" የተባለው መስቀል ነው። በኃላ ላይ የአዲስ ኪዳን እደ-ክታባት"manuscripts" ደንገል 66፣ ደንገል 45 እና 75 ልባስ ላይ ይህ አንክ የተባለው መስቀል ምልክት ተደርጓል። ዋቢ ምንጭ ይመልከቱ፦
የብሪታኒካ መድብለ-ዕውቀት(ኢንሳይክሎፔድያ) (1946)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 753
ጨረቃ እና ኮከብ በ 1299 ድኅረ-ልደት ዑስማን ጋዚ የቱርክ ኢምፓየር ከተመሠረተ በኃላ ከመስቀለኞች ለመለየት አርማ ተደርጎ መጠቀም ተጀመረ። በመቀጠል በሦስተኛው ሙስጠፋ በ1757 ድኅረ-ልደት የአገር ባንዲራ እና በመሥጂድ ማማ ላይ ጨረቃ እና ኮከብ ተደርጎ መጠቀም ተጀመረ። በቁርኣን ሆነ በሐዲስ "ጨረቃ እና ኮከብ የኢሥላም አርማ ነው" የሚል ሽታው እንኳን የለም። ቀደምት ሠለፎች የሆኑት ሦስቱ ትውልዶችም ጨረቃ እና ኮከብ ለምልክትነት ተጠቅመው አያውቁም። ጨረቃ እና የንጋት ኮከብ ፀሐይ አምላካችን አላህ ለሰው ልጆች የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን መቁጠሪያ ያደረጋቸው ፍጡራን ብቻ ናቸው፦
6፥96 እርሱም ጎህን ከሌሊት ጨለማ ፈልቃቂ ሌሊትንም ማረፊያ *”ፀሐይንና ጨረቃንም ለጊዜ መቁጠሪያ አድራጊ ነው”*፡፡ فَالِقُ الْإِصْبَاحِ وَجَعَلَ اللَّيْلَ سَكَنًا وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ حُسْبَانًا ۚ ذَٰلِكَ تَقْدِيرُ الْعَزِيزِ الْعَلِيمِ
10፥5 *እርሱ ያ ፀሐይን አንጻባራቂ ጨረቃንም አብሪ ያደረገ ነው፡፡ የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን ታውቁ ዘንድም ለእርሱ መስፈሪያዎችን የለካ ነው፡፡ አላህ ይህንን በእውነት እንጂ በከንቱ አልፈጠረውም"*፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦች አንቀጾችን ያብራራል፡፡ هُوَ الَّذِي جَعَلَ الشَّمْسَ ضِيَاءً وَالْقَمَرَ نُورًا وَقَدَّرَهُ مَنَازِلَ لِتَعْلَمُوا عَدَدَ السِّنِينَ وَالْحِسَابَ ۚ مَا خَلَقَ اللَّهُ ذَٰلِكَ إِلَّا بِالْحَقِّ ۚ يُفَصِّلُ الْآيَاتِ لِقَوْمٍ يَعْلَمُونَ
>>Click here to continue<<