TG Telegram Group & Channel
Nolawi ኖላዊ | United States America (US)
Create: Update:

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (12)

9- ሰላምታ ስጥ

ሰላምታ የግንኙነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ። ሰላምታ የወዳጅነት ፣ የናፍቆት ፣ የስብሰባ ፣ የስብከት ፣ የደብዳቤ ፣ የአዋጅ ፣ የቃለ ምዕዳን መክፈቻ ነው ። ሰላምታ የተቋማት መግለጫ ነው። ካህን ፣ ወታደር ፣ እስካውት ፣ ስፖርተኛ ፣ ሙስሊም ፣ ክርስቲያን በሰላምታ ይለያል ። ሰላምታ እንስሳት እንኳ ሲገናኙ በቋንቋቸው የሚገልጡት የፍቅር ንባብ ነው ። ሰዎች እንስሳትን ፣ እንስሳት ሰዎችን በሰላምታ ይቀበላሉ ። ሰላምታ ለሚያውቁት ሰው ብቻ ሳይሆን ለማያውቁት ሰውም የሚሰጥ ስጦታ ነው ። ሰላምታ በሃይማኖት ዓለም አምልኮ ነው ። በሰላምታ የሚመሰገነው እግዚአብሔር ነውና ። ሰላምታ በሰላም የመምጣታችን ማስገንዘቢያ ነው ። ሰላምታ ካልሰጠን ሰዎች በክፉ እንደመጣን ገምተው በክፉ ይዘጋጃሉ ። ሰላምታ የሰውን ልብ የምናስከፍትበት የመጀመሪያው የደወል ድምፅ ነው ። አንድ ሙሉ ሰው ሰላምታ ማቅረብ የሚችል ሰው መሆን አለበት ። ልጆችን ገና በጠዋቱ ሰላምታ መስጠትን ማለማመድ አለብን ። “ሰላምታ ስጡ” ስለሚባል ሰላምታ ስጦታ ነው። ሁሉም ሰው መስጠት የሚችለው ስጦታ ነው ።

የአንዳንድ ሰዎች ሰላምታ በጣም ይማርካል ። “ምነው ሰላም ባሉኝ!” በማለት ሰው ሁሉ ይጓጓል ። ሰላምታ ሰውነትና መንፈሳዊነት ባላቸው ትውልዶች የተከበረ ዕንቈ ነው ። ገንዘብን እንጂ ፍቅርን ለማይፈልግ ሆድ አደር ትውልድ ግን ሰላምታ ጊዜ ማጥፊያ ነው ። በአገራችን እስከ ቅርብ ዓመታት በመንገድ የተገናኘ ሰው ሰላምታ ይለዋወጣል ። ከየት እንደ መጣ ፣ ወዴት እንደሚሄድ አውርቶ የአቅሙን ያህል ድጋፍ ያደርጋል ። አሁንም በገጠሩ ሰውና ሰው ሲገናኝ ሰላምታ ይሰጣጣል ። “ከብት እንኳ ሲገናኝ እምቧ ይባባል ።” ሰው ሰውን ሲያገኝ ሰላም ሊል ይገባዋል ። በየመንገዱ ቆም ብለን የምንለዋወጠው ሰላምታ የራሳችንን ዋጋ የሚጨምር ፣ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። ደግሞም መነጋገር ትልቁ የአእምሮ ጭንቀት ማስተንፈሻ ነው ። ከንግግር ውስጥ ብልሃት ይገኛል ። በአገራችን አንዱ የአንዱ የሥነ ልቡናው አካሚ ሆኖ ኖሯል ። ብዙ ችግር ቢኖርም ጭንቀት እንዳይኖር ብዙ ማስተንፈሻዎች ነበሩ ። ልቅሶውን ፣ ኀዘኑን ፣ ጭንቀቱን የምናስተናግድበት የዜማ መንገዶች ፣ የግጥም ድርድሮች አሉን ። በመድኃኒት ከሚገኝ ፈውስ በእርስ በርስ ፍቅር የሚገኝ ፈውስ ትልቅ ዋጋ ያለው ነው ።

የሰላምታ ባለጠጋ መሆን አለብህ ። ጌታ በትእዛዝ ቃሉ፡- “ሰላምታ ስጡ” ብሏል ። (ማቴ. 10 ፡ 13 ።) ወደ ቤት ስትገባ ፣ ወደ ሥራህ ስትሰማራ ፣ ስብሰባ ስትከፍት ሰላምታ መስጠት አለብህ ። ሰላምታህ ለቀጣይ ጉዳይ በር ከፋች ነው ። በሩ ካልተከፈተ ማለፍ እንደማይቻል ሰላምታህ ውጤታማ ካልሆነ ምንም መስጠትና መቀበል አትችልም ። ሰላምታህን ከሚጎዱ ነገሮች ውስጥ ጥቂቱን እንይ ። ጨፍጋጋና ኮስታራ ፣ ቍጠኛ ፊት ሰላምታን ይጎዳል ። ፈገግ ማለት የራስህንም ቆዳ ማፍታታት ነው ። ደግሞም እውነተኛ ፈገግታ ከፀሐይ ብርሃን ይልቅ ያምራል ። ኑሮ የጨለመባቸው ባንተ እውነተኛ ፈገግታ ሊበራላቸው ይችላል ። “ለካ ዛሬም ፈገግታና ሳቅ አለ” እንዲሉ ያደርጋቸዋል ። ስለ ተኮሳተርህ አትከበርም ፣ ፈገግ ስላልህ አትናቅም ። የክብር መገኛው ወይ ፍቅር ወይ ፍርሃት ነው ። ፍርሃት የሚያመጣው ክብር ሰዎችን እንዲሸሹህ ያደርጋል ። የፍቅር አክብሮት ግን እንደ ማለዳ ፀሐይ ብርሃኑን እየጨመረ እንደሚሄድ ነው ።

ሰላምታህን የሚጎዳው ኩራት ያለበት ድምፀትህ ነው ። ከመሬት ተነሥቶ ልጥጥ የሚል ሰው አትሁን ። ቃላትህንም እያስረዘምህና እየበጣጠስህ ከአፍህ አታውጣ ። ወንበር ሠርተህ ካልነገሥሁ አትበል ። ትዕቢት ራስን በቅጡ ያለማወቅ ውጤት ነው ። ደግሞም የባዶነት ማሳያ ነው ። ዓለት ጉብ ብሎ ፣ ከብዶ የሚኖር ነው ። ሲፈረከስና ራሱን ሲያሳንስ ግን ቤት መሥሪያ ፣ መንገድ ማውጫ የሚሆን ነው ። ጠቃሚ የምትሆነው በትሕትና ብቻ ነው ። የገዛ ክንፏ የከበዳት ወፍ መብረር አትችልም ። ትዕቢትም ራስን ማክበድ ፣ የራስን ሬሳ መሸከም ነው ። ። ሰላምታን የሚጎዳው ሌላው የምትመርጣቸው ቃላት ናቸው ። ሰዓቶችን ለይ ። ማታ ላይ እንዴት አደራችሁ? አይባልም ። ሰላምታ ስትሰጥ ከቀልብህ መሆን አለብህ ። ደግሞም የሰዎችን መዐረግ ማወቅና በመዐረጋቸው መሠረት መጥራት አለብህ ። ሰላምታህ በሚያግባባችሁ ነገሮች ብቻ የታጀበ መሆን አለበት ። ገና ከበር ጠብ የሚጀምር ባለጌ ነው ። ቅሬታ ሰላምታህን ይጎዳዋልና አስቀድመህ መፍታት አለብህ ።

ሰላምታ አልችልም አይባልም ። በሕይወት ውስጥ ትንሹና ቀላሉ ነገር እርሱ ነውና ። ምናልባት ተፋትተው ይሆናልና በሰላምታህ ዳር ዳሩን በል እንጂ ወደ ትዳሩ አትግባ ። ምናልባት ሞቶበት ይሆናልና “እገሌስ?” ብለህ ስትጠይቅ ጠንቃቃ ሁን ። ምናልባት ከፍቶት ይሆናልና በቀልድ አትጀምር ። ሰላምታህ ግን ያንን ሰው ነጻነት የሚሰጠው መሆን አለበት ። ይልቁንም ወደ ቤትህ የመጣው ሰው ለመቆየትም ላለመቆየትም የሚወስነው በሰላምታህ መጠን ነው ። አንተ በዚህ ምድር ላይ ቤት የለህምና በቤትህ እንግዳ የሆንከው አንተ ሆይ ! እንግዳ ተቀበል ።

ሰላምታህ አባት የሆነ እንደሁ ጉልበትና እጁን መሳም ያስፈልግሃል ። ፓትርያርክ እንደሆነ ብፁዕ አባታችን አይባልም ። ቅዱስ አባታችን ወይም ብፁዕ ወቅዱስ እያልህ ሰላምታህን አቅርብ ። ጳጳስ የሆነ እንደሁ ብፁዕ አባታችን ብለህ ጥራ ። የሲኖዶስ አባላት ፊት ስትቆም ቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብለህ በየመዐርጉ ሰላምታ አቅርብ ። መሳይና ወዳጅህን ስታገኝ እንደ ቅርበትህ በእጅህ ጨብጥ ። እንደ ቅርበትህ መሳሳምን አትርሳ ። ይሁዳ ጌታን ስሞታል ። በእውነት ቢሆን መልካም ነበረ ። በእውነት መሳም የፍቅር መግለጫ ነው ። ሕፃናት ከሆኑም የምታውቀውን ሕፃን ስትስም የማታውቃቸውንም ሕፃናት አብረህ ሳም ። ስታዋራቸውም በርከክ ብለህ ፊት ለፊት እያየህ አዋራቸው ። አንድ ቀን አድገው “ያን ጊዜ ሕፃን ሳለን ታከብረን ነበር” ብለው ሊያመሰግኑህ ይመጣሉ ። የሰው ሚስትና እጮኛን በጣም ሰላም ማለትና መቀራረብን ተዉ ። ባልዋ በሌለበትም የሰው ቤት አትሂድ ። ወደ ባል ስትደውል “ሚስትህን ሰላም በልልኝ” በል ። ማንንም ሰው ስታገኝ አንገትህን ዘንበል አድርገህ ሰላም በል ። ሰው ልዑል ፣ የንጉሥ ልጅ ነውና ። ማክበር መከበር ነው ። ክብርህን ግዛው እንጂ አትሽጠው ። ባለጌንም ከወዳጅህ ጋር አታስተዋውቅ ። ምንም ቢከፋህ የልብህን ችግር በፊትህ አደባባይ ላይ አታስነብብ ። እዚህ ላይ ላቆም እንዳላደክምህ !

ሰላም ይብዛልህ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም.

>>Click here to continue<<

Nolawi ኖላዊ

Share with your best friend
VIEW MORE

United States America Popular Telegram Group (US)