🕊
[ † እንኳን ለተባረከ ወር ሐምሌ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
† እግዚአብሔርን ቸር የምንለው በባሕርዩ ፍጹም ቸር በመሆኑ ነው:: ይሕንን ደግሞ ለማረጋገጥ መቅመስ ይቻላል:: ይገባልም:: [መዝ.፴፫፥፯] ይሔው ደግሞ ያን ሁሉ ኃጢአታችንን ታግሶ ከወርኀ ሐምሌ አደረሰን:: ለዚሕ ቸርነቱ አምልኮ : ውዳሴና ስግደት ይገባዋል::
ለወርኀ ነሐሴ ደግሞ እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::
🕊 † ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ † 🕊
† ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት ቅዱስ አግናጥዮስ ገና በልጅነቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ : ራሱ ጌታችን ትንቢት የተናገረለት [ማቴ.፲፰፥፩] እና ከጌታ ዕርገት በኋላ ሐዋርያትን የተከተለ አባት ነው:: ጌታ ሲያርግ የአምስት ዓመት ሕፃን ሲሆን ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ሐዋርያትንና ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል::
ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ሲደርስ [ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት - በ፸ ዓ/ም] እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል:: አስቀድሞ ከወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እግር ምሥጢርና ፍቅርን ጠጥቷልና የተለየ ሰው ነበር:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከአንጾኪያ እየተነሳ ምድረ እስያንም በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሷል::
በአካል ያልደረሰባቸውን በጦማር [በክታብ] አስተምሯል:: በአካሉ እንኳ ምንም በጾም በጸሎትና በብዙ ድካም የተቀጠቀጠ ቢሆን ግርማው የሚያስፈራ ነበር:: ከነገር ሁሉ በኋላ የወቅቱ ቄሣር ጠራብሎስ ይዞ አሰቃይቶ ለአንበሳ አስበልቶታል:: በዚህ ምክንያት "ምጥው ለአንበሳ-ለአንበሳ የተሰጠ" እየተባለ ይጠራል::
🕊 † አባ ብዮክ እና አባ ብንያሚን † 🕊
† እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ናቸው:: ካህን አባታቸው በሚገባ ቢያሳድጋቸው እነሱም ገና በወጣትነት የሚደነቅ የክህነት አገልግሎትን ሰጥተዋል:: ሙሉ ሌሊት ለጸሎት : ሲነጋ ለኪዳን : በሠርክ ደግሞ ለቅዳሴ ይፋጠኑ ነበር:: ሁሌም በየቤቱ እየዞሩ የደከመውን ሲያበረቱ : የታመመውን ሲፈውሱ : ያዘነውን ሲያጽናኑ ውለው ትንሽ ቂጣ ለራት ይመገባሉ::
ሰውነታቸው በፍቅር ሽቱ የታሸ ነበርና ብዙዎችን መለወጥ ቻሉ:: አንዴ ቅዳሴ ሊገቡ ሲሉ "አባታችሁ ሊሞት ነው" ቢሏቸው "ሰማያዊው አባት ይቀድማል" ብለው ቀድሰዋል:: አባታቸውንም ቀብረውታል:: በመጨረሻ ግን አንድ ቀን ለመስዋዕት ብለው ያዘጋጁትን የበረከት ሕብስት እባብ በልቶባቸው አገኙ:: እንደ ምንም ፈልገው እባቡን ገደሉት::
ነገር ግን ያ የተባረከ ሕብስት በሆዱ ውስጥ ነበርና ምን ያድርጉት? ጌታን ስለ ማክበር ሊበሉት ፈልገው ጌታን ቢጠይቁት መልአኩ መጥቶ "ሰማዕትነት ሆኖ ይቆጠርላቹሃል" አላቸው:: ሁለቱ ወንድማማቾች ብዮክና ብንያሚን ፈጣሪያቸውን አመስግነው በሉት:: ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሁለቱንም እንደተቃቀፉ ዐርፈው አገኟቸው:: መልካም እረኞቻቸው ናቸውና ከታላቅ ለቅሶ ጋር ቀብረዋቸዋል::
🕊 † ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ወጻድቅት † 🕊
† ይህቺ ቅድስት እናታችን ደግሞ ገና በአሥራ ሁለት ዓመቷ ታላቅ እህቷን ተከትላ ገዳም ትገባለች:: በሚገርም ተጋድሎ በጥቂት ጊዜ አጋንንትን አሳፍራ መነኮሳይያትንም አስገርማቸዋለች:: ትጋቷ ግሩም ነበርና ስትታዘዝ : ስትጸልይና ስትሰግድ ያለ እንቅልፍና ምግብ ቀናት ያልፉ ነበር:: በዚህ የተቆጣ ሰይጣን አረማዊ መኮንንን ይዞባት መጣ::
ሌሎች ደናግል ሲያመልጡ እርሷ ለመከራ ተዘጋጅታ ጠበቀችው:: አዕምሮ የጎደለው መኮንኑም ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ ጽኑዕ ጽኑዕ መከራን አመጣባት:: በተጋድሎ ባለቀ አካሏ ሁሉንም ቻለች:: በዚህች ቀን ግን አንገቷን በሰይፍ አስቆርጧታል::
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ትዕግስትና ጽናት ለእኛም ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
🕊 † ቅዱስ ቶማስ † 🕊
ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ" ብሎ መከራቸው::
ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::
እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ [መግደሉ] ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች::
ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ::
የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል የገደልኩሽ እኔ:: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው:: እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች:: ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::
††† ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::
🕊
[ † ሐምሌ ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሰማዕት
፪. አበው ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
፫. ቅድስት ቅፍሮንያ [ ሰማዕት ወጻድቅት ]
፬. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፭. አቡነ ገብረ መድኅን ጻድቅ
፮. አባ ክልዮስ ዘሮሜ
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፬. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭. ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
† " በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው "በመንግስተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?" አሉት:: ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ:: እንዲህም አለ :- "እውነት እላቹሃለሁ:: ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ከቶ አትገቡም:: እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግስተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው::" † [ማቴ. ፲፰፥፩]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
>>Click here to continue<<