አምስቱ የማሕበራዊ ሚዲያ ሃሳብ (Comment) ሰጪነት መርሆች
በማሕበራዊ ገጾች ያለንን ተሳትፎ የመልካም ተጽእኖ ምንጭ ማድረግ ከፈለግን እነዚህ አምስት ሕጎች ይጠቅሙናል፡፡
1. የምትሰጡት ሃሳብ (Comment) አሉታዊ ከሚሆን ይልቅ አዎንታዊ ቢሆን ይመረጣል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ አሉታዊ-ተኮር የሆኑ ሃሳቦችን ለመሰንዘር የሚጋብዙን ሁኔታዎች ቢከሰቱም፣ እነሱን ሃሳቦቻችንንም እንኳን ልናመጣ የምንፈልገውን ለውጥ በማጉላት አዎንታዊ ቀለም መስጠት እንደምንችል እናስታውስ፡፡
2. በምትሰጡት ሃሳብ (Comment) ሰዎችን መንቀፍ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሰዎችን መደገፍ ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ስህተት አራማጅን ሰው መንቀፍ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖርም፣ አብዛኛው ዝንባሌያችንና ልምምዳችን ግን የሚደገፉትን ከመደገፍ ይልቅ የሚነቀፉትን መንቀፍ ላይ የሚያተኩር እንዳይሆን መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡
3. በምትሰጡት ሃሳብ (Comment) አማካኝነት አንድን ሰው ለማድነቅ ብላችሁ ሌሎችን አለማንቋሸሽ ይመረጣል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ስናደንቅ ሊደነቁ የማገባቸውን የሌሎች ሰዎች ሁኔታ ማጋለጣችን ባይቀርም፣ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ሰዎችን ማንቋሸሽ የእኛን የተቀባይነት ደረጃና የመልእክት ጥንካሬ ስለሚያወርደው በጥንቃቄ ማድረግ መልካም ነው፡፡
4. በምትሰጡት ሃሳብ (Comment) አማካኝነት የምትሞግቱት ነገር ካለ ከሰዎቹ ጋር ከመጋጨት ይልቅ ሃሳባችሁን ከሃሳባቸው ጋር በማጋጭ የበረታው ሃሳብ እንዲያሸነፍ መፍቀድ ይመረጣል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን ጤና-ቢስ ሃሳብ ለመሞገት የሰዎቹን ማንነት መጥቀስ የግድ ቢሆንም፣ ዋናው ትኩረታችን ግን የሰዎቹን ስም፣ ህልውና እና ማንነት ማንቋሸሽ ሳይሆን የተዛባ ሃሳባቸውን ማዳከም እንደሆነ አንዘንጋ፡፡
5. በምትሰጡት ሃሳብ (Comment) ላይ እርግጠኝነት ከሌላችሁ ሃሳብ ከመስጠት ይልቅ ዝም ማለት ይመረጣል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ቀለል ያሉ ሃሳቦችን መሰንዘር ችግር ባይኖረውም፣ የከረረ ስሜትንና አቋምን ለመግለጽ የሚጋብዝ ሁኔታ ሲገጥመን ግን በነገሩና በእውነታው ላይ እርግጠኛነትን መያዛችንን አንዘንጋ፡፡
https://hottg.com/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
>>Click here to continue<<
