TG Telegram Group Link
Channel: የሜሪ አጫጭር ተረኮች
Back to Bottom
«አንተ አብረኸኝ ስላለህ ደስ ነው ያለኝ!! የማለቅሰው አጎቴ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ሰፈሩ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ባንተ አይደለም እሺ!!» እያልኩት ተደጋግፈን እንቅልፍ ወሰደን!!

አዲስ አበባ

አዲስ አበባ <እንኳን ደህና መጣችሁ!> ብላ አልተቀበለችንም!! አውቶብስ ተራ እንደወረድኩ ነው ይሄ ከእኔ ዓለም በምንም የማይገጣጠም ውቅያኖስ እንደሆነ የገባኝ!! አዲስ አበቤዎች ሲያወሩ እንኳን የሚደማመጡ አይመስሉም። ሁሉም ያወራል፣ ሁሉም ይራወጣል፣ የተረጋጋ የለም! የት ሊሄዱ እንደሚቸኩሉ እንጃ ቸኩለው እያወሩ ቸኩለው እየተገጫጩ ይተላለፋሉ። ከራሱ መንገድ ውጪ ማንም በአካባቢው ያለውን አያስተውልም። በጩኸቱ ጆሮዬ ዛለ። ኪዳንን በአንድ እጄ ጥፍንግ አድርጌ ይዤ በሌላ እጄ ልብሳችን ያለበትን ፔስታል ይዤ <አልጋ> የሚሉ ልጆችን ተከትዬ የዛን ቀን የትኋን እራት ሆነን አደርን!! አዲስአበባ ቀማኛው ብዙ ነው ሲሉ ስለሰማሁ ምግብ ልንበላ በገባንበት ሁሉ የማየውን በጥንቃቄ እከታተላለሁ። በሀገሬ ባለፍኩ ባገደምኩበት ሰው የሚጎነበስልኝ ፣ ሁሉ የሚያውቀኝ ነበርኩ:: ….. እዚህ ባዳነት ተሰማኝ። እዚህ ማንም ነኝ!! ከኪዳን ውጪ የሚያነጋግረኝ እንኳን የሌለ ማንም ነኝ!!

በበነጋታው ስልክ መደወያ ቦታ ፈልጌ አሰልጣኙጋ ስልክ ደወልኩ እና ያለንበት መጣ!!! የምንከራየው ቤት እስካገኝ እቤቱ ይወስደኛል መቼም የእግዜር እንግዳ ዝም አይባልም ብዬ ስጠብቅ እሱ እቴ!! የዛኑ ቀን በእጁ በያዛት ስልክ ለደላሎች ደውሎ ቤት እንዲፈልጉ ነግሮልኝ የማላውቅበት ምድረ ገበያ ህዝብ የሚተራመስበት ሰፈር አልጋ አስይዞን ሄደ። አሁን ብቻዬን እንደሆንኩ አወቅኩ!! አባት እና እናቴ የሉም! አጎቴ የለም! አሁን ለኪዳን እነሱን መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ ለካ!!

አንዲት ትንሽዬ የጭቃ ቤት በአስጠኚው በኩል አጊንተን ተከራየን!! የምንተኛበት እና የምናበስልበት ዕቃ ገዛን!! ኑሮ ተጀመረ!! መጀመሪያ አካባቢ መኪና ማጠብ ስራ አገኘሁ። አምስት መኪና በነፃ ካጠብኩ በኋላ ነው የቀጠሩኝ። ሰፈሩን መውጫ መግቢያ ተሽሎክልኬ አወቅኩት። የሆነ ቀን ጠዋት ከኪዳን ጋር ዳቦ በሻያችንን በልተን ከቤት ልወጣ ስል

«ሜል?»
«ወዬ»
«እንዳትቆጭኝ! አልቆጣህም አባባ ይሙት በይ!» አለኝ ከዓመታት በኋላም የሞተውን አባቴን እየገደልን ነው የምንምለው።
«አባባ ይሙት አልቆጣህም ምንድነው?»
«እኔምኮ ትልቅ ልጅ ሆኛለሁ!! ስራ ፈልጌ የማልሰራው ለምንድነው?» አለኝ እንዳልቆጣው እየተሳቀቀ

«አባባ ይሙት እቆጣሃለሁ!! ሁለተኛ እንዲህ እንዳትለኝ!! አንተ አርፈህ ተቀመጥ ከወር በኋላ ትምህርት ሲጀመር ትምህርትህን ወጥረህ ትማራለህ!! ስራህ ትምህርትህ ነው!! ተግባባን?» ብዬ እንደፈራውም ጮህኩበት

«አዎ» ሲለኝ ስቅቅ ብሎ አሳዘነኝ እና አቀፍኩት።

«ላንተ ብዬኮ ነው!! ታውቅ የለ እንደምወድህ? አንተ ተምረህ ስራ ስትይዝ ያኔ አንተ ትሰራለህ እኔ እቤት እቀመጣለሁ!! አሁን ግን እኔ ታላቅህ አይደለሁ? እኔ እሰራለሁ አንተ ትማራለህ!!» ስለው ጭንቅላቱን ነቀነቀ። እናት መሆን ፣ ልጅ ማሳደግ : እናት መቼ እንደምትቆጣ: መች እንደምታባብል : መች እንደምትቀጣ ... ምኑም በቅጡ ሳይገባኝ ለካ እናትም የመሆን ሀላፊነትን ወስጃለሁ።

የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አንዱ በጉልቤነቱ የሚፈሩት ጥጋበኛ ሴት ሆኜ ከወንዶቹጋ መኪና ማጠቤን ሊያፌዝበት ሞከረ። ያልፈጠረብኝን አይ አለመተዋወቅ ብዬ ታገስኩት። በሌላኛው ቀን መጥቶ ግን ከኋላ ቂጤን ሲመታኝ መታገስ የምችልበት ልብ አጣሁ እና አፍንጫውን አልኩት። በቦታው የነበረው ሁሉ ደንግጦ ብድግ አለ። ልጁ ያልጠበቀው ቡጢ ስለጠጣ መጀመሪያ ተደናግጦ የደማ አፍንጫውን መጠራረግ ጀመረ። ቀጥሎ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ሊገለግሉት የያዙትን ሁሉ እየተወራጨ ደነፋ!! እኔ በናታችሁ ልቀቁት ስል ፣ እሱ ከወድያ ልቀቁኝ ሲል …. አንድ በአንድ ሰው እየተሰበሰበ የፈሪ ድብድብ ሆነ። ድንገት ለቀቁት እና እኔና እሱ ተያይዝን። ለካስ ሲገላግሉ የነበሩት ልጆች የሸሹት ፖሊሶች መምጣታቸውን አይተው ነው። ፖሊሶቹ ማናችንንም ምንም የጠየቁትም ያጣሩትም የለም! አፋፍሰው ብቻ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን።

<እባካችሁ ትንሽ ወንድሜ ብቻውን ነው> ብል ማን ይስማኝ? ጀርባዬ ላይ ካሳረፈው ጥቁር ዱላ ህመም በላይ የተሰማኝ የኪዳን ብቻውን በፍርሃት መራድ ነው። ትቼው የጠፋሁ ይመስለዋል? ሊፈልገኝ ወጥቶ መንገድ ይጠፋበት እና የማያውቀው መንደር መንገድ ላይ ሲያለቅስ ታየኝ። ብዙ ክፉ ነገር ታየኝ። ተንዘፈዘፍኩ። ደቂቃ ባለፈ ቁጥር ፍርሃት ከአንጀቴ ይተራመሳል። ሰዓቱ አይሄድም!! ማልቀስ እፈልጋለሁ ግን እንባ አይወጣኝም።

<ጥጋባቸው በርዶላቸዋል> ብለው በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሲለቁን እግሬ መሮጥ አቅቶት ተንቀጠቀጠ። የቤቱን በር አልፌ ስገባ ኪዳን ባይኖር የት ብዬ ነው የምፈልገው? ራሴን ረገምኩ! ደህና ተደላድሎ ከሚኖርበት ቤት ይዤው የወጣውበትን ቀን ረገምኩ። ሰውነቴ እየተንቀጠቀጠ በሩን ከፍቼ ስገባ ኪዳን ኩርምት ብሎ ፍራሹ ላይ ተቀምጧል። ሲያየኝ ዘሎ እላዬ ላይ ተሰቅሎ እንደህፃን ድምፅ አውጥቶ ማልቀስ ጀመረ። የሱ መርበትበት ይብስ አርበተበተኝ እና አብሬው እዬዬ ማለት ጀመርኩ። እህል ሳይበላ ከአሁን አሁን መጣች ብሎ ኩርምት ብሎ በር በሩን ሲያይ ነው ያደረው።

ፈሪ ሆንኩ! ለኪዳን ስል ፈሪ ሆንኩ!! ለእሱ ስል ብቻዬን ብሆን የማልውጠውን ብዙ መናቅ ዋጥኩ። ለእሱ ስል የማላልፈውን ውርደት አለፍኩ። አንገቴን ደፋሁለት!!! ከብዙ ስራ ቅየራ በኋላ …… ኪዳንም ትምህርቱን ብዙ ቀን ከተማረ በኋላ ….. ብዙ ጥጋበኛ አንገቴን ደፍቼ ካሳለፍኩ በኋላ …..….. በራሴው ሰውንም ከተማውንም መልመድ ከጀመርኩ በኋላ……. የከተማ ሚኒባስ ወያላ ሆኜ እቁብ መጣል ከጀመርኩ በኋላ …… አንድ ቀን ተሰብስበን ተራ የምንጠብቅበት ቦታ ኪዳን መጥቶ ሲፈልገኝ በእድሜ በጣም ከሚበልጠው ልጅ ጋር ነገር ተፈላለጉና ኪዳንን በቁመቱ አንስቶ በጠረባ ጣለው። ደርሼ ልጁን ሳንጠለጥለው ከሚፈላው ደሜ ውጪ የሚሰማኝ ነገር አልነበረም። ምን እንዳደረግኩ አላውቅም!

«ሜል!» ብሎ ኪዳን ሲለምነኝ ነው ጆሮዬ ድምፅ መስማት የቻለው። ፖሊስ ከመቼ መጥቶ ብዬ ስሳቀቅ ግርግሩ ሰክኖ የሆነ ሰውዬ ተጠጋኝ እና

«ስራ ልስጥሽ! እዚህ ከተሳፋሪ ፍራንክ እየለቃቀምሽ ፀሃይ እና ዝናብ እየተፈራረቀብሽ ከምታገኝው እልፍ እጥፍ ደመወዝ የሚከፈልሽ ስራ ላስቀጥርሽ! » አለኝ

«እንዴ ምንድነው ስራው ?» አልኩት

«ደውዪልኝ» ብሎ ስልኩ ያለበት ቢዝነስ ካርድ ሰጥቶኝ ሄደ። ተሰብስቦ የነበረውን ወሬኛ አላስተዋልኩትም ነበር።

«ኸረ በለው! በአንድ ቦክስኮ ስሙን ሁሉ ነው ያስረሳሽው!! መሬት ሲደርስ ኦልሬዲ ቤተሰቡን ዘንግቷል!!» እያሉ ትከሻዬን አቅፈው ማውራት ጀመሩ። ሊያዋራኝ ይኮራ የነበረ ሁላ ጓደኛዬ ሊሆን ሰበብ ይፈልግ ጀመር።

...... አልጨረስንም!!! ....
(ስለመልካም የልደት ቀን ምኞታችሁ ሁሉ አምላክ አብዝቶ ይባርክልኝ!! ውብ ቀን ውብኛ ዋሉልኝ!! ❤️❤️❤️❤️)
ቤተሰብ አፉ በሉኝ!! ለሊት early flight ስለነበረብኝ 11 ሰዓት የወጣሁ ስጦዝ ውዬ አሁን ገና ነው መቀመጫዬ ቤቱ ገብቶ መቀመጫ ያገኘው!! (የቡዴና ጉዳይ ነው!) ለሊት ነቅቼ እፅፋለሁ እንጂ አንድ መስመር እንኳን መጨረስ አልችልም!! ትወዱኝ የለ? ፌንት በልቼ (ማነው ግን ፌንት ይበላል ያለን? ምን ምን ይላል?) እናላችሁ ፌንት በልቼ ሜላት ስሙን እንዳዘነጋችው ሰውዬ የታሪኩን ሂደት ከምረሳባችሁ እረፍት አድርጌ በአዲስ መንፈስ ብፅፍ ይበጀናል።

ውብ አዳር!!❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አንድ)
(ሜሪ ፈለቀ)

« የበፊቷን ሴት መሆን አልፈልግም!!!» አልኩት ኪዳንን እንዴት እንደምናስወጣው የሚያቀርበው አማራጭ ሁሉ የሆነን ሰው ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆንብኝ

«ይሆንልሻል ?» አለ ማደንዘዣው እየለቀቀው የቁስሉ ህመም እየተሰማው ሲያወራም ጭምር እየተሰቃየ ።
«ውስጥ ያለህ ሰው ካሜራ መግጠም የሚያስችል ቅርበት አለው?»
«ይመስለኛል!! ምን አስበሽ ነው? ስልኬን ከኪሴ ውስጥ ወዲህ በይውማ እርግጡን ልንገርሽ! በቅድሚያ ግን ያሰብሽውን ልስማው?»

አመነታሁ! ከራሴ ውጪ ማንንም ሰው አምኜ የማውቅ ሰው አልነበርኩም! አለማመን በደሜ ውስጥ ያለ ነገር ነው። በሁለት ወር ከምናምን ጊዜ ሙልጭ ብሎ ሊጠራ አይችልም። የብዙ ዓመት ልምዴ ሁሌም ጀርባ እና ፊቴን ራሴው ስጠብቅ ፣ በመንገዴ የተደገፍኳቸው ሲንሸራተቱብኝ ፣ ከጎኔ ናቸው ያልኳቸው ጎኔን ሲወጉኝ ….. ነው። አውቃለሁ እኮ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶልኛል። በማንም ሰው ሚዛን ከዚህ በላይ ከእኔ ጎን መሆኑን ሊያሳይለት የሚችል ምንም ማረጋገጫ አይኖርም። በቃ ግን የዛች ሜላት ልብ አመነታ። ለአፍታ ዝም ስል ገብቶታል።

«አሁንም እምነትሽን አላገኘሁም ማለት ነው?? እንዲያው ምን ባደርግልሽ ነው የምታምኝኝ ዓለሜ?» የጎንጥ ድምፅ አይመስልም። ሳላምነው እንኳን የሚቆጣኝ ድምፅ ሳይሆን ምንም ማድረግ የማይችል በጣም የተከፋ ድምፅ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ <ዓለሜ> ብሎ እንደጠራኝ ያላስተዋልኩ መስዬ አለፍኩ።

«እሺ ይሁን!! ዝርዝሩን አትንገሪኝ!! እንዲሆን የምትፈልጊውን ብቻ ንገሪኝ!!» አለ በዛው በከፋው ድምፁ

«ውስጥ ያለህን ሰው ምን ያህል ታምነዋለህ?»
«በመድሃንያለም!! አንች የምታውቂያቸውን ሰዎች አላውቅም!! እኔ የማውቃቸው ግን እስከህይወት የሚታመኑኝ ሰዎች አሉኝ!!»

ለእኔ የማመን ትርጉም እርሱ ካለው ይለያል። አመኔታ ከሚታመነው ሰው ይልቅ የሚያምነው ሰው ላይ ይመስለኛል ጫናው። ማንንም ሰው <እገሌ በፍፁም አይከዳኝም! በፍፁም ፊቱን አያዞርብኝም!> ብሎ መቶ ፐርሰንት ሰውየው ላይ መዘርፈጥ የዋህነትም ጅልነትም ነው። ምክንያቱም ማንም ሰው በማይደራደረው ነገር ከመጡበት አሳልፎ ይሰጥሃል። እኔ እገሌን አምነዋለሁ ስል ፍፁም አይከዳኝም ማለቴ ሳይሆን ቢከዳኝ ወይ ፊቱን ቢያዞርብኝ እንኳን ያለበቂ ምክንያት አልከዳኝም ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ክፍት እስከመሆን የሚደርስ ልብ አለኝ ማለት ነው። ከበቀል በፊት <ለምን?> ብዬ መጠየቅ የምችልበት ልብ ካለኝ ያን ሰው አምኜዋለሁ ማለት ነው።

ሰዎች በፍቅር ለወደቁለት ሰው <አምንሃለሁ> ወይም <አምንሻለሁ> ብለው ልባቸውን ሲሰጡ ያን የወደዱትን ሰው <በፍፁም ልቤን እንደማትሰብረው አውቃለሁ!> እያሉት ነው እንዴ? እኔ አይመስለኝም። <ብትሰብረው እንኳን ልሰጥህ ዝግጁ ነኝ! ብትሰብረው እንኳን ህመሙን እስከመቀበል ድረስ ነው ፍቅሬ!> እያሉት እንጂ!


«አትፍረድብኝ! የመጣሁበት መንገድ ከሚታመኑት ይልቅ የማይታመኑት የበዙበት ነው! በዛ ላይ አንዲት ስህተት ብሰራ አደጋ ላይ ያለው ኪዳን ነው! በሱ ጉዳይ ማንም ላይ ባልታመን ተረዳኝ!! ደግሞም እኮ ጎንጥ ለልጅህ …… » ብዬ ነገሩን መጨረስ ይቅር ያላልኩት ያስመስልብኛል ብዬ ተውኩት

«ላውጋሽ ሁሉንም ከስር መሰረቱ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? ስሚኝና ቅያሜሽን ያዥው ካሻሽ!»
«ቅያሜ አይደለምኮ! ግን እረስቼዋለሁ ብልህ ውሸቴን ነው!»

እውነታው ይቅርታ ማድረግ እና መርሳት ይለያያል። ይቅር ብዬዋለሁ ማለት ከዛ በኋላ ያደረገኝን ነገር ሳስታውስ ቁጣ ወይም በቀል ወይም ጥላቻ ሳይሰማኝ አልፈዋለሁ ማለት ነው እንጂ ድርጊቱን ረስቼዋለሁ ማለት አይደለም!! ይቅር ብያለሁ ማለት የበደለኝን ሰው ሳየው ለቡጢ የሚዘረጋው እጄ ለማቀፍ መዘርጋት ይችላል ማለት እንጂ ያ ሰው በዛው ወጥመድ እንደማይጥለኝ አምኜ (መጃጃል ብለው ይቀለኛል) መጠንቀቅ እተዋለሁ ማለት አይደለም!! በኔ ልምድና ፍቺ ይቅርታ ይህ ይመስለኛል። ሀይማኖተኛም ባልሆን ከሰማኋቸው ጥቂት የመፅሃፍ ቅዱስ ስብከቶች በመነሳት እራሱ እግዚአብሄርም ይቅር ብዬሃለሁ ሲል በጥፋትህ አልቀጣህም ምህረት አጊንተህበታል ማለቱ እንጂ ስራህን ረስቸዋለሁ ማለቱ አይመስለኝም። ቢሆን ኖሮ እስራኤሎችን አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ይቅር ካላቸው በኋላ አንድ ሺህ ሁለተኛ ጊዜ ባዕድ ሲያመልኩ ከግብፅ ካወጣቸው ጀምሮ የበደሉትን ባልዘረዘረላቸው ነበር።
ጎንጥ እኔጋ መስራት ከጀመረ ከተወሰነ ወር በኋላ ልጁ ታማበት ነበር። ለሳምንት አስፈቅዶኝ ጠፍቶ ተመልሶ ሲመጣ ልቡ ተሰብሮ ልጁ ኩላሊቷ መቀየር እንዳለበት እና የሱ ኩላሊት ማች እንዳላደረገ ሲነግረኝ ምክንያቴ ለሷ ማዘን ይሆን ለሱ ወይም በደም የጨቀየ ህይወቴን በደል መቀነስ ለማላውቃት ህፃን ኩላሊቴን ልሰጥለት ፈቃደኛ ነበርኩ። ሄጄ ምርመራውን አድርጌላት ነበር።

የዛን ቀን ለእመቤት ይገርማታል ብዬ ለጎንጥ ልጅ ላደርግ ያሰብኩትን ስነግራት እሷ ግን በሚያሳዝን አይን እያየችኝ
«ሜልዬ? የመረጥሽውን ህይወት ድጋሚ የማስተካከል እድል ቢኖርሽ ምርጫሽ ይለይ ነበር?» አለችኝ

«አላውቅም! አስቤው አላውቅም! ምናልባት እንደማንኛውም ሰው ዓይነት ህይወት ኖሮኝ ቢሆን ምን እንደምመርጥ አላውቅም!! ግን ማንኛዋም ህፃን እኔ ያለፍኩበትን መንገድ አላለፈችም!! ማንኛዋም ህፃን እኔ ያየሁትን አላየችም!!»

«እኔ ግን ሲመስለኝ እንደማንኛዋም ሴት ሚስት መሆን እናት መሆን ….. ስስ መሆን …. ማፍቀር …. ባፈቀሩት ሰው ልብ መሰበር ….. ማለቃቀስ ….. እነዚህን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት ልትሰሚው ስለማትፈልጊ እንጂ የሆነ ልብሽ ጥግ ተደብቆ ያለ ይመስለኛል።» አለችኝ። ጋዜጠኛ አይደለች? ወሬ ማዳመቅ ትችልበታለች።

«ሌላውስ ይሁን ልብ ተሰብሮ ማልቀስ መፈለግ የጤና ነው?» አልኳት ወሬው ሲኮሳተር ራሴን እፈልግ ይሆን አልፈልግ መጠየቅ ሽሽት። አፍቅሬ አላውቅም ወይም ፍቅር ይሉት ነገር በእኔ የህይወት ጉዞ ገደቡን ያለፈ ቅብጠት ነው። ከቅፅበት ስጋዊ መንደድ አልፎ አቅሉን ስቶ በፍቅሬ የነሆለለ ወንድም አላስታውስም!! ጭራሹኑ ከልብሴ ስር የሴት ገላ መኖሩ ትዝ የሚለው ወንድ ልብሴን አውልቄ ያየኝ ብቻ ይመስለኛል።

«እሱ ራሱ ጣዕም እንዳለው ብታውቂ? አፍቅረሽ ጧ ብለሽ! ከሌላ ሴት ጋር አየሁት ብለሽ ግንባርሽ ላይ ሻሽ ሸብ አድርገሽ ትኩስ ነገር የሞላው ኩባያ ይዘሽ ለጓደኛሽ ማውራት ……. »

«በይ እናቴ ያንቺ የጤና ፍቅር አይደለም! ታየኝኮ ማግ ይዤ ለወንድ ስንሰቀሰቅ!» ብያት ስቄ ከደንኩት።

የጎንጥን ልጅ ሆስፒታል ሄጄ ሳያት ተስፋ ባዘሉ የልጅነት ዓይኖቿ ውስጥ የራሴን ልጅነት አየሁት። ኩላሊቴ ሊያድናት እንደሚችል ሲነገረኝ የነበረኝን የደስታ ስሜት የዛሬን ያህል አስታውሰዋለሁ። ከዛን ቀን በፊት ሆስፒታል የመተኛት ከፍተኛ ፍርሃት ነበረብኝ። በተለይ ማደንዘዣ የሚያስወስድ ነገር ከሆነ። ራሴን ባላወቅኩበት ቅፅበት የሆነ ሰው የሆነ ነገር ያደርገኛል ብዬ እፈራለሁ። በጥይት ተመትቼ ሀኪም አምኜ ሆስፒታል የማልተኛ ሴት በገዛ ፈቃዴ ቅደዱና ኩላሊቴን አውጡ ብዬ የሆስፒታል አልጋ ላይ ልተኛ ዝግጁ ነበርኩ። ማንም ምንም ቢያደርገኝ ይሁን ከዛች ህፃን አይበልጥም ራሴን አስቱኝ ብዬ ፍርሃቴን ልውጥ ዝግጁ ነበርኩ። መኪናዋን ጊቢ እስካስገባ እንኳን አቅበጥብጦኝ

«እንኳን ደስ አለህ!!» ስለው ፊቱን ወደሌላ ቦታ አዙሮ እየተገማሸረ
«በአምላክዎት! ግን ሀሳቤን አንስቻለሁ!! ከዚህ ወድያ የእርሶ እርዳታ አያሻኝም!» አለ ሁኔታው ንቀት ወይ ፅያፌ በሚመስል ሁኔታ እየጎፈላ !! የተሰማኝ ስሜት ልሰጠው የነበረውን ኩላሊት አልፈልግም የተባልኩ ሳይሆን ሊሰጠኝ የነበረ ኩላሊት ተከልክዬ ሞቴ የፈጠነ አይነት ነገር ነበር። ምክንያቱን ደጋግሜ ብጠይቀውም መልሱ

«ራሴን እንዳብራራ አያስገድዱኝ!! ሌላ ሰው ተገኝቷል!» ብቻ ነው። የሆነ የማላውቀው ተስፋ ልበለው ደስታ አላውቅም የተነነ! የሆነ ነገሬን የቀማኝ መሰለኝ። ያበሳጨኝ ደግሞ ንግግሩ ትህትና እንኳን ያልነበረው መሆኑ ነው። የሆነ በድክመቴ ያገኘኝ ነገር መሰለኝ።

«ድሮምኮ የሰው ልጅ ያለቦታው ክብር ሲሰጡት ሽቅብ ካልሸናሁ ይላል።» አልኩት ብስጭት እያልኩ

«እትዬ ይልቅ እላፊ አንነጋገር!! ስራዬን መልቀቅ ስለምሻ ሌላ ዘበኛ ቢፈልጉ ጥሩ ነው!» ሲለኝ የተናደድኩበት ምክንያት የቱ እንደሆነ ሳይገባኝ ጨስኩ!

«ለአንድ አመት ነው ልትሰራ የፈረምከው!! ኮንትራትህን ሳትጨርስ ወዴትም አትሄድም! ሞክረኝና ታያታለህ!» ብዬው ገባው።

በነጋታው ለራሴ ራሱ በማይገባኝ ምክንያት ልጁ ደህና መሆኗን ማወቅ ፈለግኩ። አላውቅም ብቻ እጇን ይዤ <አይዞሽ> ማለት አማረኝ። ምናልባት እሙ እንዳለችው የከደንኩት እናት የመሆን ስሜት ይኖር ይሆናል። እልሄን ውጬ ልጁን ላያት እንደምፈልግ ስነግረው።

«ይቅርታ ያድርጉልኝ እትዬ ለጊዜው ከቤተሰብ ውጪ ማንም እንዲያያት አልፈቅድም!! በሌላ አይዩብኝ ልነግሮት በማልችለው ምክንያት ነው!! " አለኝ። የፈረደባት እመቤት ጋር ሄጄ

«ይሄ የማይረባ! ሌላ ሰው ስለተገኘ አያስፈልግም አይለኝም? ቱ! » እያልኩ ስደነፋ እንባዋ እስኪፈስ እየሳቀች

«እንዲህ ያበሳጨሽ ለምን ኩላሊቴ አልወጣም ነው ወይስ ለምን እሱ እንደሌሎች በዙሪያሽ ያሉ ሰዎች እቴጌ እመቤቴ አላለኝም አልተሽቆጠቆጠልኝም ነው? ይሄ ሰውዬማ ከገባ ጀምሮ ነርቭሽን ነክቶታል።»

«ባክሽን አንቺ ደግሞ! ጭራሽ ስራዬን እለቃለሁ ይበለኝ?» እኔ እበሳጫለሁ እሷ ትስቃለች። «ምኑ ነው አሁን ይሄ የሚያስቀው?»

«ለማንም ሰውኮ እንዲህ ቦታ ሰጥተሽ አታውቂም! ያውም ለዘበኛሽ? ጥጋቡ ነው የሚያንተከትክሽ ወይስ ሌላ ነገር አለ?» አለችኝ መሳቋን ሳታቆም። ከዛን ቀን በኋላ ስለጎንጥ ስናወራ < ጎንጤ ጥጋቡ> ነበር የምትለው።

ከቀናት በኋላ እሙ እንዳለችው የመንተክተኬ ምክንያቱ አልገባ ሲለኝ። ስራውን መልቀቅ እንደሚችል ሌላ ዘበኛ እንዳገኘው ስነግረው ደግሞ

«ሀሳቤን አንስቻለሁ! ኮንትራቴን ሳልጨርስ ወየትም ፍንክች አልልም» ብሎ አናቴን በብስጭት አዞሮው።

«እኔ ነኝና ሜላት! ሰውዬ ስትፈልግ እወጣለሁ ስትፈልግ እገባለሁ እያልክ እንደፈለግክ ሀሳብህን የምታነሳ የምትጥልበት የሰፈርህ ጠጅ ቤት አይደለም ይሄ! የቀጠርኩህ እኔ ነኝ! ስፈልግ ደግሞ በቃኝ ብዬ የማባርርህም እኔ ነኝ! ከነገ ጀምሮ ላይህ አልፈልግም!»

«ተናገርኩኮ ፍርማዬን ሳልጨርስ አልሄድም!» ብሎ እያወራሁት ትቶኝ ሌላ ስራ መስራቱን ቀጠለ።

አሁን ሲመስለኝ ያልጨረሰው ስራ ስለነበረ ነው የቆየው። ከዛ ቀን በኋላ የሰላም ቃላት ተለዋውጠን አናውቅም ነበር። አሁን ልለው የነበረው። <ለልጅህ ስልኮ እዛ አልጋ ላይ ተኝቼ ልደነዝዝ ዝግጁ ነበርኩ። ያ እንኳን ለጠላቶቼ ከመስራት አላገደህም!> ልለው ነበር። ይቅር አልኩት እንጂ አልረሳሁትም።

***********************************


ያቀበልኩትን ስልኩን ባልተመታበት ጎን እጁ እየነካካ ያልኩትን እንዳልሰማ ዝም ብሎ አልፎ!!
«ማንም ሰው እንዳልተከተለሽ እርግጠኛ ሆነሽ እዚህ ቦታ ሂጂ! የምትፈልጊውን ንገሪው።» ብሎ የምንገናኝበትን አድራሻ ሰውየው የሚለብሰው ልብስ እና ኮፍያ ቀለም። የምንግባባበት ኮድ ፣ የምንገናኝበትን ሰዓት እና የሰውየውን ፎቶ በጭንቅላቴ መያዝ እስክችል አስደጋገመኝ።

«እሺ ግን አንተ እርግጠኛ ነህ ምንም አትሆንም?»

«አታስቢ! ለጊዜው እኔን ለማጥቃት ሆስፒታል ድረስ የሚያስመጣ ምክንያት ያለው ጠላት የለኝም!» አለ እንድሄድ መውጫውን እየጠቆመኝ። ተነሳሁ ግን እግሬ አልተራመደም! ቆሜ ግራ በገባው ስሜት ዘቅዝቄ እያየሁት ቆየሁ። እጄን በሚይዘኝ አያያዙ ያዘኝ እና

« ድንገት ካንቺ አቅም በላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር ቢያንስ ምንም ምርጫ ከጠፋሽ የምትደውይለት የመጀመሪያ ሰው እንደሆንኩ ቃል ጊቢልኝ!» አለኝ

«ብደውልልህስ? ቀና ማለት እንኳን የማትችል ሰው ምን እንድታደርግ ነው?»
«ብቻ ደውይልኝ! ምልክት ስጭኝ! ያን እንደምታደርጊ ቃልሽን ስጭኝ!!» እያለኝ ስልኩን ወደ ስልኬ ደወለ። «ስልክሽ ፊት ለፊት የኔ ቁጥር ይኑር!»

«እሺ በራሴ የማልወጣው ነገር ከገጠመኝ እደውላለሁ።» አልኩት እጄን አልለቀቀኝም። ላስለቅቀውም አልቸኮልኩም። በእጁ የአውራ ጣት እንደመደባበስ ካደረገው በኋላ አንስቶ ወደ ከንፈሩ አስጠጋው። የእጄን አይበሉባ ሳይሆን ገልብጦ መዳፌን የውስጥ እጄን መሃሉን በከንፈሩ በስሱ ሳመው። ሳመው ወይ ዳሰሰው ወይ ተጫነው። የሆነ ነገር …….. የእጅ ውስጥ ተስሞ ሰው እንዲህ እንደመስከርም እንደመጦዝም ያለ ስሜት ይሰማዋል?

«…. ተደናበርኩልሽ ጥይት እንደሳተው!» ያለው ዘፋኙ እንዲህ ተሰምቶት ነው የሚሆነው።

.............. አልጨረስንም ..............
ውብ ቀን ውብና አዋዋል ዋሉልኝማ❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሁለት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የሳመውን እጄን ተቀብዬው ከሆስፒታሉ ወጥቼኮ ታክሲ ተሳፍሬ ወደቃሊቲ መንገድ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ። እጄን ተቀብዬው አልኩኝ እንጂ እየተሰማኝ ያለው ወይ ከንፈሩ እጄ ላይ የቀረ ወይ ደግሞ እጄ እዛው እሱጋ ከንፈሩ ላይ የቀረ አይነት ስሜት ነው። የሳመኝን እጄን የሳመኝን ቦታ አንዳች የእግዜር ተአምር የፈለቀበት ነገር ይመስል እየደጋገምኩ አየዋለሁ። ደግሞ እየደጋገምኩ እሱ እንደሳመው እስመዋለሁ። ቀስ ብሎ ልስልስ ያለ …… እርጥበት ያለው ግን የሚሞቅ …….. ከዛ ደግሞ ከእግሬ ጥፍር ድረስ እስከ አናቴ እንደኤሌክትሪክ ሞገድ ጥዝዝዝ ብሎ በደምስሬ ውስጥ ይሆን የተጓዘው ፣ ከጅማቶቼ ጎን ለጎን ባገኘው ክፍት ቦታ ይሆን እየተሽሎከለከ የተጓዘው ባልገባኝ አካሄድ የናጠኝ …… የሆነ መለኮታዊ የሆነ መሳም ነገር …..

ስሳም የመጀመሪያዬ ሆኖ አይደለም። በትግል ፣ ኑሮን ለማሸነፍ በመጋጋጥ ፣ ኪዳንን ትልቅ ቦታ እንዲደርስ በመታተር ፣ በበቀል ፣ ሴራ በመጎንጎን ፣ ገንዘብ እና ጉልበትን በማካበት …… እና ሌሎች ብዙ ለሌላው ሰው ስሜት የማይሰጡ ነገሮችን በማድረግ ውስጥ ከወንድ ጋር የሚደራረጉ አልባሌ ነገሮችን ከማድረግ አልታቀብኩም። እንደእውነቱ ከሆነ ብዙ አድርጌያለሁ። አብሮ በመግባት እና በመውጣት እንደፍቅረኛ ወግ ያሳለፍኩት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከዳዊት ጋር ነበር። ዳዊት በከተማችን ውስጥ አለ የሚባል ባለሃብት ልጅ ነው። አባቱ በገንዘቡ ባለስልጣናትን የሚሾፍር ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። የእድሜ ልክ እስራት ፍርዴን በ6 ዓመት ያቀለለልኝ እሱ ነው። ውለታ ውሎልኝ አይደለም! በልዋጩ ሶስት ነገር ሰጥቼዋለሁ። አንድ የነበረኝን 48% የሚሸፍን የአንድ ባንክ አክስዮን (እሱ 20% ስለነበረው የእኔን ሲጨምር በባንኩ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ያደርገዋል።) ሁለት የራቁት ዳንስ ቤቱን ግማሽ ልሸጥለት (ዳዊት የገባው በዛ ነው) ሶስተኛው እና ዋነኛው (ሌሎቹ ተጨማሪ ናቸው) የአንድ እሱ የሚፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣን ሚስጥር (ለምን እንደፈለገው አልገባኝም ምክንያቱም እስካሁን አልተጠቀመበትም። ወይም እያስፈራራበት እየተጠቀመበት ይሆናል አላውቅም! ሰውየው ግን እስካሁን ስልጣኑ ላይ ነው።)

አንዲት ከትንሽ መንደር መጥታ ኑሮን ለመግፋት ትፍጨረጨር የነበረች ሴት የባለስልጣናት ሚስጥር እጇ ላይ እንዴት ወደቀ? ይሄ ሁሉ ሀብትስ እንዴት ተቆለለ? የሚሆን አይመስልም አይደል? ሆኗል!!

እዚህ ሀገር አንድ የገባኝን ነገር ልንገራችሁ! በተለይ እላይኛው የኑሮ መደብ እና ስልጣን ላይ የተፈናጠጡት ሰዎቻችን ዘንድ ….. በገንዘብ አቅም የማይሆን ምንም ነገር የለም። የሚለያየው የገንዘቡ መጠን ብቻ ነው። በመቶ ሺህዎች <ሀቀኝነቴን ፣ እምነቴን ፣ ህሊናዬን > ሲል የነበረ ለሚሊየኖች እጅ ይሰጣል። ለሚሊየኖች <ቤተሰቤን ፣ አምላኬን ፣ ቃሌን ፣ ህዝቤን > ያለው ደግሞ ለቢሊየን ወድቆ ይሰግዳል። ገንዘቡን የምታቀርብለት ሰው ወይም ድርጅት የሌለውን ያህል ወይም በቀላሉ ሊያገኝ የማይችለውን ያህል ገንዘብ መጠን አቅርብለት! የምትፈልገውን ይሸጥልሃል። ለምን ሚስቱ አትሆንም!!! በስህተት አምልጦ የሾለከ <በገንዘብ የማልሸጠው ህሊና አለኝ> ያለ ጎርባጭ ከተገኘ …… በነዛኛዎቹ ይሰለቀጣል። <ህዝብን በተገቢ ሁኔታ ባለማገልገል፣ የህዝብን ጥቅም ባለማስቀደም > ምናምን ምናምን የሚባሉ ፖለቲካዊ ሀቅ የሚመስሉ ውስልትናዎች ተለጥፈውበት እንደ እድሉ አርፎ የማይቀመጥ ቅብጥብጥ ከሆነ ወደ እስር ቤት ……. ለቤተሰቤ አንገቴን ልድፋ ያለ የቤተሰብ ሰው ከሆነ ደግሞ ወደቤት ይላካል።

እንግዲህ ከዳዊት ጋር አብረን መስራት የጀመርነው ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ መሆኑ ነው። ወድጄው አይደለም! ማለቴ እንደፍቅረኛ! እንደስራ ባልደረባ ጭንቅላቱ ለቢዝነስ የተፈጠረ፣ ለተንኮል እና ሴራ እኔን የተስተካከለ ፈጥኖ አሳቢ ፣ አባቱ ስለሚንቀው ለአባቱ የሆነ ጀብድ ሰርቶ ራሱን ማስመስከር አብዝቶ የሚሻ ሰው ነው። ከምለብሳቸው የወሮበላ ልብሶች ውስጥ ያለ የሴት ገላዬን ራቁቱን ሳያየው የተመኘ ብቸኛ ወንድ ይመስለኛል። ባለገንዘብ ፣ ባለጉልበት ፣ ባለሀይል ከሆንኩ በኋላ ለአመታት በዙሪያዬ ያለ ሰው ሁሉ እንደአለቃ የሚፈራኝ ፣ እንደሰው የሚያከብረኝ ፣ በዛ ካለ ትንሽ የሚቀርቡኝ እንደወዳጅ የሚያዩኝ ሴት ነበርኩ እንጂ ማንም በሴትነቴ የተመኘኝ አላስታውስም። ሴት መሆኔ ትዝ የሚላቸውም አይመስለኝም። እሱ ግን እንደስራ ባልደረባው ሳይሆን እንደሴት አየኝ!! የሚጋረፍ ፊቴ ሳያግደው ለወራት አበባ አመላለሰልኝ (እያየ ፊቱ ላይ አበባውን በጫጭቄ እበትነዋለሁ) ። <ደነዝ ነህ ወይ አትሰማም? አንተ ምኔም መሆን አትችልም!> እያልኩት በየቀኑ ቆንጆ መሆኔን ነገረኝ። በግልፅ <አይደለም ፍቅረኛዬ ልትሆን ለአንድ ቀን ተሳስቼ አብሬህ ብተኛ የምፀፀትብህ አይነት ሰው ነህ!> እያልኩት እንኳን በየቀኑ ሳይደክመው እንደሚወደኝ እየነገረኝ ዓመት ተቆጠረ። አንድ ቀን ከአባቱ ጋር ተጣልቶ ቢሮ ተቀምጦ እንደ ትንሽዬ ሴት ልጅ ሲንሰቀሰቅ ደረስኩ። ምን እንደሆነ ስጠይቀው እንባውን ከንፍጡ እየደባለቀ ማልቀሱን ሳያቆም በአባቱ ፊት ሁል ጊዜ ትንሽ መሆኑን ነገረኝ። አሳዘነኝኮ ግን ከማልወደው ነገሩ አንዱ ይሄ ልፍስፍስ ሴታ ሴት ነገሩ ነው። የዛን ቀን ግን

«ዛሬ እራት ልጋብዝህ?» አልኩት። እንባው ጥሎት ጠፋ! ከዛ በኋላ እንደፍቅረኞች የሚፈፃፀመውን ነገር ሁሉ እንፈፃፅማለን። አልጋ ላይ ሲያዩት ስልባቦት እንደሚመስለው ገላው አይደለም ወይም እንደሴታሴት አኳኋኑ። ስለዚህ ሴታዊ ፍላጎቴን ለማግኘት የማላውቀው ሰው ጋር ከምሄድ ጥሩ ቅብብሎሽ ነበር። አንዳንዴ ምንችክ ሲልብኝ እዘጋዋለሁ። ደግሞ መልሰን እንጀምራለን። ስለእውነቱ ግንኙነታችን ምን እንደሆነ ወይም ወዴት እንደሚሄድ እንኳን ውልም ስምም የለውም ነበር። እንኳን እጄን ስሞኝ የስሜቴ የመጨረሻ ጡዘት ጠርዝ ላይ እንኳን እንዲህ ዛሬ ጎንጥ እጄን ሲስመኝ እንደተሰማኝ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም!! ኸረ እንኳን ሊሰማኝ መኖሩንም አላውቅም!! ፊልም ላይ እንኳን ትኩረታቸው ከንፈር እንጂ እጅ እና ከንፈር ሲገናኝ እንዲህ አስማታዊ ስሜት እንዳለው መች ይነግሩናል?
ቃሊቲ በሩ ላይ እንደደረስኩ ዘበኛው ሲያየኝ እንደተለመደው በወዳጅነት «ቁርጠትዬ እስቲ ዛሬ ደህና ጊቢልኝ ታውቂ የለ ሚስትየው ስታላምጠኝ ነው የምትከርመው?» አለኝ።

«ይገባልሃል! ሂድ ባርችን ጥራልኝ!! እዚህ ስትቅለሰለስ እኮ እኔን አማክረህ አራት የወለድክ ነው የምትመስለው!»

«እሱማ ይጠራልሻል!! ግን ሰሞኑን ምርጫ ደርሷል ብለው የሌለ ህግ እያጠበቁ ነው!!»

«በቃ እሱ ታሳቢ ተደርጎ ይገባልሃል! መርዶ ሊነገራት ነው …. ወንድሟ ራሱን አጥፍቶ ነው …. መዓተኛ አይደለህ? አንዱን ቀባጥርና ጥራልኝ» ብዬ ከኪሴ ብር አውጥቼ አቀበልኩት። እሱ ወደ ውስጥ ሲገባ እየሆነ ያለውን ባላየ ዝም ብሎ የተቀመጠውን ሌላ ጠባቂ ብር በያዘ እጄ ጨበጥኩት። እየወተወተ አመሰገነኝ!!

«ያልጠየቅሽኝን እያካካስሽ ነው በየቀኑ?» አለች እሙ ገና ከመድረሷ «ጎንጤ ጥጋቡስ ዛሬ የለም?»

« ሁሉንም ነገር ላስረዳሽ ጊዜ አይበቃኝም!! እርዳታሽን ፈልጌ ነው የመጣሁት!! ከዛ ደግሞ በአጭሩ ትናንት ላይሽ የመጣሁ ጊዜ የማውቀው ታሪክ አልነበረም። የተመታሁ ጊዜ ሚሞሪዬን እንዳለ አጥቼ ነበር።»

«እና አሁን?» ብላ ግራ ገብቷት ከላይ እስከታች አስተዋለችኝ።
«ከትናንት እስከአሁን በ24 ሰዓታት ያልተፈጠረ ነገር የለም ብልሽ ይቀላል። አንድ ቀን ሳይሆን አንድ ዓመት የሆነ ነው የሚመስለው። ኪዳንን ላስለቅቅ በነበረ ሂደት የተኩስ ልውውጥ ነበር። በዛ መሃል ሲመስለኝ የሽጉጥ ተውሱ ትውስታዬን የወሰደብኝ ተኩስ አደጋን አስታወሰ እና ትውስታዬን ቀሰቀሰው። አላውቅም የተከሰተውን ብቻ አስታወስኩ ሁሉንም!!»

«wait a minute …. It’s too much information eko (ጭንቅላቷን የሆነ ከደነዘዘበት እንደማባነን፣ እንደማንቃት ያለ እየወዘወዘች) እሺ የትውስታ መሄድ መምጣቱ ይቆየኝ! ኪዳን safe ሆነ? ሆ! አይገርምሽም? I felt it ደግሞ እኮ……. Something was off » አለች አሁንም ዓይኗ እላዬ ላይ መርመስመሱን ሳታቆም!

«አልሆነም!! አሁንም እነሱጋ ነው ለዛ ነው እርዳታሽን የምፈልገው!!»
«ምንም እየገባኝ አይደለም! ተኩስ ነበር አላልሽኝም? አንቺ ታዲያ እንዴት እዚህ ተገኘሽ?»
«እሙዬ እመኚኝ ስናወራ ውለን ብናድር አይገባሽም!! ጎንጥ ከነርሱ አንዱ ነው። እኔ በሱ ምክንያት ነው እዚህ ያለሁት! እሱ ደግሞ ሆስፒታል ነው ተመትቶ!! (ይበልጥ ሲዞርባት አየሁ) ሌላ ቀን እነግርሻለሁ እሱን!!»

«ጎንጤ ጥጋቡ የእነሱ? እኮ ዘበኛሽ ሰላይ? እመኚኝ አመትም ብትነግሪኝ ይሄ ነገር አይገባኝም!!»
«እኔም ብዙ አልገባኝም ኪዳኔን ቅድሚያ ልስጥ ብዬ እንጂ!!»
«እሺ ምንድነው እንዳደርግልሽ የምትፈልጊው?»
«እናንተ ቴሌቭዥን ጣቢያ አሁን በምርጫው ዙሪያ እየሰራ ያለ ጋዜጠኛ እንዲተባበረኝ እንድታደርጊልኝ እፈልጋለሁ። እና ደግሞ ዛሬ የሁለት ሰዓቱን ዜና የሚያነበውን ሰው!»

«እሺ አገኘሁልሽ! ምን አስበሽ ነው?» አለች ጭራሽ ግራ ተጋብታ!!
«የምርጫው ዜና ሲተላለፍ አቶ ደሳለኝም አንዱ እጩ ተወዳዳሪ እንደመሆናቸው አንዱ ጋዜጠኛችሁ እቤታቸው ተገኝተው ላይቭ አጭር ቃለመጠይቅ ያደርጉላቸዋል። የምታደርጉትን አድርጉ ስትፈልጉ ሙሉውን ቃለመጠይቅ ከዜና በኋላ ያቅርቡት። እኔ የምፈልገው ከእኔጋ በተቀናጀ ሰዓት ላይቭ መግባታቸውን ነው።»

«እየገባኝ አይደለም!! የማስበውን እያሰብሽ ከሆነ በጣም ሪስክ አለው!»
«አውቃለሁ ግን ከዚህ የተሻለ ደም ሳይፈስ፣ ህይወት ሳይጠፋ ኪዳንን ላገኝ የምችልበት ምንም አማራጭ አልታየኝም!! ብቻ አንቺ ይሄን ማድረግ ትችዪ እንደው ንገሪኝ?»

«ወይ ጉድ! እስኪ ስልክሽን ስጪኝ ልደዋውል!!»

«እሺ በስልኬ ግን ምንም አይነት መረጃ እንዳትቀያየሪ! ከእኔ ጋር እንዲገናኑ ብቻ በሆነ መላ ንገሪያቸው። ምናልባት አላውቅም!! ስልኬን ሲሰጡኝ ውስጡ የነበረ ብዙ ነገር አፅድተው ነው የሰጡኝ። ሁሉንም ሶሻል ሚዲያዎቼን አዘግተውታል። መቼም የማላስታውስ ነበር የመሰላቸው መሰለኝ ወይም ከማስታወሴ በፊት እንደሚደፉኝ እርግጠኞች ነበሩ።»

«እንደዛ ከሆነ መደወሉ በራሱ ሪስክ አለው!! (ዘወር ብላ ወደ ጠባቂው) ሼባው? ዛሬ ለሚስትህ ዓመትበዓል ማስመሰል አላማረህም? ስልክህን ለ5 ደቂቃ ልደውልበት ?» አለችው። የጠባቂውን ስልክ ተቀብላ ሁለት ቦታ ስልክ ደዋወለች። ስልኮቹንም ለእኔ እንድመዘግብ ነገረችኝ። እኔ በምፈልገው መንገድ አዘጋጀችልኝ። መልሳ ለጠባቂው ከሰጠኋት ብር ጋር ስልኩን እየሰጠችው

«ሳመኝኮ!» የሚለው ቃል አፌን አምልጦ ሲወጣ እኔው ራሴ ስሰማው እና እሷ ጆሮ ጠልቆ ሽው ብላ ዞራ ስታፈጥብኝ አንድ ቅፅበት ነው።

«ጎንጥ! ከንፈሬን አይደለም ደግሞ እጄን ነው! እዚህጋ! » ብያት የሳመኝን እጄን እንደሌላ ሰው ባዕድ እጅ ሳየው አይታ

«እርፍ መጃጃል!! እጅሽን ስሞሽ ድንግልናዋን ዛሬ እንደሰጠች ልጃገረድ እንዲህ የተሽኮረመምሽ ሌላ ነገር ቢያደርግሽ ክንፍ አውጥተሽ ልትበሪ ነው?» ብላ መሳሜን ስላቀለለችብኝ ተናደድኩ። እንዲህ ያለ መሳም ተስማ ባታውቅ ነው ያልገባት። ወዲያው ቀጥላ «እንዴ ደግሞ ቆይ አሁን ከደቂቃዎች በፊት የእነርሱ ወገን ነው አላልሽኝም? አንቺ ሴት ዛሬ ግራ ያልተጋባ ምንም ወሬ ያለሽ አልመሰለኝም!»


«እንዳልሽው ነው ሁሉም ነገር ግራ የተጋባ ነው!! እጄን የሳመኝ ግን ግራ አያጋባም ሃሃሃሃሃሃ ኩልልል ብሎ ጥርት ያለ ነው።» ብያት ዝርዝሩን ከሰሞኑ መጥቼ ልነግራት ተስማምተን ተለያየን።

ተመልሼ ወደከተማ እየሄድኩ ተናኜጋ ደውዬ የተወሰነ ጥሬ ብር እና ለእንዲህ አይነት ጊዜ ለመጠቀም ገዝቼ አስቀምጫቸው ከነበሩ ሲሞች አንዱን እንድታመጣ ቦታውን ነገርኳት። በመንገዴ አዲስ የስልክ ቀፎ ገዛሁ። ዳዊትጋ ስልክ ደውዬ መኪናዬ ስለተበላሸች አሁኑኑ የእርሱን እንዲያውሰኝ ስጠይቀው በዛ ጭንቅንቅ መንገድ ነድቶ ሳይሆን በአየር ላይ በሮ በሚመስል ፍጥነት ያልኩት ቦታ ደረሰ። መኪናዋን ልነዳ ከተቀመጥኩ በኋላ ምንም እንኳን ሁሉም ትውስታዬ ቢመለስ ለሰከንዶች መንዳት መቻሌን እርግጠኛ አልሆንኩም ነበር። ወይም ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር።

ሁሉንም ነገር ባቀድኩት መሰረት ማስተካከሌን ለመቶኛ ጊዜ ካረጋገጥኩ በኋላ መፀለይ አሰብኩ። ሰዓቱ ገና ስለነበር የቀረበኝ ቤተክርስቲያን ገባሁ እና በሩ አካባቢ ቆምኩ። ከዛ ግራ ተጋባሁ!!! ላለፈው በደሌ ሁሉ አንድም ቀን መጥቼ ንሰሃ አልገባሁም!! በደም የተነከረ እጄን ወደ እርሱ መዘርጋት ድፍረትም ሆነብኝ!! ከዛ ደግሞ ያለፈውን ሁ,ለት ወር ከምናምንኮ ፀልዬ ነበር!! ሰምቶኝ ይሆን ወይስ አያውቀኝ ይሆን? ወይስ ባኮረፈ ፊቱ ነው ሲያየኝ የነበረው? ደግሞ መልሼ ከሰማኝ ይስማኝ ብዬ መፀለይ ጀመርኩ።

«አምላክ ሆይ ታውቀኛለህ ብዬ አስባለሁ። ካላወቅከኝ ሜላት ነኝ። ያለፈውን ሀጥያቴን ሁሉ ብናዘዝ መሽቶ ይነጋል። ከዛ በፊት ግን ያንተን እርዳታ እሻለሁ ተለመነኝ!! አሁንም የምሰራው ባንተ ዘንድ ልክ ይሆን ስህተት አላውቅም! ግን የተሻለ የመጨረሻ አማራጭ የምለውን ነው የመረጥኩት። እኔም ራሴ የድሮዋን ሜላት መሆን አልፈልግም! አንተም እንደማትወዳት ነው የማስበው!! ያለፈውን ሁሉ ማረኝ እና ለእኔ ስትል ሳይሆን ለወንድሜ ስትል፣ ለዛች ደጅህ ለማትጠፋ ምስኪን እናቴ ስትል ….. ወንድሜን ይዤው እንድመለስ እርዳኝ!! እባክህ እ? ከፈለግክ አትማረኝ! ከፈለግክም ቅጣኝ ግን በወንድሜ አትቅጣኝ!! እ? » የሆነ ከሰማይ <እሺ> የሚል ድምፅ እሰማ ይመስል አንጋጥጬ ቆየሁ!!

መኪናዬ ውስጥ ገብቼ ኪዳን ወዳለበት ቦታ መንዳት ጀመርኩ። ትናንት ከነበረበት ቤት ቀይረውታል። ከምሽቱ 3 ሰዓት የሚፈልገውን ይዤለት እንደምመጣ ስለነገርኩት እኔን ለመጠበቅ በጊዜ ከሚስትየው ጋር ወደዛው መሄዳቸውን አረጋግጫለሁ። የእሱ እቅድ ያው እንደተለመደው የራሱን ሰዎች እና መኪና ልኮ ይዘውኝ ልሄዱ ነው። እኔ ቀድሜ እዛው እንደምደርስ የሚጠረጥርበት ምንም ፍንጭ የለውም። በገዛሁት ስልክ እቤቱ ውስጥ የተጠመዱትን ካሜራዎች መቆጣጠር እችላለሁ። ሳሎኑን በሁለት አንግል፣ ኮሪደሩን እና ኪዳን ያለበትን ክፍል። ኪዳን አልጋው ላይ ኩርምት ብሎ ከመጋደሙ ውጪ ምኑም ታግቶ ያለ አይመስልም። ደጁ ላይ ጠብደል ጠባቂ ቆሟል። ለአፍታ ጎንጥን አሰብኩ> አሁን በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆኜ የእሱን አሳሳም ማሰብ ነበረብኝ? አስቤስ እጄን መሳም ነበረብኝ?
አቅራቢያው ስደርስ የጋዜጠኛው ቡድን እኩል ደረሰ። ስልኬ ላይ የማየውን እቤት ያሉት ካሜራዎች እይታ አቀበልኳቸው። እነርሱ በኮምፒውተር ፣ በተለያዩ ገመዶች ፣ ማይክራፎኖች እና ሌሎች ነገሮች በሞላው የመኪናቸው ጀርባ የሚሰካካውን ሰካክተው ዝግጁ መሆናቸውን ሲነግሩኝ መኪናችንን የአጥር በሩጋ አስጠግተን አቁመን እኔ እና አንድ ማይክራፎን የያዘ ጋዜጠኛ እና ሌሎች ሁለት ካሜራ እና ካሜራ ረዳት ወርደን ስንጠጋ ጠባቂው የያዘውን መሳሪያ ወደፊት አስቀድሞ ወደእኛ ቀረበ።

«ጋዜጠኞች ነን!! ላይቭ ነው! አቶ ደሳለኝ ስለምርጫው ትንሽ እንዲሉልን ነው!» አለው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ። ጠባቂው ምኑም አልተመቸውም። ለሌላኛው ጠባቂ መልዕክቱን ለአቶ ደሳለኝ እንዲያስተላልፍ ጮክ ብሎ ተናግሮ እኛን እንድንጠብቅ አዘዘን። ሌላኛው ጠባቂ ከደቂቃዎች በኋላ አቶ ደሳለኝን አስከትሎ ብቅ አለ።

«እኔ ከምንም ዓይነት ጋዜጠኛ ጋር ቀጠሮ አልያዝኩም!! ምን አይነት ጣጣ ነው! ሰው ማረፍ አይችልም? ደግሞ ይሄን ቤት ማን አሳያችሁ?» እያለ እየተነጫነጨ ቀና ሲል ከእኔ ጋር ተያየን። ሊቀየር ሲዳዳው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ ለካሜራ ማኑ እንዲጀምር ምልክት ሰጠው። ቀጥሎም የቴሌቭዥን ጣቢያውን ፈቃድ እያቀበለው

« አቶ ደሳለኝ ላይቭ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተከታተሎት ነው። በዚህ ምርጫ ለየት ባለ የምርጫ ቅስቀሳዎ የህዝብን ቀልብ የሳቡ ይመስላል። ወደ ውስጥ ገብተን አንድ ሁለት ነገር ቢሉን? » አለው። ግራ ተጋባ እና እየተወነባበደ ሳቅ አይሉት ስላቅ ያልለየለት ፈገግታ ፈገግ እያለ ወደውስጥ ጋበዘን። ይሄኔ ፅፌ አዘጋጅቼው የነበረውን መልዕክት ኪዳን ያለበትን ክፍል ጨምሮ ካሜራ የተገጠመባቸውን ክፍሎች ምስል ከሚያሳየው ምስልጋ ላኩለት። ስልኩ መልዕክት መቀበሉን ቢሰማም አላየውም።

«አቶ ደሳለኝ መልዕክቱ የሚያስፈልጎ መልዕክት ይመስለኛል።» አልኩት ጠጋ ብዬው። በጥፍሮቹ ቢቦጫጭረኝ ደስ እንደሚለው እያስታወቀበት የግዱን ፈገግ ብሎ ወደሳሎን እየመራን መልዕክቱን አነበበው።

« ቴሌቭዥንህን ክፈተው ካላመንከኝ ላይቭ ነህ!! ኪዳን ያለበት ክፍል ጨምሮ ኮሪደርህ እና ሳሎንህ በድብቅ ካሜራ እይታ ውስጥ ነው። የምስሉ መዳረሻ መቼም ይገባሃል የኢትዮጵያ ህዝብ አይን ነው። አርፈህ በቀጣፊ ምላስህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለህን ፍቅር እና ብትመረጥ የማታደርገውን የውሸት ቃልህን ላይቭ ዘብዝበህ የምርጫ ቅስቀሳህን ብታደርግ ይሻልሃል ወይስ ዜናውን ከምርጫ ቅስቀሳ ወደአፈና ወንጀል ብንቀይረው? ምርጫው ያንተ ነው!! ከጋዜጠኞቹ ጋር እያወራህ ወንድሜን ሳሎን አስመጣልኝ። ምንም ግርግር ሳንፈጥር ከጋዜጠኞቹ ቀደም ብዬ ውልቅ ብዬ እወጣልሃለሁ!! አይ ካልክ ግን እዚሁ ላይቭ ወንድሜን እንዳገትከው ከነምስሉ ለጋዜጠኛው ሹክ እለዋለሁ። እዛው ላይቭ ጮማ ዜና አይመስልህም? በዛ ላይ ያን የቪዲዮ ቅጂ እመርቅላቸዋለሁ።!!» እያነበበ ጋዜጠኛው ደጋግሞ ስሙን ይጠራዋል። አልሰማውም!! እንደመባነን ብሎ

«እ እ!! የሆነ ትንሽ አስቸኳይ መልዕክት ደርሶኝኮ እ!!» ተንተባተበ።
«አዝናለሁ መጥፎ ዜና ነው?» አለው ጋዜጠኛው።
«አይ እንደው ትንሽ ነገር ነው። እኔ የምልህ እና አሁን ይሄም ላይቭ እየተላለፈ ነው?» ብሎ የቴሌቭዥኑን ሪሞት አንስቶ እየከፈተ የሆነች ተንኮል ያለበት አስተያየት ወደእኔ አየ። ልቤ በመጠኑም ቢሆን መደለቅ ጀመረ። ደቂቃ እንኳን ዝንፍ ያለ ክፍተት ከተፈጠረ ሰውየው እዛ ያለነውን በሙሉ ጭጭ አድርጎ የቀደመ እቅዱን ለማሳካት የጋዜጠኞቹ ብዛትም ማንነትም የሚያሳስበው ሰው አይደለም። ጋዜጠኛው ነውም አይደለምም ሳይለው (ምክንያቱም እስከዛ ደቂቃ ድረስ ላይቭ አልነበረም) ቀጠለ። በቴሌቭዥኑ ዜና የምታቀርበዋ ሴት ስለአቶ ደሳለኝ አውርታ ስታበቃ ባልደረባዋን ጋበዘችው። ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ። መልሱም መላ ቅጡ የጠፋበት ወሬ ከመሆኑ በተጨማሪ በተቀመጠበት ላብ ያጠምቀው ጀመር። እየተንተባተበ ጥቂት እንዳወራ ሚስትየው ብቅ እንዳለች እየሆነ ባለው ነገር ግራ ተጋብታ ፍሬን ያዘች። በሚቀባጥረው ወሬ መሃል ወደሚስቱ ዞሮ «እስቲ ኪዳንን የሚጠጣ ውሃ እንዲያመጣ አድርጊልኝ! ቡናም ሻይም ሳልላችሁ በሞቴ ለእናንተስ ምን ይምጣላችሁ?» አለው ጋዜጠኛውን! ጋዜጠኛው ቀጥታ በዜና መሃል እየተላለፈ ያለ ፕሮግራም ላይ መዘለባበዱ እያናደደው ግን በጨዋ ደንብ ቀጠለ።

«በእውነቱ አቶ ደሳለኝ በዚህ አጋጣሚ ሳይዘጋጁ የመጣንቦት ቢሆንም እንግዳ ተቀባይነትዎ እና ልግስናዎ አልተለየንም። ከልብ እናመሰግናለን!! ባልደረባዬ የቀሩትን ዜናዎች ለማቅረብ እየተጠባበቀች ስለሆነ ለህዝቤ ማለት አለብኝ የሚሉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦት!! »

ጋዜጠኛውን በቅጡ የሰማው አይመስልም። ሚስቱ እንደጅብራ መገተሯ አሳስቦት በግንባሩ መልዕክት ሊያስተላልፍላት እየሞከረ ነው። እያመነታች ከሳሎኑ ስትወጣ ልቤ መደለቋን ቀጠለች። እሱም ለዚህ የፈረደበት የኢትዮጵያ ህዝብ ላቡንና ወሬውን በቲቪ ማስተላለፉን ቀጠለ። ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዙ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!!


.......... አልጨረስንም!! .........

(ዛሬ አጠረ የሚል ሰው እጋጨዋለሁ!!! 😂😂ይልቅ እያነበባችሁ ላሽ የምትሉ ልጆች እስኪ ቢያንስ ሪአክት አድርጉ። ጌታን አይቆጥርም!! ካያችሁት ውስጥ ምን ያህላችሁ እንዳነበባችሁት እንዳውቅ ነው!! ኮመንት ላይ ፊልም መሆን ነው ያለበት የምትሉኝ ልጆች ደግሞ እስኪ ገፀባህርያቱን እገሌ ቢሰራው የምትሉትን ፃፉ!! )

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ!❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሶስት)
(ሜሪ ፈለቀ)


ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዞ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!! ብርጭቆውን ተቀብዬው ለደሳለኝ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ በሁለት እጄ ሳቀብለው ጭራሽ የሚያወራው ተወነባበደበት። ጋዜጠኛው በሚሆነው ትርምስ ትዕግስቱ ነው ያለቀው። ኪዳን እየሆነ ያለው ነገር ግር ብሎት አይኑን ከወድያ ወዲህ ያንቀዋልላል። ወደጆሮው ጠጋ ብዬ «አምላክን በልመና አታድክም!! » አልኩት እና ጠቀስኩት። ፈገግ ብሎ ደረቱን እንደመንፋት አድርጎ ጎምለል እያየ ዙሪያውን መቃኘት ጀመረ። አተኩሮ ላየው የሆነ ቁራጭ የፊልም ትወና እየከወነ ነው የሚመስለው። ሁሌም እንዲህ ነው! ከልጅነታችን ጀምሮ ከልጆች ጋር ተደባድቤ እኔ ከሆንኩ ያሸነፍኩት የፀቡ መሃል ሜዳ ይገባና ደረቱን ነፍቶ ይንቀባረራል። «ማን መሰለችህ? የእኔ እህት እኮ ናት!!» ይላል እየተጀነነ።

• * * * * * * * * * * * * *

ድሮ ልጅ እያለን አባቴ እናቴ ላይ ሙድ የሚይዝበት መላው ነበር አሁን እኔ እና ኪዳን የምንግባባበት ኮድ። እናቴ ብር እጇ ላይ ቢኖርም ባይኖርም አለኝ አትለውም!! ብር ጨርሰሻል ወይ ብሎ ቀጥታ ከጠየቃት መልሷ ሁሌም አዎን ነው። በአቋራጭ ነው የሚያጣራው

«አስካል እንደው ከአባወራዎቹ ልደብለቅበት እስኪ መቀነትሽን ፈትሽልኝ!» ይላታል

«አይ እንግዲህ እንኳን ላንተ አምቡላህን መጋቻ ለልጆቼም የሚቀምሱትን ማሰናዳበት አልሞላልኝ» ትለዋለች

«ውይ በሞትኩት እናቴን! አያ ተካን አበድረኝ ልበለው ይሆን? እንደው ቸሩ መድሃንያለም ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ» ይላል ወደላይ እንደማንጋጠጥ ብሎ በአንድ አይኑ እሷን አጮልቆ እያየ እና እያስተዛዘነ (ልበደራቸው የሚላቸው ሰዎች ስም ይቀያየራል)

«አይ እንግዲህ አምላክን በልመና ማድከም ደግም አይደል!! የምንችለውን እናደራርግና በተረፈው ማመስገን ነው። ያመሰገንነው አምላክ የጎደለውን ይሞላል!» ትለዋለች ልትወጣ ነጠላዋን እላይዋ ላይ እያደረገች። አለኝም እንዳትለው ለእሱ መጠጫ መስጠት አትፈልግም። የለኝም እንዳትለው ባሏ የሰው ፊት ሊያይባት ሲሆን በዘዴ አድበስብሳ! አባቴ እሷ ዞር ስትል ጠብቆ እየሳቀ

«እም! መች አጣኋት እናታችሁን? አላት ማለት ነው! አሁን ዘንቢል ሙሉ ሸምታ ትመጣ የለ? ምንአለ በሉኝ!» ይላል። እንዳለውም ከገበያ መዓት ነገር ሸማምታ ስትመጣ አባቴ ያላትን አንነግራትም ተያይዘን እንስቃለን!!

የእውነትም እጇ ላይ ብር ከሌላት መልሷ ይለያል። የአባዬ ጥያቄ ስሞቹንና አጠያየቁን ቀይሮ ያው ነው። የመጨረሻው <ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ> የሚልበት ጋር ሲደርስ

«እንግዲህ አንድዬ ያውቃል!! እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድር!!» ካለች አባቴ አሁንም እሷ ዞር ስትል ጠብቆ

«አሁን የእውነቷን ነው የላትም ማለት ነው!!» ብሎ ከኛ ፊቱን አዙሮ ብር ይቆጥር እና « ገበያ ውረጅበት ብሎሻል! ብላችሁ ስጧት» ብሎ ለአንዳችን ያቀብለናል። ለምን እራሱ እንደማይሰጣት አሁንም ድረስ አይገባኝም!! ምናልባት ለእኛ ማስተማር የፈለገው ነገር ይኖር ይሆን ነበር። ሁሌም መልሷ እንዲሁ ነው። ሁሌም የእርሱ አጠያየቅ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ገና እሱ ሲጠይቃት በተለይ እኔ ሳቄ ይመጣል። ለእማዬ <እየፈተነሽ ነው!> አልላትም!! ለትንሿ ልቤ የእነርሱ የፍቅር ቋንቋቸው መሆኑ ገብቷት ነው መሰለኝ በተለይ የሌላት ጊዜ እሱ ሲያዝንላት ልቤ በሙቀት ቅልጥ ትላለች።

ከኪዳን ጋር ልጆች ሆነን እናታችንን የምናስታውስበት አንዱ ጨዋታችን ነበር። አድገን የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ የተነከርን ጊዜ ደግሞ ምልክት መሰጣጫችን ሆነ። ያለንበት ሁኔታ ተስፋ ያለው፣ መውጫ ያለው ፣ ደህንነታችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ከሆነ። «አምላክን በልመና አታድክሚ….. » የምትለዋ! ለምሳሌ ባለፈው ኪዳን እንዳለኝ « ደህና ነኝ አታስቢ! አልጎዱኝም!! ተረጋግተሽ መላውን ፈልጊ!» እንደማለት ነው!! ወይም ደግሞ « አንድዬ ያውቃል» ብዬ መልዕክት ካደረስኩት «እንዳትደውልልኝ፣ በምንም መንገድ ልታገኘን አትሞክር! ያለሁበት ሁኔታ ሲሪየስ ነው!!» እንደማለት ነው። እንደገባንበት ማጥ መልእክቱ ይለያያል። እኔ እና እሱ እንግባባበታለን!! በደፈናው ያለንበትን ሁኔታ አስከፊነት የምንለዋወጥበት ነው።


• * * * * * * * * *

ጋዜጠኛው ከዚህ በኋላ ላይቭ እንዳለ ሊቆይ የሚችለው ከ2 ደቂቃ አይበልጥም!! እንደየትም ብሎ ቢያራዝምልኝ ሊጨምርልኝ የሚችለው 1 ደቂቃ ነው። በዛ 2 ደቂቃ ደግሞ መኪናችን ጋር መድረስ አለብን። ለጋዜጠኛው ተጨማሪ ደቂቃ ማስረዘም ከቻለ ምልክት ሰጠሁት። ትከሻውን ሰበቀ። እሞክራለሁ እንደማለት ነገር።

«አንቺ እስከበሩ ትሸኝናለሽ እኮ!!» አልኳት ሚስትየውን። ባሏ አፉ እዛ ይለፍልፍ እንጂ አይኑም ቀልቡም እኛጋ ነው። ባይገባትም እየመራችን ወጣች። በፍጥነት ወደአጥሩ በር እየተጓዝኩ

«ልትከተሉኝ ብታስቡ! መንገዴ ላይ የሆነ ነገር ልትፈጥሩ ብትሞክሩ ውርድ ከራሴ!! ወጥተሽ ጋዜጠኞቹ መኪና ውስጥ ገብተሽ ማረጋገጥ ትችያለሽ!! አሁን ላይቭ እየተላለፈ ያለው የባልሽ ቃለመጠይቅ ብቻ ነው። አንዲት ዝንፍ ያለች ነገር አደርጋለሁ ብላችሁ ብትሞክሩ እዛ መኪና ውስጥ ያሉት ባለሞያዎች አንድ በተን ብቻ ነው መጫን የሚጠበቅባቸው። ቤትሽ እያንዳንዱ ክፍል ካሜራ አስቀምጫለሁ!! እየሆነ ያለው ነገር አሁን እኔና አንቺ የምናወራውም ምስል ሳይቀር ሪከርድድ ነው። መኪናዬ በስህተት ጎማዋ ቢቀንስ አልኩሽ ሁሉንም ምስል ገጣጥሞ ዜና ማዋቀር አይከብድምኣ? ቻው! መልካም እድል በይልኝ ባልሽን!! እም ጷ» በእጄ የመሳም ምልክት አሳይቻት ራሷ ለዘበኞቹ እንዲያሳልፉኝ ምልክት ሰጠቻቸው እና እኛ ስንወጣ

«ቱ » ብላ በንዴት እና በጥላቻ ምራቋን ስትተፋ እሰማታለሁ። እኔና ኪዳን በሩጫ መኪናችን ውስጥ ስንገባ ጋዜጠኛው የላይቭ ስርጭቱን ጨርሷል። ከአካባቢው እስክርቅ ድረስ በማይነዳ ፍጥነት እየነዳሁ ምንም ቃል ሳልተነፍስ ሸመጠጥኩት። ብዙ እርቀን እንኳን እንዳልተረጋጋሁ ያወቅኩት ኪዳን

«ሜል በፍፁም እዚህ ድረስ ሊከተሉሽ አይችሉምኮ!» ሲለኝ ነው።

«አይችሉም ብሎ ተዘናግቶ ወጥመዳቸው ውስጥ ከመውደቅ ሊሞክሩ ይችላሉ ብሎ መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው!! አታውቃቸውም እስከምን ጥግ መሄድ የሚያስችል ጭካኔ እንዳላቸው።» እጁን ሰዶ ትከሻዬን ዳሰስ ዳሰስ ሲያደርገኝ ዞሬ አየሁት። የናፍቆቴ መጠን እየሆኑ በነበሩት ክስተቶች ተከድኖ እንጂ ገደቡን የጣሰ እንደነበር የገባኝ ዓይኖቹን ሳያቸው ነው። መኪናዬን ጥጉን አስያዝኩት እና አቀፍኩት!!

«ለምን መጣህ? በዝህች ዓለም ያለኝ ብቸኛ ነገሬ አንተ መሆንህን አታውቅም? የሆነ ነገር ሆነህብኝስ ቢሆን? ሰው እንደማልሆን አታውቅም?» ቁጣም ፍቅርም እንባም ሳግም ያንቀረቅቡኝ ጀመር። ያውቀዋል ስስቴን!! ሁሌም እየተቆጣሁት ወይ እየጮህኩበት ሳለቅስ አይመልስልኝም። ስረጋጋ ነው ምክንያቱን የሚነግረኝ!!

«ይቅርታ ሜል! ይቅርታ እሺ!» አለኝ ከእኔ በላይ አጥብቆ አቅፎኝ እያባበለኝ!! መረጋጋቴን ሲያይ!!
«ብዙ ጠበቅኩሽኮ ሜል! አንድም ሶሻል ሚዲያ አካውንትሽ አክቲቭ አይደለም!! ካንቺ ሳልሰማ ብዙ የቆየሁበት ቀን 12 ቀን ነው መጀመሪያ የታሰርሽ ጊዜ!! ቢያንስ እንዳላስብ በሰው ትልኪብኝ ነበርኮ!! ቢቸግረኝ መልዕክት ላኩልሽኮ (ትዝ አለኝ! ቁጥሩ ከማይታይ ላኪ ላመስግን ወይስ ልፀልይ? የሚል መልዕክት ስልኬ ነበረው! ስላልገባኝ እንጂ!! ምንም ቢፈጠር የምደውልለት እኔ ነኝ እንጂ እሱ እንዳይደውል ህግ አለን!! ስልኩን በቃሌ ነው የማውቀው እንጂ ሴቭ አላደርገውም!!)

…… በእኔ አስችሎሽ በጤናሽ ሁለት ወር እንደማትቆዪ አውቃለሁ። እኔስ አንቺን ባጣ ሰው እንደማልሆን አታውቂም? ከዛ በላይ መጠበቅ አልችልም ነበር ትኬቴን ቆርጬ መጣሁ!! የያዝኩትን ሻንጣ የያዝኩት ሆቴል ክፍል ወርውሬ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ማንን መጠየቅ እንደነበረብኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ እቤት መሄዱ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ብዬ ክለቡጋ ሄድኩ!! መምጣቴንም እዛ መሆኔንም ማን እንደነገራቸው አላውቅም!! ከዛ ወጥቼ ታክሲ ልይዝ ስጠብቅ መጥተው በመኪናቸው ከበቡኝ!!»

«ቆይ ቆይ ቆይ (ከእቅፉ ወጣሁ!) ክለብ ማንን አገኘህ? ማንን አናገርክ? ስንት ሰዓት ነው የሄድከውስ?»

«አመሻሽ ነገር 11 ወይ 12 ሰዓት ገደማ!! ብዙ ሰው ነበርኮ እኔእንጃ!» አለኝ ግራ እየገባው።

«ከበር ጀምሮ ያናገርከውን ሰው አንድ በአንድ ንገረኝ!! ለማስታወስ ሞክር!» እያልኩት መኪናውን አስነስቼ መንዳት ጀመርኩ።

«ጋርዶቹን? መግባት አይቻልም ሰዓት ገና ነው ብለው እንቢ አሉኝ መጀመሪያ እ ….. ከዛ አንቺን ፈልጌ እንደሆነ ከካናዳ የተላከ ዕቃ ላደርስ እንደሆነ ነገርኳቸው እና ከውስጥ የሆነ ሰው ጠርተው አገናኙኝ። ከዛ ለእነርሱ የነገርኳቸውን ስነግረው ሄደሽ እንደማታውቂ …. አንድ ቀን ብቅ ብለሽ እንደነበር ነገረኝ። የግድ ማድረስ ያለብኝ እቃ አለ ስለው እሱም ገብቶ ዳዊት የሚባል ሰው ጠራልኝ። ፍቅረኛሽ መሆኑን ነገረኝ (እዚህጋ የአይመስለኝም ሽርደዳ ያለበት ፈገግታ ፈገግ ብሎ በቁም ነገር የሚያወራውን እየተከታተልኩ እንደሆነ ሲያውቅ ወደ ቁምነገሩ ተመለሰ።) እሱ ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘኝ እና ከዛ በቃ ያልታወቀ ሰው በሽጉጥ መትቶሽ እንደነበር ከዛም ድጋሚ ከሰዎች ጋር ተጣልተሽ እስከሆስፒታል የሚያደርስ ጉዳት ደርሶብሽ እንደነበር እና እቤት እንደማገኝሽ ነገረኝ።»

« ከኤርፖርት ሆቴልህ? ከሆቴልህ ክለብ? በመሃል የሄድክበት ቦታ አለ? አስታውስ? ያናገርከው ሰው? ሁለቴ የገጠመህ ሰው?»

«ሜል? እኔን ታውቂኝ የለ? ጀርባዬን እያየሁ የምሄድ ሰውኮ አይደለሁም!! ግን ማንንም አላገኘሁም!! ከዛ ውጪ የትም አልሄድኩም! ያናገረኝም ያናገርኩትም ሰው የለም ከሪሴፕሽኖቹ ውጪ!!» አለኝ ተጨንቆ

«ክለብ ውስጥ ሌላ ማን ነበር?»
«የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ!! ቤቱን እያስተካከሉ ምናምን የነበሩ እኔ እንጃ በደንብ አላስተዋልኩም ግን ሴቶችም ነበሩ!!»

«ስምህን የነገርከው ወይም የእኔ ወንድም መሆንህን የነገርከው ሰው አለ?»
«ለዳዊት! ስሜን ነግሬዋለሁ ግን ያንቺ ወንድም መሆኔን አልነገርኩትም!! ዳዊት እባላለሁ ሲለኝ ኪዳን! ብዬዋለሁ!!»

«ምን ያህል ይሆናል ውስጥ የቆየኸው?»
«እኔ እንጃ አንድ ሰዓት!! የሚጠጣ ጋብዞኝ አንድ አንድ ብርጭቆ ይዘን ነው የሆነውን የነገረኝ!! ይኸው ጀመረሽ ነገር ስትቀምሪ መሃል ቤት እኔን የምታጦዥኝ ነገርሽ!»

«ጥርጣሬ እንጂ ያረጋገጥኩት ነገር ስለሌለ ልነግርህ አልችልምኮ ኪዳንዬ! መጠጡን የጋበዘህ እሱ ነው? አልጠጣም ብለኸው ነበር? እንድትጠጣ ወተዋተህ?»

«አይ እውነትም ፍቅረኛሽ ነበር በሚገባ ነው የምታውቂው!! አዎ አልጠጣም እቸኩላለሁ ስለው። <እዚህ ድረስ መጥተህ ሳላስተናግድህ መሄድህን ሜሉ ብትሰማ ትቀየመኛለች፤ አንድ ብርጭቆ ይዘን የሆነውን ላውራህ አለኝ!!»

«ይሄ የውሻ ልጅ!! እውነት ባይሆን ነው የሚሻለው እንጂ አልለቀውም! (ይሄ ጤነኛ ንዴት ይሆን አልገባኝም! ጭንቅላቴ ከውስጥ የተወጠረ አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ የሆነ ሊፈነዳ የቀረበ ነገር። ደረቴ ላይ እልህ እና ቁጣ ከትንፋሼ ጋር እኔ ልውጣ እኔ ልቅደም ግብ ግብ የገጠሙ አይነት ስሜት) ይሄ ሙት እሱም ሰው ሆኖ መሆኑ ነው?» ኪዳን እየሆነ ያለው ግራ ገብቶት

«ሜል? እሱ ደውሎላቸው ነው የመጡት ብለሽ ነው የምታስቢው? ከአጠገቤኮ ለአፍታም ዞር አላለም ነበር። ኸረ በፍፁም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አይመስልም! ግማሹን ሰዓትኮ እንዴት እንደሚወድሽ ነው ሲነግረኝ የነበረው። ደግሞ ፍቅሩ አይኑ ላይ ያስታውቃል። ምንም ከማድረግሽ በፊት አጣሪ እህትዬ በእኔ ሞት? እ?»

«ሌባ አይኑ እና ቅቤ ምላሱ አይሸውድህ!! በእርግብ ላባ ያጌጠ እባብ ነው!! ታውቀኛለህ ደግሞ ባልተረጋገጠ ነገር ምንም አላደርግም!!» እያልኩት ስልኬን አውጥቼ ደወልኩ!!

«ሻለቃ! ሜላት ነኝ!!»
«ሜላት ሜላት?»
«አውቀኸኛል ባክህ! እንዴት አስታውሳ ደወለች ብለህ ከሆነ ግራ የተጋባኸው አዎ አስታውሼ ነው!! አደጋ የደረሰብኝ ቀን ለኤግዝቢትነት በሚል የወሰዳችሁትን ስልኬን መረጃውን ከውስጡ አፅድታችሁ እንደመለሳችሁልኝም ጭምር ነው ያስታወስኩት! ለሶስተኛ ወገን አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ ማለቴ ሸጣችሁ የግሌን መረጃ እንደነገዳችሁበትም ጭምር!! ልቀጥል?»

«ምን እንደምታወሪ ታውቂዋለሽ? ወይስ ጥይቱ ሚሞሪሽን ብቻ ሳይሆን ማሰቢያሽንም ነው የወሰደው?»

«ምን እንደማወራ አሳምረህ ታውቃለህ!! ፌስቡኬ የእኔ መሆኑን ሰይጣን እንኳን አይደርስበትም። ድንገት እኔ በተመታሁ በነጋታው 10 ዓመት ሙሉ ማን መሆኔ ሳይታወቅ የተጠቀምኩበት አካውንት በአስማት ታወቀና ዘጉት ነው የምትለኝ ያለኸው? ኦው ለምን ስልኬን እንደሚፈልጉት አልነገሩህም ማለት ነው?» ዝም አለ ለአፍታ

«የውልህ! በጣም በተቻለኝ አቅም ጥሩ ሴት ልሆን እየሞከርኩ ያለሁበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ፈጣሪህን አመስግን!! ከናንተ ጋር አውጫጭኝ የምጫወትበት ጊዜ የለኝም!! አንድ መረጃ ብቻ ነው የምፈልገው!! የመታኝን ሰው ማወቅ ነው የምፈልገው!! መሃል ከተማ ነው! አመለጠ ምናምን በሚል ተረት ተረት እኔን አትሸውደኝም!! ግማሽ መንገድ ላግዝህ? ጥቁር ጃጓር መኪና የጎማው ቸርኬ ወርቅማ ፣ ከኋላው መስታወት በቀኝ በኩል ጠርዝ ላይ ትንሽዬ ቀይ ስቲከር ያለበት፣ ታርጋ ቁጥሩ የመጨረሻ ሁለት ቁጥር 52 ነው!! እኔ ሁለት ጥይት መትቶኝ ይሄን ሁሉ መረጃ ስቶር ማድረግ ከቻልኩ ምርመራውን የያዘው ወይም ይዞ የለቀቀው ባልደረባህ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሙሉ መረጃውን ጠረጴዛህ ላይ ማኖር አይቸግረውም!! ሌላው ደግሞ ሴት ናት!! ወንድ ለመምሰል የሞከረች ሴት ናት!! መኪናው በማን ስም እንደተመዘገበ እና ሴትየዋ ማን እንደሆነች ብቻ ነው ማወቅ የምፈልገው። ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውልልሃለሁ! ከዛ ቀድመህ አሁንም ቢሆን የምትነግረኝ ነገር ካለህ ግን ዝግጁ ነኝ!!» ዝም አለኝ። ስልኩን ዘጋሁት!! እና ወደኪዳን ዞሬ

«ያረፍክበት ሆቴል ደውል እና ሻንጣህን መውሰድ እንደምትችል አረጋግጥ!! የምታርፍበት ሌላ ቦታ እንፈልጋለን። ለጊዜው እኔም ወደቤት መሄድ ያለብኝ አይመስለኝም!!»


«በእንዲህ ዓይነት ሰዓትኮ ሌላ የማላውቃት ሴት ነው የምትሆኝብኝ!! ውስጥሽ ሁለት ሴት ያለች ነው የሚመስለኝ! የእኔ ሜል እና የሌላ ሰው ሜላት! የእኔዋ እናት፣ እህት፣ ስስ ፣ የምታለቅስ ፣ የምታቅፍ ፣ የምታባብል ፣ ቀድማኝ የምትሞትልኝ …….. ያችኛዋ አያድርስ ነው!! » አለ ኪዳን በመገረም ሲያየኝ ቆይቶ!!
«መሸነፊያዬም መጀገኛዬም አንተ መሆንህን አታውቅም? ባንተ ሲመጡብኝ ነው እጅ የምሰጠውም አውሬ የምሆነውም! ያን ታውቃለህ አይደል?»

«አውቃለሁ ሜል። ግን አሁንኮ ትልቅ ሰውዬ ነኝ!! ሚስትኮ ላገባ እየተሰናዳሁ ያለው ግብዳ ሰውዬ ነኝ! እስከመቼ ነው የምትጠብቂኝ? (ዞር ብዬ ያለፉትን ቀናት እንደማስታወስ ሳየው) ይሄ የተለየ situation ነው። እንዲህ ያለ አጋጣሚ ከተፈጠረማ በድዴም ቀርቼ እንደምትደርሺልኝ አውቃለሁ። ገብቶሻል ምን ማለት እንደፈለግኩ!! መቼ ነው አንቺ የራስሽ የሆነ ህይወት የሚኖርሽ? ለእኔ ብለሽ ፣ ለአባዬ ብለሽ ወይም ለእማዬ ብለሽ የማትኖሪው። ለሜላት ብለሽ የምትኖሪው ቀን መቼ ነው? (ይሄን ሲለኝ ስለእማዬ ለካ መንገር አለብኝ። ምን ብዬ ነው የምነግረው? የሞተችዋ እናታችን ከሞት ተነሳች! ነው የምለው?) ደግሞ አባት ልሆንልሽ ነው!» ሲለኝ ስለእማዬ ያሰብኩት ጠፋብኝ። መኪናውን አቆምኩ።

«ሊንዳ እርጉዝ ናት? ስንት ወሯ ነው?» እያልኩት እሺ የአሁኑ እንባ ምን የሚሉት ነው? እንደትናንት በሚመስለኝ የቀናት ርዝመት ውስጥ እግሬ ላይ ተጠምጥሞ ትተሽኝ አትሂጂ ብሎ የሚያለቅስ ትንሽዬ ልጅ ነበርኮ!! አባቱ የሞተበት እናቱ ትታው የሄደች ቀንኮ <አባዬ ዳቦ ገዝቶ ሲመጣ ዳቦ በሻይ ነው የምበላው እንጀራ አልበላም!> ብሎ ያለቀሰ የአባቱ ሳጥን ውስጥ መቆለፍ ያልገባው ሚጢጢ ነበረ።

«ስድስት ወር ሆናት! ሴት ናት!» አለኝ እንደመኩራትም እያደረገው። ዝም አልኩ!! ዝምታዬ ውስጥ ግን ብዙ ጩኸት ነበረ። ደስ የሚል ከዛ ደግሞ የሚከፋ ስሜት እንዴት ተብሎ ይብራራል? የእኔ ኪዳን ፣ ልጄ ፣ ታናሼ ፣ ዓለሜ ፣ ብቸኛ የዓይን ማረፊያዬ አደገልኝ!! እሱ አድጎ ልጅ ሊያሳድግ ነው!! እንዲኖረው የተመኘሁለትን እና የተመኘውን ሁሉ አንድም ሳይጎድልበት አግኝቷል። በህይወቴ ትልቁ ድሌ እና ስኬቴ እኮ እሱ ነው!! ከዛ ግን ለምን የመከፋት ስሜት ተሰማኝ? ለእሱ ደስ አለኝ ለእኔ ግን ከፋኝ። የሆነ እዝህች ምድር ላይ ለመኖር የመጣሁበትን ዓላማ የጨረስኩ ፤ የምኖርለት ምክንያት ምንም ያልቀረኝ ፤ ከዚህ በኋላ እኔ የማላስፈልገው ፤ የራቀኝ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ይሄን ግን ለእርሱ ልነግረው አልፈለግኩም። ደስታው ትንሽ እንኳን እንዲደበዝዝበት አልፈልግም!! አቅፌው እንባዬን እየጠረግኩ ደስ እንዳለኝ ነግሬው መኪናዬን መንዳት ጀመርኩ። ሆቴሉ ደውለን ሪሴፕሽን እቃውን እንዲያስቀምጡልን አድርገን። የሚከፋፈለውን ከፍለን ሻንጣውን ወሰድን። ለአፍታም ቢሆን ከእኔ እይታ ዘወር እንዲል ስላልፈለግኩ ሆቴል ከመያዛችን በፊት ጎንጥን ለማየት ወደሆስፒታል ነዳሁ።

«የእኔ ኪዳን? አውቃለሁ ታጥበህ ልብስ ለመቀየር እንደቸኩልክ!! ለትንሽ ደቂቃ ሆስፒታል የሆነ ሰው ጠይቀን እንመለስ እና ደግሞም የምነግርህ ትልቅ ነገር አለ።» አልኩት በመንገዳችን።

«ምንድነው እሱ? የምነግርህ ትልቅ ነገር ስትዪ ሁሌም የሚከተለው ደስ የማይል ነው!! ምንድነው እሱ? ምን ልታደርጊ ነው? ደህና ነሽ አንቺኣ?»

«ኸረ ጭራሽ እንደሱ አይነት ነገር አይደለም!! እንደውም ደስ የሚል ነው መሰለኝ! ቢያንስ በግማሽ!»

ጎንጥ የተኛበት ክፍል ስንገባ ትንፋሹን ሰብስቦ የሆነ መርዶ እየጠበቀ ያለ ይመስል ነበር። ከሆዱ ድረስ ትንፋሹን ስቦ በረጅሙ የመገላገል ዓይነት ተነፈሰ እና ፈገግ አለ።

«ነፍሴን እኮ አወክሻት ዓለሜ? ከቤቱ ወጣች ካሉኝ ቆየ!! ስትዘገዪ ከመንገድ ምን አገኘሽ ብዬ ነፍሴ ከስጋዬ ልትለይ?» አለ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር መልስ ባልጠበቀ ጥያቄ ዓይነት አስረዝሞ!! ማለት የፈለግኩት የነበረው <ልቤንኮ በረደኝ! እጄን ያዘኝ! ጦሽ ብዬ ላልቅስና! ኸረ በመድሃንያለም ነፍሴን አታስጨንቂያት! እያልክ አባብለኝ!> ነው። ያልኩት ግን «የኪዳንን ሻንጣ ልናመጣ በዛው ሄድን! ይቅርታ ቢያንስ መልዕክት እንኳን መላክ ነበረብኝ!»

ኪዳን አንዴ እኔን አንዴ እሱን <እየሆነ ያለውን ነገር አንዳችሁ ትነግሩኝ?> በሚል አስተያየት ያየናል።


.......... አልጨረስንም ..........

(ከዛ ግን በሞቴ ትናንት ሜላትን አንቺi ብትሰሪያት ብላችሁ ሙድ የያዛችሁት ግን ግፍ አትፈሩም? ወይስ እንደው ፎቶዎቼን እንኳን አላያችሁም? ለራሴ ከሽጉጥ ትንሽ ከፍ የምል አንድ ፍሬ ሴትዮ ሽጉጥ ይዤ ስታኮስ አስባችሁኛል? ደግሞኮ ክላሽንኮቭም ትይዛለች። በቁመትም በክብደትም ታላቄ ነው የሚሆነው እሱ ደግሞ!! ተውኣ!! 😂😂)

በተረፈው ውብ ሰንበት ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ ❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አራት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«ጓደኛዬ ነው!! ትናንት አንተን ትተን ስንወጣ ተከትለውን ነበር።» ብዬ ሆስፒታል የመተኛቱን ሚስጥር አብራራሁ ጎንጥን ምኔ ነው ብዬ ማስተዋወቅ እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ ማቅረቤ ይሁን ማራቄ ልኬቱን እንጃ!! ወዲያው ግን ስም ሲለዋወጡ በስሙ ያውቀዋል እና ኪዳን ዞሮ አየኝ! <ጎንጥ ይሄ እኔ የማውቀው ጎንጤ?> ዓይነት አስተያየት! ምንም እንዳይጠይቀኝ በልምምጥ ሳየው እኔን ተወኝ! ከዛ ግን ወንበር ስቦ ጎንጥ ፊት ተቀምጦ አንዱን ጥያቄ ከሌላው እያስከተለ ይደራርብ ጀመር።

«ቤተሰብ አለህ? ማለቴ የራስህ ሚስትና ልጆች? አዲስአበባ ከመጣህ ቆየህ? ሜልጋ ሳትሰራ በፊት ምንድነበር የምትሰራው? ሴት ጓደኞችህን ሁሉ <ዓለሜ> ብለህ አትጠራም መቼም አይደል? ስራህ ስለሆነ ነው ወይስ ሜል ስለሆነች ነው (በአገጩ የተመታውን ጠቆመው) ከዳንክ በኋላ ….. »

«ኪዳን?» አልኩኝ በልመና መጠየቁን እንዲያቆም ….. በአንድ በኩል ግን መልሳቸውን ልሰማቸው የምፈልጋቸው ጥያቄዎች መሆናቸው ለጎንጥ መልስ እንድጓጓ አደረገኝ። የእውነት ከዳነ በኋላስ?

«ሴት ልጅ አለችኝ!» የሚለውን ብቻ ነው ከዚህ ሁሉ ጥያቄ ፈገግ እያለ መርጦ የመለሰው። ኪዳን ሌላውን ጥያቄ እንዲመልስለት አንገቱን አስግጎ ጠብቆ ዝም ሲለው

«come on!» አለ

«መሽቶም የለ? ሂዱና ጎናችሁን አሳርፉ!! » ሲል ነው ጎኔ አልጋ ከነካ 48 ሰዓት እንዳለፈው ትዝ ያለኝ።

«እርግጠኛ ነህ ብቻህን ምንም አትሆንም?»

«ምንም አልሆን አልኩሽ እኮ!!» ያለበት ድምፅ <ዓለሜ> እንደሚለው ያለ ማባበል አለው ነገር? ወይም መስሎኝ ነው 48 ሰዓት ያልተኛ ሰው ብዙ ያልተባለ ነገር የመስማት እድሉ ከፍተኛ ነው።

ይሄን ካለ በኋላ ለሆነ ደቂቃ የሆነ ያልተለመደ ዓይነት ዝምታ ተፈጠረ። ቻው ብዬው መውጣት እፈልጋለሁ ግን የአልጋው ግርጌጋ እንደተገተርኩ ነው። ልቤና እግሬ ተጣሉብኝ!! እንድሄድ እየጠበቀ ነው ግን በዓይኖቹ እንድቆይለት እያባበለኝ ነው ወይም መሰለኝ። በእንደዛ ዓይነት ፖዝ ፎቶ አንሺ ያስቆመኝ ነው የምመስለው።

«እኔ የምለው? እኔኮ ብቻዬን ማደር እችላለሁ! አንቺ ለምን እዚህ አትቆዪም?» የሚለው የኪዳን ንግግር ነው እኩል ሁለታችንንም እንደመባነን ያደረገን

«አይሆንም!» አልን ሁለታችንም በአንድ ድምፅ ግንኮ አሁንም ኪዳንን ያየው የለም እኔና እሱ ዓይናችን አልተፋታም! ከዛ ደግሞ ራሴው አይሆንም ያልኩትን እሱም አይሆንም ማለቱ ለምን ከፋኝ?

«እህእ? ወይ ሶስታችንም እዚሁ እንደር?» አለ ኪዳን ሳቅ እያፈነው። አሁን ሁለታችንም አየነው። ስንወጣ ሲያበሽቀኝ እንደሚያድር አውቃለሁ።

«ደግ! በሉ ቸር እደሩ!! ትከሻሽን መገላመጥ አትዘንጊ!» አለ በቃ ተሰናብቼሻለሁ ሂጂ እንደማለት ነገር ከነበረበት በቀስታ ዘወር እያለ።

«የምትባባሉትን ተባባሉ በሩጋ ነኝ!» ብሎ ኪዳን ወጣ!! ምን እንደሚባል የማውቀው የለኝም!! ማለት የምፈልገው መኖሩንም እንጃ! ካለሁበት ተንቀሳቅሼ ልቀርበው ፈልጌ ማፈር ነው ግራ መጋባት የማላውቀው ስሜት ጨመደደኝ። ጭንቅላቴም ልቤም ሰውነቴም ተባብረውብኝ ማድረግ የምሻው ብቸኛ ነገርኮ እሱን መንካት ነው። እንዲህ ሆኖ የሚያውቅ ሰው ኖሮ ያውቅ ይሆን አላውቅም! ገብቶት ነው መሰለኝ ወይም እሱም እንደእኔ አካላቶቹ አምፀውበት ሊነካኝ ፈልጎ እጁን እንድይዘው ዘረጋልኝ። ከረሜላ አይቶ ሲቁለጨለጭ ምራቁ አፉ ውስጥ ሞልቶ ወደ ጎሮሮው ሲደፍቅበት ቆይቶ ከረሜላውን እንደሰጡት ህፃን በአንድ እርምጃ ዘልዬ እጁን ያዝኩት። እጁን እጄ ላይ ከማጫወቱ ውጪ በቃላት አላወራኝም። በዓይኖቹ የሚያወራው ደግሞ ትርጉሙ እኔ እንደምፈታው ይሆን ሌላ እየገባኝ አይደለም። <የዓይን ቋንቋ እንደፈቺው ነው!>

«ከዳንክ በኋላስ?» አልኩት ለሚመልስልኝ መልስ ሳልዘጋጅ

«አላውቅም!» አለኝ ከአይኔ ውስጥ ቆፍሮ የሚያወጣው ስሜት ያለ ይመስል በአይኑ አይኔ ውስጥ እየቆፈረ። መልሱ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠበቅኩት ነገር ስላልነበረ አልከፋኝም! እሙ እንዳለችው ከመጃጃልም በላይ እየሆንኩ እንደሆነ የገባኝ ከ<አላውቅም> አስከትሎ <ዓለሜ> አለማለቱ ከፋኝ! አንዴ አለሜ በለኝ ብለው ሆዱን ይዞ አይስቅብኝም? ይባላልስ?

«አንቺ ምንድነው የምትፈልጊው?» አለኝ

«አላውቅም! ምን እንደምፈልግ አላውቅም!» አለ አፌ! የምፈልግ የነበረው ግን ዓለሜ እንዲለኝ ፣ የምፈልግ የነበረው እንደቀኑ የእጄን መዳፍ መሃሉን እንዲስምልኝ፣ እምፈልግ የነበረውማ ለአንዴ በህይወቴ ጀግና ጀግና የማልጫወትበት ሰው እንዲሆነኝ ……. ለአንዴ ብቻ ፍርሃቴን ፣ ድክመቴን ፣ ማፈሬን ፣ ሽንፈቴን ፣ …. ከእንባዬ ጋር ለውሼ ደረቱ ላይ እንድተነፍሰው በክንዱ ደግፎ ደረቱ ላይ እንዲያቅፈኝ ….. እፈልግ የነበረውማ ይሄ ያልኩት ሁሉ ሲሆን ዘመናት ቢቆጠሩ ነበር። ቀጥዬ ያልኩት ግን

«ኪዳን አባት ሊሆን ነው!» የሚለውን ነው! ሳልፈልግ ድምፄ ውስጥ መከፋቴ ተሰማብኝ። የያዘውን እጄን ስቦ ወደደረቱ አስጠግቶ ደረቱ ላይ አጥብቆ ያዘው። ይሄ ሰውዬማ ከእጄጋር የሆነ ነገር አለው! ነውስ እጄና ልቤ የሚያገናኛቸው ነገር አለ እጄን የሆነ ነገር ሲያደርገኝ ልቤ አብሮ የሚያሸበሽበው?
«ዳር የተተውሽ መሰለሽ?» ሲለኝ እንባዬ ታገለኝ!! ነግሬዋለሁ? አልነገርኩትም! የተሰማኝን በልከኛው ቃል እንዴት ማስቀመጥ ቻለበት? አንዲት ፊደል ከአፌ ቢወጣ እንባዬ እንደሚያጅበው ስለገባኝ ዓይኖቹን ሸሽቼ ዝም አልኩ። ደረቱ ላይ የያዘውን እጄን እዛው ትቶት በእጁ አገጬን ደግፎ ዓይኖቹን እንዳያቸው አደረገኝ።

«መቼም ቢሆን በምንም የማይተካሽ እህቱ ነሽ!! ሚሽትና ልጁ ያንቺን ቦታ አይጋፉም!! ኪዳንን በዚህ ሁሉ መዓት ፍቅር ስትወጂ ልብሽ ጠቦሽ አባትሽን አስወጥተሻል? ወይሳ እናትሽን? እኔን ወደልብሽ ስታስገቢስ ልብሽ አልበቃ ብሎ ከኪዳን ፍቅር አጎደልሽ? የእርሱን ቦታ ቀነስሽ?»

«አይ!!» ብዬ ጭንቅላቴን በአሉታ ከነቀነቅኩ በኋላ ነውኮ መጨረሻ ላይ ያለውን ለራሴ ደግሜ ስሰማው ዓይኔን የማሳርፍበት የጠፋኝ። ጥሩ እየሰማሁት ነበርኮ ከመጨረሻው እሱን ልቤ ካስገባበት ዓረፍተ ነገር በፊት! <አይ> ያልኩት ምንድነው ቆይ? የኪዳንን ፍቅር ሳታጎድል ነው ልቤ የገባኸው ነው አይደል ያልኩት? የጥያቄው መልስ እንደተመለሰለት ፈገግ ብሎ አገጬ ላይ አውራ ጣቱን አሸት አሸት ነገር አድርጎ እጁን ደረቱ ላይ ወደተወው እጄ መልሶ እንደቅድሙ አጥብቆ ደረቱ ላይ ያዘው።

«ያልኩት ሀቅ አለው?» ብሎ አወነባበደብኝ። ምናለ ዝም ቢለኝ ገብቶት የለ?
«ምኑ?»
«ከልብሽ ገብቻለሁ?»
«አዎ! መሰለኝ! እኔ እንጃ አላውቅም! በምን አውቃለሁ?» በዚህ ነፋሻማ አየር እንዲህ ሊሞቀኝ ይገባ ነበር? ስፈራ ጉልበቴን እንደቁርጥማት እንደሚያደርገኝ ነገር አሁን ሊሰማኝ ይገባ ነበር? ሳቅ እንደማለት ነገር ብሎ

«በይ ተነሽ ሂጅ አሁን እየጠበቀሽ ነው!!» ብሎ እጄን አንስቶ አገላብጦ ይስመው ጀመር!! አንዴ ሁለቴ ሶስቴ ….. ሁለቴ አይበሉባውን አንዴ ወይም ሶስቴ መሃል እጄን….. እኔ እንጃ አንድ አራቴ ጎኑን ….. ጣቶቼን …… ከመጀመሪያው በኋላ እንኳን ቁጥሩን ላውቀው እንደባለፈው ራሴንም አለመዘንጋቴ በቸርነቱ ነው። ከዛ ነገና ዛሬዬን ከደባለቀብኝ በኋላማ ምንም እንዳልሆነ ነገር እጄን መለሰልኝ። ማድረግ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር። ግን ለመሄድ ተነሳሁ እና ወደበሩ መንገድ ጀመርኩ። ልቤማ ደረቴ ውስጥ የለችም! እንጂ ሰውነቴ እንዲህ ወደኋላ ባልጎተተኝ። በሩጋ ደርሼ ዘወር አልኩና

«ነገ እኮ እማዬጋ ልሄድ እችል ይሆናል።» አልኩት ለምን እንዳልኩት ሁሉ እኔ እንጃ! ምናልባት አንድ ደቂቃ እሱጋ መቆያ ምክንያት እየፈለግኩ መሰለኝ።

«ደግ!!» ብቻ ነው ያለው!! እንዴ? ምንድነው ሰው ማግዶ እሪሪሪ እስኪሉ መጠበቅ? ኮስተር እንዳልኩ ለራሴ እየታወቀኝ በሩን ይዤ ቆምኩ!

«ምነው ዓለሜ? የምትነግሪኝ አለሽ እንዴ?» ሲል ከንፈሬ ሳላዘው ሸሽቶ ያለኝ ጥርስ ሁሉ ንፋስ ዳበሰው

«ምንም የለም! ደህና እደር በቃ!» ብዬው ወጣሁ። መኪናው ጋር እስክንደርስ ከኪዳን ጋር ምንም ቃል አልተለዋወጥንም! መጣሁ መጣሁ እያለ እየተናነቀው እንደሆነ ያስታውቅበታል።

«ትከሻሽን መገላመጡን አትርሽ ዓለሜ!» አለ መጨረሻ ላይ ከት ብሎ እየሳቀ

«አፍህን ዝጋ እሺ!! አንድ ነገር እንዳትለኝ!» አልኩት ሳቅም ማፈርም በደባለቀው ቁጣ

«ጀግና ነው ግን ሜል ሙች!! ይፈርምልኝ! ጠባቂ ሆኖ ገብቶ ጠብ ያድርግልኝ? ሜል ገና ስታይው ፍስስ እኮ ነው ያልሽው!»

«ኪዳን ተወኝ አልኩ እኮ!»

«አንዴማ ጨብጬው ልምጣ ሜል ሙች» ብሎ ወደኋላው እንደመመለስ አለ

«ባክህ አርፈህ መኪና ውስጥ ግባ አትጨማለቅ!!»

የማውቀው ገስትሀውስ ደውዬ አልጋ ያዝኩ። መንገዱን ሁሉ ሲያበሽቀኝ እና ሲገረም ዘለቅነው «ምን አባቱ አድርጎሽ ነው ግን ስንቱን ወንድ ያሸና ልብሽን ዘጭ ያደረገው? ፣ እኔንኮ እዛ እንደሌለሁ ረሳችሁኝ ሆ! ፣ እድሜ ደጉ ሜል ስትሽኮረመም ያሳየኝ? ፣ ፍቅር በሀገርኛ ግን ጆሮ ላይ ደስ ይላል አንቺ? ነፍሴን አወክሻትኮ ዓለሜ! ነው ያለው? > አያቆምም ይለፈልፋል። በመሃል

«ሜል ሻምበሉጋ ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውላለሁ ካልሽው ሁለት ሰዓት አለፈ!» ሲለኝ ሰዓቴን አየሁት። መርሳቴ እኔንም ኪዳንንም ገረመን!! አንድ ሰው እንዲህ የሰውን ሀሳብ መቆጣጠር ይችላል?

«እኩለለሊት ሊሆን ነው!! ጠዋት ብደውል ይሻላል!!» ስለው ኪዳን አይኑን ጎልጎሎ አውጥቶ አፈጠጠብኝ

«you know am happy for you!! ሜል ነገር አሳደረች? ያውም ሊገድላት የሚከረ ሰው ? ፍቅር ግን ደስ ሲል!!»

«ለምንድነው ግን አፍህን የማትዘጋው?»

ለሁለት ደቂቃ ዝም ይልና ደግሞ ይጀምረኛል። ማረፊያችን ደርሰን የምናወራው ቁምነገር መኖሩን ተኮሳትሬ እስክነግረው ማብሸቁን አላቆመም!!

«አሁን የምር አስጨነቅሽኝ! ምንድነው ንገሪኝ!!» አለኝ አጠገቤ አልጋው ላይ እየተቀመጠ አንድ እጁን እንደማቀፍ ትከሻዬ ላይ ጣል እያደረገ

«እማዬ አልሞተችም! በህይወት አለች!! እና ልታይህ ትፈልጋለች!»

«ማለት?» ብሎ እጁን ከትከሻዬ ላይ አነሳው

«በሰዓቱ ላንተ እውነቱን መንገር ከምትሸከመው በላይ ስለሚሆንብህ ነው ከአጎቴ ጋር ተነጋግረን እንደሞተች የነገርንህ! ታዲያ የታለች ብትለን ኖሮ መልስ አልነበረንም!»

«እና የት ነበረች?» ብሎ ስፈራው እና ስሸሸው የኖርኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ። እንዴት ብዬ እንደምነግረው ስጨነቅ

«ሜል ያኔ ህፃን ስለነበርኩ ነው የዋሸሽኝ አሁን ግን ትልቅ ሰው ነኝ ንገሪኝ!!» ብሎ ሲሆን አይቼ እንደማላውቀው ተኮሳተረ። የዛን ቀን ያየሁትን ነገር በሙሉ ነገርኩት። እየጠበቅኩ የነበረው የሚናደድ ወይ ሌላ ጥያቄ የሚያስከትል ነበር። እሱ ግን መጥቶ እያቀፈኝ

«አንቺምኮ ይሄን ሁሉ ብቻሽን የምትሸከሚበት እድሜ ላይ አልነበርሽም!!» አለኝ። ቀጥሎ ግን «አንቺ ትታን ስለሄደች አላዘንሽባትምኣ?» ብሎ ያላሰብኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ።

«አላውቅም የኔ ኪዳን! ልጅ እያለን ብዙ ጊዜ ተናድጄባት አውቃለሁ። የምናደደው ግን ትታኝ ከመሄዷ በላይ ካየሁት ነገር በላይ እናትነቷን እንደማይላት እንዴት አልተረዳችልኝም ብዬ ነው! ከውርደቷ በላይ ፍቅሯ እንደሚገዝፍብኝ እንዴት ማሰብ አትችልም ብዬ ነው። ከዛ ግን የዛን ቀን ዓይኗ ውስጥ ያየሁት ህመሟ ከምናደድበት ይበልጥብኝና አንድ ቀን አጊንቻት ባቅፋት ነበር የምመኝ የነበረው»

«እሺ አገኛታለሁ!! ላገኛት ፈልጋለሁ!!» አለኝ።

«ታማለች ኪዳንዬ" አልኩት!እናቱን የማግኘት ተስፋ እንደሰጠሁት ትዝ ሲለኝ ብዙ ከማለሙ በፊት እየተሽቀዳደምኩ ይመስል ተቅለብልቤ

«ታማለች ማለት? የከፋ?»

«አዎን!! ታውቃለህ ለበደሌ እየቀጣኝ ሁሉ መስሎ ተሰምቶኝ ያውቃል! ዓይኗን ደግሜ ባየው ብዬ ዘመኔን የተመኘሁላት እናቴን በመጨረሻ ሳገኛት ለሞቷ ቀናት እየቆጠረች ሆነ።» ከዚህ በኋላ ለረዥም ሰዓት ዝም ተባባልን!! በቃ ዝም! የዛለው ሰውነቴ የተቀመጥኩበት ወደቀ። እግሬን ወደላይ ሰብስቤ ተጋደምኩ።
የነቃሁት የቧንቧ ውሃ ሲወርድ ሰምቼ ነው። ኪዳን ቀድሞኝ ነቅቷል ወይም አልተኛም! አልጋው ጫፍ ላይ እንቅልፍ እንደወሰደኝ ልብስ ደርቦልኛል። ምናልባት እንቅልፍ አልወስድ ብሎት የነበረ ይሆን ብዬ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። በደቂቃዎች ውስጥ እናትህ አለችም ልትሞትም ነው የሚል መርዶ አርድቼው እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ አደርኩ። እናቴን አግኝቻት ልትሞት መሆኑን ሳውቅ ለወራት መቀበል አቅቶኝ የሆንኩትን መሆን አስቤ ያጠፋሁ መሰለኝ። ብቅ ሲል

«ይቅርታ ቀሰቀስኩሽ እንዴ?» አለኝ

«ነግቶ የለ! ምነው እንቅልፍ አልወሰደህም እንዴ?»

«አይ ተኝቻለሁ!» ይበለኝ እንጄ የእኔን ኪዳን መች አጣሁት እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር ነው ያደረው። አስር ጊዜ <ደህና ነህ> እለዋለሁ። <ደህና ነኝ> ይለኛል።

«ማውራት ትፈልጋለህ ኪዳንዬ?»

«አልፈልግም! ዝም ብለን እንሂድ!» አለኝ።

ከመሄዴ በፊት ብዙ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩኝ። ሆስፒታል ሄጄ ጎንጥን ማየት። ሻለቃው ጋር መደወል፣ ሴትየዋ ማን መሆኗን አውቄ ማግኘት….. ብዙ!! ከኪዳን የሚበልጥ ነገር የለኝም አይደል? እሱ እንዲህ በዝምታ ተለጉሞ የሚሰማውን እንኳን ሳላውቅ ራሴን ማስቀደም አልሆንልሽ አለኝ!! ክፍላችን የመጣውን ቁርስ እንደነገሩ እየለኳኮፍን መኪና ስፈልግ የሚያዘጋጅልኝ ሰው ጋር ደውዬ መኪና እንዲያመጣልኝ ካደረግኩ በኋላ የዳዊትን መኪና ሌላ ቦታ ወስዶ እንዲያቆምልኝ አደረግኩ። ለዳዊት ደውዬ መኪናውን ከቆመበት እንዲወስድ ስነግረው ምንም እንዳልጠረጠርኩ ለመምሰል ከራሴ ታገልኩ። መንገድ ከጀመርን በኋላ ሻንበሉ ደወለ። የመኪናው ባለቤት እና ልትገድለኝ የሞከረችው ሴት የተለያዩ ናቸው። ግን ሁለቱም በስማቸው የማውቃቸው አይደሉም!!

«ቢሮ ብቅ ካልሽ የሁለቱንም ፎቶ ላሳይሽ እችላለሁ!!» ብሎ ስልኩን ዘጋው!! መልዕክቱ አንድም ለመላክ አላምንሽም ነው ሁለትም ፎቶውን ለማየት ተጨማሪ ዋጋ አለው ነው። ስልኩን ዘግቼ ዝም አልኩ! ኪዳንም ምንም አልጠየቀኝም!! ዝምታው አስጨነቀኝ!! ልቤ ድንጋይ የተጫነበት እስኪመስለን ድረስ እንደከበደኝ ተጉዘን ከሰዓታት በኋላ እነእማዬጋ ደረስን!! አጎቴ ከበር እንደተቀበለን ኪዳንን እያገላበጠ ስሞ አልጠግብ አለው!!

«አቤት አንተ መድሃንያለም ምን ይሳንሃል!! አስካል ልጅሽ መጣልሽ!» እያላት ወደ ውስጥ ገባ!! እማዬ ለመነሳት በዛለ ጉልበቷ ተፍጨረጨረች። ከሁለት ቀን በፊት ካየኋት በላይ ገርጥታለች። ይብሱን የከሳችም መሰለኝ። ዝም እንዳባባሉ ፣ እንደማታው አጠያየቁ ከኪዳን ጋር ሲተያዩ አሁን የሚሆኑትን የሚሆኑ አይመስልም ነበር። ጉልበቷን አቅፎ ተንሰቀሰቀ። ፀጉሩን እየደባበሰች ተንፈቀፈቀች። እኔና አጎቴ የሁለቱን መሆን እያየን ስንነፋረቅ ቆይተን! አጎቴ ፊቱ ላይ የተዝረከረከ እንባውን ጠራርጎ ሲያበቃ ደግሞ እንዳላለቀሰ ሰው ኮስተር ብሎ

«አይ ደግም አይደል የምን ለቅሶ ነው?» አላለም?

............ አልጨረስንም!! ..............
(ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ ❤️❤️❤️❤️)
እንዴት አደርን ቤተሰብ♥️♥️♥️ ዛሬ በጣም በጠዋት የምከውናት ስራ ስላለችኝ ከ8 ሰዓት በፊት የማደርስላችሁ አይመስለኝም!!! ልክ 8 ሰዓት ላይ ክፈቱ... እንደውሃ ቀጂ ከምትመላለሱብኝ ብዬ ነው!!! የዛሬው የቆመበት ቦታ ደግሞ ቢያንስ ልብ የሚሰቅል አይደለም::

በነገራችሁ ላይ እስከአሁን ያነበባችሁት በA4 ወረቀት 75 ገፅ መሆኑን ታውቃላችሁ??? በመፅሃፍ ገፅ ቢዘጋጅ 150 ገፅ ይሆናል!!!... already..መጠነኛ መፅሃፍ ፅፈናል🤣🤣🤣 በየቀኑ ያለ ኢዲት ከመፃፋችን ውጪ ....

በነገራችሁ ላይ am really thankful ስለጨዋ እና ምርጥ ተከታዮቼ... 🙏🏽🙏🏽🙏🏽🙏🏽

ምንም ያህል በየቀኑ መፃፍ የሚያደክም ቢሆንም ደስ እያለኝ ነው የማደርገው.... ኮመንታችሁን ሳነብ እየሳቅኩ... እየተገረምኩ .... ለነገ የተሻለ ልፅፍላችሁ እየበረታሁ ነው ቀኔ የሚያልፈው!!

ሁሌ ስለሚሳደብ ሰው ስነጫነጭ የናንተን ፍቅርና ክብር ቦታ ያልሰጠሁ እንዳይመስልብኝ!! ...

ወከባ በበዛበት የሳይበር ዘመን ሀያ ምናምን ክፍል ድረስ የሚዘልቅ ፅሁፍ በጉጉት የምታነቡ ምርጥዬ ተከታዮች ማፍራት መታደል ነውኮ!!! በብዙ ያክብርልኝ!!!

በኃላ ከነጎንጥጋ ደግሞ እንገናኝ❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

ብዙ ነገር አጥቼ እንደነበር የተሰማኝ አሁን ላይ ነው። የእማዬን አልጋ ከበን ቡና ተፈልቶ ቆሎ እየቆረጠምን አንዱን ወሬ ስናነሳ አንዱን ስንጥል በብዙ ሳቅ እና ደግሞ በደስታ ለቅሶ የታጀበ ቀን እየዋልን ያለፉ አመታቴን አስቤ ብዙ እንደጎደለኝ ገባኝ።

ደግሞ በዚህ ሁሉ የቤተሰብ ፍቅር ታቅፌ ልቤ ክንፍ አውጥታ ጎንጥ ጋር ስትሄድ፣ የያዘኝን አያያዝ ፣ የሳመኝን መሳም ፣ የጠራኝን መጥራት አሰብ አድርጌ ብቻዬን ፈገግ ስል ባለፉት ዓመታቶቼ ብዙ እንዳለፈኝ ገባኝ። ብዙ እንዳልኖርኩ ገባኝ!!

«እትዬ ዛሬ ሌላ ሰው ሆነው በንፁህ ልብ ስለተቀበሉት ነው የሚያጎብጥ ሸክም የሆነብዎት። ቂም ባቄመና በጠለሸ ልብ ሆነው ሲቀበሉት እንዲህ አልተሰማዎት ይሆናል።» ነበር ያለው ጎንጥ እንዴት ይሄን ሁሉ ጥላቻ ተሸክሜ ኖርኩ ስለው?
በንፁህ ልብ አይደለም። በፍቅር ልብ ሳየው ነው ዓለምን እና ዙሪያዬን የማይበት መነፅር የተቀየረው። በፍቅር ዓይን!! ሁሉ እንዳለኝ የተሰማኝ፣ መኖር ደስ የሚል ነገር መሆኑን ማሰብ የጀመርኩት በፍቅር ልቤ ማየት ስጀምር ነው።

እናቴን አቀፍኳት፣ ኪዳንዬ አለኝ፣ አጎቴን አለኝ፣ ጎንጥ ይኑረኝ አይኑረኝ ባላውቅም አዎ በልቤ ውስጥ ግን ከነጥጋቡ አለኝ!! ምን እጠይቃለሁ ሌላ? አጎቴ እናታችን ስለደከመች ካጠገቧ ባንርቅ መልካም መሆኑን ስለነገረን በአካሌ ላለመሄድ ወሰንኩ። ግን ልትሞት ቀናት የቀራት እናቴን አቅፌ ልቤ አዲስአበባ መሸምጠጡ ራስወዳድነት ነው? እንደዛ እየተሰማኝኮ ራሴን እገስፃለሁ። ልቤ አልሰማኝ አለኝ እንጂ!!


የገባን ቀን ማታ ምናልባት ለጥንቃቄ በሚል። በኪዳን ስልክ ዋትሳፕ መልዕክት ላኩለት። ሁለት መስመር ለመፃፍ ከ20 ደቂቃ በላይ ፈጀብኝ። ለኪዳን ካልሆነ በቀር ፅፌ የማውቀው ማስፈራሪያ ወይ ቢዝነስ ነክ ነገር አልያም የሆነ መልእክት እንጂ ፍቅር ነክ ነገር እንዴት እንደሚፃፍ አላውቅም። ምን ተብሎ ነው የሚጀመረውስ? ሀይ ጎንጥ? ስሙ ደግሞ ሲጠራ ምንም የፍቅር ቅላፄ የለውም!! እንዴት ዋልክ ዓለሜ? ልበለው? አይሆንም እሱ ሲል ነው እንደሱ የሚያምርበት! ሀኒ ልበለው? ሆ ጎንጥን ሀኒ? ራሴኑ አሳቀኝ!! ያቺ የድሮ ሚስቱ እንደጠራችው ጎኔ ልበለው? ኡፍፍፍ

«ሰላም ዋልክ? እኔ ነኝ!! በጠዋት ላይህ ሳልችል ቀርቼ እማዬጋ መጥቻለሁ!! ደህና አድረህ ዋልክ?» በቃ መፃፍ የቻልኩት ይሄን ብቻ ነው። ምን አይነቷ ነፈዝ ነኝ በፈጣሪ!! ከዛማ ስልኩን አቅፌ የፃፍኩለት መልዕክት ሰማያዊ የራይት ምልክት እስኪያሳየኝ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።

«ዓለሜ ናፈቀሽ እንዴ?» ይለኛል ኪዳን ሲያበሽቀኝ

«ለምን ግን አታርፍም?» እላለሁ

«ጎንጤን ነው?» ይላል አጎቴ

«እንዴ? እኔ ብቻ ነኝ የማላውቀው ማለት ነው? አንደኛውን ሽማግሌ ልኳል አትይኝም እንዴ?»

«እዚህ ከርሞ አይደል እንዴ የሄደው? ዓይነውሃው ያስታውቃልኮ ፍቅር እንዳለበት! መች አይኑን ከርሷ ላይ አንስቶ! <ጎንጤ እርሻ ወረድ ብለን እንምጣ ?> ብለው <አይ ጋሼ ከርሷ ባልርቅ ነው የሚሻል። ደህና መሆኗን ማየት አለብኝ> ይለኛል። <እንደው ታች ሰፈር ደረስ ብለን ብንመጣስ?> ብለው <ይቅርታ ጋሼ ዛሬ ልክም አይደለች ርቄ አልሄድ> ይለኛል። ኋላማ <እኔ የምለው ጎንጤ? ትከጅላታለህ እንዴ?> እለዋለሁ ቆጣ ብሎ <ምን ማለቶት ነው!> አለኛ» እናቴን ጨምሮ ሁሉም ይስቃሉ። እንደኮረዳ እሽኮረመማለሁ።

ስልኩ መልዕክት መቀበሉን የሚገልፅ ድምፅ ሲያሰማ ከመቀመጫዬ እንደመዝለል ሁሉ ሲያደርገኝ ቡና የምታፈላው ትንሽዬ ዘመዳችን ሳትቀር በአንድ ላይ አውካኩብኝ። የትልቅ ሰው ያልሆነ ማፈር አፍሬ መልዕክቱን ለማየት ሁሉ ስግደረደር ቆየሁ።

<እኔ ደግ ነኝ! የሚቻልሽ ከሆነ ድምፅሽን ታሰሚኛለሽ?> ነው የሚለው መልዕክቱ! አሁን ይሄ እሺ ምኑ ነው የሚያስቦርቀው? በፍቅርሽ ሞቻለሁ የተባለች ኮረዳ እንኳን እኔ የምሆነውን መሆን አትሆንምኮ! ትቻቸው ወደበር ወጣሁ እና ደወልኩለት። ቶሎ አውርተሽ መጨረስ አለብሽ የተባልኩ ይመስል የተፈጠረውን ለምን ሳላየው እንደመጣሁ እማዬ ስለደከመች ወደከተማ እንደማልመለስ በጥድፊያ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ አውርቼ ሳበቃ ሳቅ ብሎ

«ለመዝጋት ተቻኮልሽ እንዴ?» አለኝ
«አይ!» እያልኩ በቆምኩበት በጫማዬ መሬቱን እየቆፈርኩ መሆኑን አየሁ

«ደግ! ያሻሽን ያህል ጊዜ ቆይ!! » አለኝ

«አንተስ?»

«እኔ ምን እሆናለሁ?» አለኝ እኔ ማወቅ የፈለግኩት ከዛስ የሚለውን….. እኔ ያሻኝን ያህል ጊዜ እዚህ ስቆይ እሱስ? ከሆስፒታል ሲወጣ ቤት ሄዶ ይጠብቀኛል? ወይስ ያለሁበት ይመጣልኛል? ወይስ እኔ ወደማላውቀው ቤቱ ይሄድብኛል?

ያናደደኝን ወይ የተጣላኝን ሰው በጉልበት እንዴት እንደማግተው አውቅ ነበርኮ! የወደድኩትን ሰው እንዴት አባቴ አድርጌ ነው የራሴ የማደርገው? እሱን አልችልበትም!! በጉልበት ባገቱት ሰው ላይ ሙሉ ስልጣን ማራመድ ይቻላል። በፍቅር የወደቁለትን ሰው ራሱ ፈቅዶ ወደእኔ ካልቀረበ ምንድነው የማደርገው? ዝም አልኩ!!

«ዝም አልሽኝ እኮ ዓለሜ?» አለኝ ጠብቆ

«ምን እንደምል አላውቅበትም!! ያለፍከውን አላውቅም! ወደፊት ምን እንደምታስብ አላውቅም! ነገ ምን እንደምንሆን አላውቅም! አሁንም ምን እንደሆንን አላውቅም!! አላውቅህምኮ ጭራሽ! እኔ ግን እዚህ ልትሞት ያለች እናቴን አቅፌ ካንተ ሌላ ሀሳብ የለኝም!! ይሄ እንዴት ያለ መሸነፍ ነው ቆይ?» አልኩት።

«የት እሄድብሻለሁ? አለሁ አደል? ሁሉን ትደርሽበት የለ? አንች ብቻ የተሸነፍሽ አታድርጊው እንጅ!!» ብሎ ግማሽ መልስ ምን ግማሽ እሩብ መልስ ይመልስልኛል።

«እንዲህ እንድትለኝ አይደለም የምፈልገው!» ስለው እየሳቀ

«እንዴት እንድልሽ ነው የምትፈልጊ? ቁጣው የምንድነው ታዲያ?» ሲለኝ ነው እየተቆጣሁ እንደሆነ ያስተዋልኩት

«እንደምትወደኝ ነው ማወቅ የምፈልገው!! እንዳልነሳ ሆኜ በፍቅርህ ከመውደቄ በፊት እየተሰማኝ ያለው ስሜት የእኔ ብቻ እንዳልሆነ ነው ማወቅ የምፈልገው! አይሆኑ አሸናነፍ ከመሸነፌ በፊት እንደማላጣህ እርግጠኛ መሆን ነው የምፈልገው? እ?» ስለው መሳቁን ሳያቆም

«ፍቅርሽም ቁጣ ነው? እንደምወድሽማ ታውቂያለሽ! መስማቱን ከሆነ የፈለግሽ እወድሻለሁኮ ዓለሜ!! ነገ ምን እንደሚሆን ከፈጣሪ ጋር እናበጀዋለን!! ዛሬን ልውደድሽ ዓለሜ ዛሬን ውደጂኝ!!»

እንኳን ፊት ሰጥቶኝ ዘጭ ለማለት እየተንደረደረ የነበረ ልቤ ዝርፍጥ ብሎ በፍቅር ነሆለለ። ከዛን ቀን በኋላ በየቀኑ ተደዋወልን!! በየቀኑ እንደሚወደኝ ነገረኝ። በየቀኑ ደጋግሜ ተሸነፍኩ። በየቀኑ ከእማዬጋ ሳቅን። በየቀኑ ድሮ ያጣነውን እቅፏን ናፍቆት መሬት ላይ አንጥፈን ለሶስት እቅፏ ውስጥ አደርን። በየቀኑ ደስ አላት!! በአስራ ሶስተኛው ቀን ጠዋት እኔና ኪዳን በቀኝና በግራዋ ሙቀቷን እየሞቅን እማዬ ዝም አለች።

እማዬን ስላጣኋት ከፋኝ። አግኝቻት ስለሞተች ደግሞ አመሰገንኩ። ኪዳንም ተመሳሳይ ስሜት ነበር የተሰማው ግን ከእኔ በላይ የእርሱ ሃዘን በረታ!! ምናልባት እኔ ለእርሱ ለመሆን ስታትር ዘመኔን ስለኖርኩ አጎደልኩበት ብዬ እንዳላስብ ዝም ብሎኝ እንጂ ሁሌም የእናቱ ናፍቆት ያንገበግበው ነበር ይሆናል። በኖረችልኝ ብሎ ሲመኝ ይሆናል የኖረው። እኔና አጎቴ ከእርሱ በርትተን እሱን ማበርታት ጀመርን።

የቀብሯ ቀን ሬሳዋ ከቤት ሲወጣ አይኖቼን ደጋግሜ አሸሁ ያየሁትን ሰው ለማጣራት። አቶ አያልነህ! ፈገግ አልኩ! ይቅር ብለውኛል ማለት ነው።
አዲስ አበባ ከገባሁ ከአመታት በኋላ ባለገንዘብ የሆንኩ ጊዜ ወደእሳቸው መንደር ላገኛቸው ተመልሼ ነበር። አፈላልጌ በጥቆማ እቤታቸውን ፈልጌ ሳገኝ እኔ አወቅኳቸው። ከዘራ ይዘው እያነከሱ ከበራቸው ወደቤት እየገቡ። እሳቸው ግን አላወቁኝም ነበር። ከአመታት በፊት ካየኋቸው አርጅተው። ተጎሳቁለው ነበር። ሰላም ካልኳቸው በኋላ ከከተማ መምጣቴን ስነግራቸው ወደቤታቸው ጋበዙኝ።

«ያስታውሱኝ ይሆን?» አልኳቸው

«ዓይኔ እያስቸገረኝ ነው ልጄ አላስታወስኩሽም! የማን ልጅ ነሽ?»

«ማን እንደሆንኩ እነግሮታለሁ! መጀመሪያ ግን ማንነቴን ስነግርዎት የምለውን ሰምተው እንደሚያስጨርሱኝ ቃል ይግቡልኝ!!»

«ልጄ እያስጨነቅሽኝኮ ነው!!»

«ቃል ይግቡልኝ!! የምለውን ሁሉ ይሰሙኛል?»

«እሽ ቃሌ ነው!!»

«ከብዙ ዓመት በፊት ከገበያ ሲመለሱ አንዲት ሴት እንደዘረፈችዎት አይጠፋዎትም መቼስ!»

«እንዴት ይጠፋኛል! ቤቴን እኮ ነው ያፈረሰችው! » ብለው በደንብ አዩኝና « አምሳል ነኝ እንዳትይኝና እዚህ ደም እንዳንፋሰስ!!»

«እስከመጨረሻው እሰማሻለሁ ብለው ቃል ገብተውልኝ የለ?»

«በይ ልስማዋ!!»

እግራቸው ላይ ወደቅኩ!! «ከዛን ቀን በኋላ ሳላስቦት የዋልኩ ያደርኩበት ቀን የለም! አንዲት ቀን እንኳን ፀፀት ሳይፈጀኝ አልፎ አያውቅም!! ይቅር አይበሉኝ! ግን ከዚህ በላይ አይቅጡኝ!! የምሰጦትን ገንዘብ ይቀበሉኝ!» አልኳቸው

ተነስተው በፍፁም አሉ!! ሚስታቸው ከጓዳ ትሰማ ነበር እና

«ደግም አይደል አያል! ይህች ልጅ ተጠጥታ መጣችም አይደል? እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል አቤቱ በደላችንን ይቅር በል ብለንም አይደል የምንጠልይ? ተነሽ ይበሏት በቃ!» አሉ። ከስንት ልምምጥ በኋላ እንዳኩረፉ ያመጣሁላቸውን ገንዘብ ተቀበሉኝ። አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች አንደኛው ማረፋቸውን ነገሩኝ! ሌላኛውን እቤታቸው ሄጄ ስላላገኘኋቸው መልዕክቴን ከገንዘቡ ጋር አስቀምጬ ተመልሼ ለአቶ አያልነህ ይቅርታዬን እንዲነግሩልኝ ለምኜ ልወጣ ስል እንዲህ አሉኝ

«ጨርሶ ይቅር ያልኩሽ እንዳይመስልሽ!! ድህነት አይኑ ይጥፋ ዛሬም ለልጆቼ ፍራንካው ስለሚያስፈልግ እንጂ ለራሴ ቢሆን እመቤቴ ምስክሬ ናት ፍንክች አላደርገውም!!» ብለውኝ ነበር። ከዓመታት በኋላ ለቅሶዬን ሊደርሱኝ የመጡት በልባቸው ይቅር የሚሉበት ፍቅር አጊንተው ቢሆን አይደል? ይቅር መባል እንዲህ ደስ እንደሚል ባውቅ ስንት ይቅርታ የምጠይቀው ነበረኝ!!


........ አልጨረስንም ......,

(የዛሬው አጭር ነው አውቃለሁ!! ውብ ዋሉልኝ❤️❤️)
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ስድስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የእማዬ ቀብር ላይ የአባቴ ገዳዮች ዘመድ አዝማድ እና ልጆች ሁሉ ሊቀብሯት ሲያጅቧት ፤ አንዳንዱም ሲያለቅሱላት እያየሁ የተሳከረ ስሜት ወረረኝ። የዛን እለት ከአቶ አያልነህ ጋር የነበሩት ሰውም አረፋፍደው ተቀላቀሉ። የኛም ወገን የእነሱም ወገን የተፈጠረውን እልቂት ይቅር ተባብለው ተሻግረውት እኔ ብቻ ነበርኩ በጥላቻ የሰከርኩት? አይደለም! እዚህ ያሉት ናቸው በይቅርታ የተሻገሩት!! ጥላቻ እና ቂማችንን ይዘን ከተማ የገባን እኔና መሰሎቼ በየሶሻል ሚዲያው በቃላት ተዋግተናል፣ ካለመንደራችን በተገናኘንበት ተጠማምደን ተጠላልፈናል፣ የደማችንን ምንጭ ተጠያይቀን ለአባቶቻችንን ፀብ እኛ ተሰነካክለናለን ተጫርሰናል፣ እኛ እንደአባቶቻችን በጥይት ተጫርሰን ባናሳያቸውም ለወለድናቸው ልጆቻችንን እና ታናናሾቻችን ጥላቻችንን አጋብተናል። እነርሱ ግን እረስተውትም እንኳን ባይሆን አልፈውት የአንዳቸውን ለቅሶ ይላቀሳሉ። እኔ ግን ከወራት በፊት እንኳን የእነእርሱን የልጅ ልጅ እንኳን ባገኝ በማያውቀው የአያቱ በደል ጥላቻዬ ውስጤ ይፈላ ነበር።

ከቀብር መልስ ሰው እየተሰናበተን ሲወጣ አቶ አያልነህ ከሚስታቸው ጋር ተሰናብተው ሊወጡ ሲሉ እጄን ያዝ አድርገው።

«እግዜሃር ያፅናሽ!» ሲሉኝ እጃቸውን በደንብ ጨብጬ ይዤ

«ዛሬ ነው የፈቱኝ!! እስከዛሬ የእርሶ እስረኛ ነበርኩ።» ስላቸው ቁጥብ ያለ ፈገግታ ፈገግ ብለው

«እኔ ይቅር ብያለሁ እርሱ ጨርሶ ይቅር ይበልሽ!! በርቱ!!» ብለውኝ ወጡ!!

በኋላ ላይም ወዳጃቸው የተቀመጡበት ሄጄ እጃቸውን ያዝ አድርጌ (በአካል ስላላገኘኋቸው ሁሌ ይከነክነኝ ነበር) «የማይገባኝን ይቅርታ ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ!!» አልኳቸው። እሳቸው ከአቶ አያልነህ በላይ በተፈታ መንፈስ

«እግዜር ያፅናሽ ልጄ!! እቤቴ በተውሽው መልዕክት የልጆቼን ህይወት ነው የቀየርሽው!! ልብሽ ቀና ነው የእኔ ልጅ ቂምና ጥላቻ ለማንም አይበጅ! ለአባትሽም ለእኛም አልሆነን!! ልብሽን ከክፉ ጠብቂው!» ብለው ጭራሽ እኔኑ አበረቱኝ።

የቀብር ቀን ማታ ፍራሽ ላይ ተቀምጠን ሊያማሽ የመጣውን ለቀስተኛ እየተቀበልን ስንሸኝ በሚገባ እና በሚወጣው ሰው መሃል ጎንጥ በሞላ ሞገሱ ጎንበስ ብሎ ድንኳኑን ሲዘልቅ ሳየው የእማዬን መሞት አሁን የተረዳሁ ይመስል ድንኳኑን በለቅሶ ደበላለቅኩት። እስከአሁን ሲገባ ሲወጣ ከነበረው ሰው የበለጠ ፣ እስከአሁን ሊያፅናናኝ ከሞከረው ህዝብ በበለጠ ፣ እንደነፍሴ ከምወደው ኪዳኔ እንኳን የበለጠ ፣ ከአጎቴም የበለጠ ……. እሱ ብቻ የበለጠ ህመሜ የሚገባው ዓይነት ነው የመሰለኝ። ድንኳኑ እንደአዲስ በለቅሶ ተናጠ። ሌላ ሰው መኖሩን ረሳሁ!! ዘልዬ እቅፉ ውስጥ ገባሁ!! አላባበለኝም አብሮኝ አለቀሰ። ሽማግሌዎች <ከመሸ እንዲህ አይለቀስም> ብለው ሊያረጋጉ ሲሞክሩ አጎቴ ከውጭ ብቅ ሲል ጎንጥን ሲያየው ከእኔ ብሶ አረፈው። ልክ የሆነ ታናሽ ወንድሙን ያገኘ ወይ ታላቅ ልጁን አልያም የብዙ ጊዜ ወዳጁን ያገኘ ይመስል

«አመለጠችኝኮ! አትከብጅኝም ትንሽ ቆይ እያልኳት አሻፈረኝ ብላ ሄደች! እንብኝ አለች! ናፍቆቴ አልወጣልኝም እያልኳት ተሸነፍኩ አለች!» እያለ ሲያለቅስ ድንኳኑ ተተራመሰ። ጭራሽ ሁለቱ ተቃቅፈው ሲላቀሱ የተወሰኑ ቀናት አብረው ያሳለፉ ሳይሆን ሳይነጋገሩ የሚግባቡ ቤተሰቦች ነው የሚመስሉት። እኔስ ስለወደድኩት ወይ ይወደኛል ብዬ ስላሰብኩ ለልቤ አቅርቤው መሰለኝ ሳየው ሀዘኔ የፈነቀለኝ። አጎቴስ? ምናልባት እኔ ያልሰማኋቸውን ቅፅበት የልብ የልባቸውን አውግተውበት ተናበው ይሆን? ወይስ ለልብ ለመቅረብ የተለየ ነፍስ ያለው ሰው አለ?

ለቅሶው ሲበርድ አጠገቤ መጥቶ ፍራሽ ላይ ተቀመጠ። ለቀስተኛው ማን ስለመሆኑ ግራ እየተጋባ ሲጠያየቅ አጎቴ «ቤተሰብ ነው!» እያለ ይመልሳል። አንድ ዘመዳችን

«የአባትሽ ቤተሰብ ነው? የእነርሱ ደም ይመስላል!» ስትለኝ በደንብ አስተዋልኩት። በጭንቅላቴ ውስጥ ሊጠፋ የደበዘዘ የአባቴን መልክ ለማነፃፀር እየታገልኩ ….. ቁመቱ ፣ ትከሻው ፣ ግርማ ሞገሱ ፣ ጥይምናው ፣ ጅንንነቱ …… ከአባቴ ጋር ይመሳሰላል። ለአፍታ <የተሸነፍኩት ሳላውቀው አባቴን እሱ ውስጥ ስላገኘሁ ይሆን?> ብዬ አሰብኩ። ሳይታወቀኝ አፍጥጬ እያየሁት ስለነበር

«ምን አስፈልጎሽ ነው?» አለኝ

«ምንም! ስለመጣህ ደስ ብሎኛል።» አልኩት

«እንዴት ይቀራል ብለሽ አሰብሽ?» ብሎ ወደትከሻው አጥብቆ ከያዘኝ በኋላ የህመም ትንፋሽ ተነፈሰ። ከሆስፒታል የሚወጣበት ቀን ቀናት እንደሚቀሩት እያወቅኩ እሱን አለማሰቤ አሳፈረኝ። እሱ አጠገቤ መሆኑን እንጂ የእርሱን ቁስል አላሰብኩለትም።

«ውይ! ይቅርታ!» ብዬ ከትከሻው ቀና ስል መልሶ ከቅድሙ በላላ ሁኔታ ትከሻው ላይ አስደግፎኝ
«ደህና ነኝ!!» አለኝ

«ሆስፒታል መቆየት ነበረብሃ?»

«አንድ ሁለት ተጨማሪ ቀን ነበረብኝ! የእኔ ሀሳብ አይግባሽ!! ደህና ነኝ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? አንች መድሃኒቴ አይደለሽ? ሆስፒታል ምናባቱ?» ብሎ ከደቂቃዎች በፊት ስንሰቀሰቅ የነበርኩትን ሴት ያሽኮረምመኛል? እያየኝ ያለ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ አይኔን የተቀመጠው ለቀስተኛ ላይ አንቀዋለልኩ።

እናቴ የሞተችብኝ እኔ ከዛ ደግሞ የተሽኮረመምኩትም እኔ …… ለሰው የሀዘኔን ጥልቀት አሳይቼ መሽኮርመሜን መደበቅ ያለብኝም እኔው!! ምክንያቱም ምንም እንኳን ሊያፅናኑ ቢመጡም ስፅናና እንደሚዳኙኝ አውቃለሁ። <የእናቷ ለቅሶ ላይ ተሽኮረመመች፣ የእናቷ ለቅሶ ላይ ስታስካካ ነበር ፣ ምን እሷ ምንም አልመሰላት ኸረ አላያችኋትም እንዴ እናቷን መቅበሯን ረስታ ከወንድ ጋር ስትለፋደድ?> እንደሚሉኝ አውቃለሁ። ግራ የሚገባኝ ሊያፅናኑኝ የሚሞክሩት የውሸት ነው ማለት ነው? ሀዘን ማብዛት ጥሩ አይደለም የሚሉት ስለሚባል ነው ማለት ነው? ስፅናና ወይ ስስቅ ታዲያ ለምን ይከፋቸዋል? <በደንብ አላለቀሰችም!> ሁሉ እንደሚባል አውቃለሁ!!

ስለዚህ ተሰብስቤ ተቀመጥኩ። እኔ ትቼው የምሄደው ህዝብ እና መንደር ቢሆንም ለአጎቴ ወሬ ትቼለት መሄድ አልፈለግኩም!! በሁለተኛው ቀን ጎንጥ የምጨራርሰው ጉዳይ አለኝ ብሎ ወደከተማ ተመለሰ።

ከእማዬ ቀብር በኋላ ቤቱ ውስጥ የሚተራመሰው ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት እየተመናመነ ሄዶ ድንኳኑ ከተነሳ በኋላም ኪዳን መሄድ የፈለገ አይመስልም። «ትንሽ ቀን እንቆይ!» ሲል ብዙ ቆየን። ሁሉም ወደቤቱ ገብቶ ሶስታችን ብቻ የቀረን ቀን ማታ ሀዘናችን በረታ እና እንደአዲስ መላቀስ ያዝን። ኪዳን ከሁለታችን ብሶ «ምናለ ትንሽ ቀን ብትሰጣት? ፣ ምናለ ትንሽ ቀን ብጠግባት? ፣» እያለ ከአምላኩ ጋር ሲሟገት አንጀቴ ልውስ ብሎብኝ ተንሰፈሰፍኩ። አጎቴ እንደልማዱ «እህቴ ፤ ክፋዬ ፣ አንድ ደሜ …. » እያለ እንዳልተነፋረቀ እንባውን በፎጣው አደራርቆ

«ተው ደግም አይደል። የፈጣሪን አይን አትውጉ! ሳናያት ሳናውቅ አልፋስ ቢሆን? የልጆቿን ዓይን ዓይታ ፤ ጠረናችሁን ስባ በትውልድ ቀዬዋ ሀገሬው ቤቱን ነቅሎ ወጥቶ በፍቅር የሸኛት እሰቡት አምላክ እንዴት ቸር እንደሆነ? ደግም አይደል?» ብሎ ተቆጥቶ አረጋጋን!! እንባችንን አቆምን እንጂ ለሚቀጥሉት ቀናት እንደተኳረፈ ሰው በመሃከላችን ብዙም የቃላት ልውውጥ አልነበረም። የሆነ ቀን ውጪ ሳሩ ላይ ተቀምጠን

«የኔ ኪዳን? አሁንም ከዚህ በላይ መቆየት ትፈልጋለህ?» አልኩት

«እኔ እንጃ ሜል! ወደ አዲስአበባ መመለስ ከፈለግሽ እንመለስ! እኔ አሁን ምን እንደምፈልግ ራሱ አላውቅም!!» አለኝ።
«አዲስአበባ ከሄድን እዛ አንድ ቀን እንኳን እንድታድር አልፈልግም!! ሳይውል ሳያድር እንድትወጣልኝ ነው የምፈልገው ምን ያደርጉብኝ ይሆን ብዬ ማሰብ አልፈልም!!»

«አውቃለሁ!! ግን አንቺስ?»

«እኔ ምን? እኔ ራሴን መጠበቅ አያቅተኝም!!»

«ሜል ብዙ ነገር ተቀይሯል። ምን ያህል እንዳስተዋልሽው አላውቅም እንጂ አንቺም ራሱ ፍፁም ተቀይረሻል። ወደኋላ ተመልሰሽ ያለፈ ህይወትሽን መኖር የምትችዪ አይመስለኝም! እሱን ነው የምታስቢው? ምንድነው የምታስቢው?» አጠያየቁ የእኔ ኪዳን አይመስልም በጣም ተኮሳትሮ እንደታላቅ ነው የሚያወራው

«አላውቅም! ራሴ እንደተቀየርኩ አውቃለሁ ነገር ግን ያለፈውን ህይወቴን ሙሉ ለሙሉ ተፋትቼ መኖር እችል እንደሆነ አላውቅም! ምክንያቱም እኔ ብቻ እንጂ የተቀየርኩት በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ሁኔታዎችም እንዳሉ ናቸው። የቱን ጥዬ የቱን ይዤ እንደምቀጥል አላውቅም!»

«ለምን ከሀገር መውጣትን አታስቢበትም? ሁሌ ጀርባሽን መጠበቅ ሳይኖርብሽ አዲስ ህይወት አዲስ ማንነት ትገነቢያለሽ!»

«እኔእንጃ የኔ ኪዳን!!»

«በጎንጥ ምክንያት ነው? የነገ አብሮነታችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል ተነጋግራችኋል?»

«አይደለም! ስለነገም ያወራነው የለም! ስለምንም ያወራነው የለም!»

«ሜልዬ እስኪ ዛሬ እንደ ትንሹ ወንድምሽ ሳይሆን እንደ 31 ዓመት ትልቅ ሰው አውሪኝ! እንደምትዋደዱ ግልፅ ነው!! እኔ ሳውቅሽ ለማንም ሆነሽ የማታውቂውን ነው ለሱ እየሆንሽ ያለሽው! ማንንም ሰው ባላቀረብሽው ልክ ነው እሱን ያቀረብሽው! ወደፊትሽን ስታስቢ እሱ አለበት? ያወራችሁት አይኑር! አንቺ ምንድነው የምታስቢው?»

«እኔ እንጃ ኪዳንዬ የእውነቴን እኮ ነው እኔንጃ የምልህ!! ታውቃለህ እኔ ፍቅር አላውቅም!! ፀብ ቢሉኝ አውቃለሁ፣ በቀል ቢሉኝ አውቃለሁ ……. ፍቅር ግን አዲሴ ነው!! ስምጥ ብዬ ከዋኘሁ በኋላ ነውኮ እንደወደድኩት እንኳን የነቃሁት! ደግሞ እኔ ብቻ የማስበው ምን ይፈይዳል? እኔ ስላሰብኩህ ና ወደፊቴ ውስጥ ላካትህ ይባላል?»

«ጠይቂዋ!»

«ምን ብዬ?»

«ምንድነው ስለወደፊት የምታስበው? አብሮነታችን ምን ድረስ ነው የሚዘልቀው? ብለሽ ነዋ!»

«እህ እሱ አይደል እንዴ ወንዱ! ይሄን መጠየቅ ያለበት እሱ አይደለም? በግድ እየገፋፋሁት ቢመስልብኝስ?» ስለው ከቀናት በፊት ሲስቅ የሰማሁትን ሳቅ ሳቀ።

«አይመስልም ዓለሜ (ልክ ጎንጥ በሚልበት ለዛ) ዘመኑ ተቀይሯል!! ሴት ተንበርክካ አግባኝ የምትልበት ዘመን ላይ ነን!»

« ምንስ ፍቅር ብርቄ ቢሆን ጥንቅር ይላታል እንጂ ተንበርክኬማ አግባኝ አልለውም! ጭራሽ? ለተሸነፍኩትም መደበቅ ቢቻለኝ በዋጥኩት! እንቢ እያለኝ እያመለጠኝ እንጂ!!» ተሳሳቅን!!

በሚቀጥለው ቀን ኦንላይን ትኬቱን ቆርጦ አጎቴን ተሰናብተን (ስንብቱ በእንባ የታጀበ ነበር።) ወደ አዲስ አበባ መጣን!! የዛኑ ቀን በረራው ነበረ። ስንሰነባበት

«ሜል አስብበታለሁ በይኝ ከሀገር መውጣቱን?»

«አስብበታለሁ ሙት!!»

«ለዓለሜ እንደምትዪው <የእህቴን ልብ ብትሰብር ውርድ ከራሴ!! ጦርነት በራስህ ላይ እንዳወጅክ ቁጠረው አንላቀቅም!!> ብሎሃል በይልኝ። የምሬን ነው ንገሪው!»

«ሂድ አሁን አርፈህ!! እነግርልሃለሁ!!»

እሱን ሸኝቼው ስመለስ ህይወቴን ካቆምኩበት መቀጠል እንደማልችል ገባኝ። ቤቴ እንኳን ያለስጋት መሄድ እንደማልችል ሳውቅ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሜ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ብዙ ቆየሁ። የእውነት ምንድነው አሁን የማደርገው? እንደድሮው ባር ሄጄ ወገበ ቀጫጭን ሴቶች የቆመ ፖል ላይ ሲውረገረጉ ፣ ለፍዳዳ ሰካራሞች ለሀጫቸውን እያዝረከረኩ ብራቸውን ሲረጩ …. .፣ አቅላቸውን የሳቱ ሱሰኞች ሀሺሺን ከሺሻው እያደባለቁ ሲያጨሱ …… እያየሁ እየተዘዋወርኩ ብሉልኝ ፣ ጠጡልኝ ፣ አጭሱልኝ ፣ ተዝናኑልኝ እያልኩ ብሬን መምታት ይቻለኛል?

ከአንድ ሰዓት በላይ ከቆምኩ በኋላ የሆነኛው ገስት ሀውስ ይዤ ለዛሬ እርፍ ብዬ መተኛት ፈለግኩና ከዛ በፊት የጎንጥን ድምፅ መስማት ፈለግኩ። አንዱ ሱቅ ገብቼ ደወልኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ገስትሀውስ ገብቼ ለማረፍ ሞከርኩ እና ተገላበጥኩ። ራሴን አሁንም ወጥቼ የሱቅ ስልክ ላይ ስደውል አገኘሁት። ዝግ ነው!! ተመልሼ ገብቼ ለጥ ብዬ አድራለሁ ያልኩትን ለሊት ስገላበጥ አደርኩ። ይሄኛው ስሜት ደስ አይልም!! ስልኩን ባይከፍተው የት ብዬ ነው የማገኘው? የድሮ ሚስቱ ቤት ሄጄ <እየገደልሽኝ ሳለ እግረመንገድሽን ጎኔ የት እንዳለ ብቻ ንገሪኝ> ነው የምላት? ደግሞ ለራሴ <ማታ አይደል ያዋራሁት? ይሄኔ ባትሪ ዘግቶበት ነው!> እላለሁ። ዛሬ እንደምመጣ እያወቀ ስልኩን የዘጋው ሊያገኘኝ ስላልፈለገ ቢሆንስ? ምን እየሆንኩ ነው ስንት ሀሳብ እያለብኝ ስለእርሱ ብቻ የማስበው? ……. ስወራጭ ቆይቼ ሊነጋ ሲቃረብ እንቅልፍ ወሰደኝ!!

እንደነቃሁ ተጣጥቤ ስልኩን ሞከርኩ። አሁንም ዝግ ነው። ወደሰፈሬ ነዳሁ እና ተናኜን ቅያሪ ልብሶች ተቀብያት ጎንጥ ብቅ ብሎ እንደው ስጠይቃት አለመምጣቱን ነገረችኝ። ልብሴን እዛው መኪና ውስጥ ቀይሬ ሻለቃው ቢሮ ሄድኩ። የሰዎቹን ፎቶ ከተገበያየሁ በኋላ እንደማላውቃቸው ሳውቅ መረጃ የሚያቀብለኝ ሰው ጋር ደወልኩ።

«ኢሜል የማደርግልህን ፎቶ ተመልከተውና መረጃ አቀብለኝ» ካልኩት በኋላ የሁለቱን ሰዎች ፎቶ እየላኩለት ልክ እንዳልሆነ የማውቀው ሀሳብ ጭንቅላቴን ወጠረኝ። ላለማድረግ ከራሴ ጋር ታገልኩ። ግን አቃተኝ!! ከስልኬ ውስጥ ጎንጥን ስቀጥረው ይዤው የነበረውን ፎቶ አብሬ ላኩለት። መልሶ ደወለልኝ እና

«ይሄን ሰውዬኮ ከዚህ በፊት ጠይቀሽኝ ነበር።»

«አውቃለሁ!! ተጨማሪ መረጃ ፈልግ!! በጓሮ ሂድ!» አልኩት (ሰውየው በግልፅ ከተመዘገበው መረጃ በላይ የተደበቀ መረጃ አለው ለማለት ነው በጓሮ ሂድ የምንባባለው)

ስልኩን ዘግቼው ኮምፒውተር ቤቱ ውስጥ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ!!!

………… አልጨረስንም …………..

(ውብ ቀን ውብኛ ዋሉልኝማ ❤️❤️❤️❤️)
ቤተሰብ እንዴት አደርን? (አንዳንዶች እዚሁ ያደራችሁኮ ነው የሚመስለው ከኮመንት ቦክስ ውስጥ😂😂) ታሪኩ ወደመጨረሻዋቹ ክፍሎች እንደመቃረቡ (ብዙም አልቀረንም ትንሽ ክፍሎች ቢቀሩት ነው) ዘለግ አድርጌ ከሰዓት እንደበቀደሙ በ8 ሰዓት (በኢትዮጵያ ሰዓት) እለጥፍላችኋለሁ ክፍል ሀያ ሰባትን!!! እስከዛ ኮመንት የምታደርጉትንም ፣ የምትጀናጀኑትንም 😂😂(በርቱና እስኪ ቃለመጠይቅ ሲደረግላችሁ <ሜሪ ቴሌግራም ላይ በነጎንጥ ታሪክ ነው የተጣበስነው> ብላችሁ ስሜን ጥቀሱማ 😂፣ የምትገምቱትንም ቀጥሉበት። ይሄ ሙልጭልጭ ጎንጤንም ከገባበት ልፈላልገው። በተረፈው እስከዛ ውብኛ ቆዩልኝ❤️❤️❤️❤️
የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሀያ ሰባት
(ሜሪ ፈለቀ)

የሰው ልጅ ለውጥ የአንድ ጀምበር ክስተት አይሆንም። ወይ ተሸርፎ ተሸርፎ የተጋተው ልምድ እየቆየ ይለውጠዋል አልያም በህይወቱ ከባድ ክስተት እንደሚወዱትን ማጣት ያለ ንዝረት 360 ዲግሪ ይቀይረዋል። የአባቴን ገዳዮች ለመጥላት የአባቴ ሞት እና የእናቴ አይኔ ስር መደፈር በቂ ነበር። የበቀል ጥንስሴን ከዜሮ መቶ ለማድረስ ለቁጥር የሚታክት ጊዜ አባቴ የሞተበት ደጃችን ላይ ተመላልሼ ክስተቱን በጭንቅላቴ ስያለሁ!! አንድ ቀን ባልሳቅኩ ቁጥር፣ ልጅነቴን ሁሉ እኔና ወንድሜ እናትና አባት እንደሌለን ባሰብ ቁጥር ሁሉ አምርሬ ጠልቼ አምርሬ ላጠፋቸው ሰውነቴ ጥላቻ ረጭቷል።

ሴት ልጅ እርቃኗን የወንድ መዝናኛ ሆና የምታስገኘውን ገንዘብ እንደገቢ ከመቁጠሬ ከዓመታት በፊት የሴት ልጅ ገላ ሲቀል አይቼ ዘግንኖኝ ነበር። <እንዴት አይነት አስተዳደግ ብታድግ ነው?>ም ብዬ ፈርጄባታለሁ። ቀን በቀን በትንሽ በትንሹ ስጋተው ቀጭን ወገብ ሳይ ፖሉ ላይ ስትጥመለመል የሚስል ጭንቅላት ኖረኝ እና አረፈው።

ያኔ ታክሲ በር ላይ ተለጥፌ ፒያሳ ሜክሲኮ የምል ጊዜ ……. በጉልበቴ ተከበርኩ። ተራ አስከባሪውም ሹፌሩም ከዛን ቀን በፊት አይቶኝ በማያውቀው የክብር ዓይን አየኝ። ፀሃይ ሲያነደኝ ውዬ የማገኘው ገንዘብ ግን ኪዳንዬን እንደምፈልገው የሚያኖርልኝ አልነበረም። ያ ሰውዬ የሰጠኝን ቢዝነስ ካርድ ለማይቆጠር ያህል ጊዜ ካሸሁት በኋላ ደወልኩለት። ሰውየው ደላላ ነው። ሊያስቀጥረኝ ያጨልኝ ቦታ እንኳን ለእንደእኔ ዓይነቷ ከትንሽ ክፍለሀገር ለመጣች ሴት ቀርቶ የፈረንጅ ፊልም ስታይ ላደገች ከተሜም ቀላል አይመስለኝም። ከተማዋ ውስጥ እኔ ነኝ ያለ የመናዊ ሰውዬ ጠባቂ መሆን ነው። መጠበቁ ደግ ነበር። ሰውየው የጋዳፊ(ስለጋዳፊ ሳውቅ ነው የገባኝ ጉዳዩ) ታናሽ የሚሰራራው ወፈፌ ነው። ጠባቂዎቹ ሴቶች እንዲሆኑ ከመፈለጉ አንድ ደርዘን ሴት እንዲጠብቀው መፈለጉ ግራ ያጋባል። ብስራተ ገብርኤል ካለው ቤቱ ቦሌ ለመድረስ በአራት መኪና እና በ10 ሴት ጠባቂ በሁለት ወንድ አጃቢ መከበብ ጤንነት ነው?

የተገናኘን ቀን ዝርዝሩን ብዙም ሳይነግረኝ ሰውየው ቤት ይዞኝ ሄደ። የቤቱ ስፋትና ውበት ቤተመንግስት ራሱ እንደዚህ ይመስላል የሚል ምስል ጭንቅላቴ ውስጥ የለም። የአጥሩ በርጋ ብቻ ወንድ ሁለት ጠባቂዎች ሲኖሩ በተረፈው ሱፍ ኮት እና ሚኒ ጉርድ የለበሱ በለበስኩት የመነቸከ ሸሚዝና ጅንስ ሱሪ የሚያሸማቅቁኝ የሚያማምሩ ሴቶች ሲቀባበሉ ብዙ ኮሪደር እና ክፍሎች አልፈን አንደኛው ቢሮ የሚመስል ክፍል አደረሱኝ። ሴቶቹ ምናልባት ከሁለቱ ውጪ ሀበሻ አይደሉም!! ሰውየው ፊቱ ከመንጣቱ የተነሳ የሰው ቆዳ ሳይሆን ነጭ ሸማ የመሰለ ፊት ያለው አረብ ነው። ጭንቅላቱ ላይ በቄንጥ የታሰረ ሻርፕ ነገር አድርጎ እንደወተት የነጣ ቀሚስ ለብሷል። ከደላላው ጋር በአረብኛ ሲነጋገሩ እንዳልወደደኝ ያስታውቅበታል። ከእግሬ እስከራሴ በማጣጣል እያየኝ ቁጣ የመሰለ ነገር ይንጣጣል። ደላላው ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ሳይገባኝ አይኔን ከሰውየው ወደ ደላላው እያቁለጨለጭኩ ሳይ ከየት መጣ ያላልኩት የሆነ ጠባቂ መሰለኝ ከጀርባዬ ሳላስበ በእጁ ቆልፎ አንቆኝ ወደላይ አነሳኝ። እነርሱ ጭቅጭቃቸውን ቀጠሉ። ደመነፍሴን እየሆነ ያለው ሳይገባኝ በቀኝ እጄ ያነቀኝን እጁን ጠምዝዤ በግራ እጄ ፍሬውን አጎንኩት። እጁን ጠምዥዤ ወደፊት ስደፋው ነው ሆነ ብለው የፈጠሩት ድራማ መሆኑን ያወቅኩት። ሰውየው <ምንም አትል> አይነት ንቅናቄ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።

እዚህ ድረስ ሰላም ነበር። እንድለካው ያመጡልኝን ልብስ ስለብሰው የለበስኩት ፓንት ሊታይ ትንሽ የቀረው ከመሆኑ ለፋሲካ የሚገዙትን በግ አዟዙረው እንደሚያዩት እየዞረኝ ሲገረምመኝ
«ምንድነው እሱ? ስራው ጥበቃ ነው አላልክም? ደግሞ ይሄን ብጣሽ ነገር አገልድሜ አንድ እርምጃ አልሄድም!! አልፈልግም ስራውን!» ብዬ ልብሱን እንድቀይር የወሰዱኝ ክፍል ሄጄ የራሴን ልብስ ስቀይር አሁንም እነርሱ እንደጭቅጭቅ ያለ ወሬ ሲያወሩ ይሰማኛል። ደላላው በኋላ ሲገባኝ ለሚከፈለው ጠርቀም ያለ ገንዘብ ነው ሽንጡን ገትሮ እንድቀጠር ሲከራከር የነበረው። ሰውየው ስራውን አልፈልግም በማለቴ ተናዶ መሆኑን በኋላ ሰማሁ። <ማን እንደሆንኩ አውቃለች? > ብሎ ነበር የደነፋው። ስንወጣ ደላላው ደሞዙን ሲነግረኝ ጠጅ እንደጠጣ ሰው ጉልበቴን ያዘኝ። ግን እንዲያውቅብኝ ስላልፈለግኩ መግደርደሬ እንዲታወቅልኝ

«የምሰራ ከሆነም ያን ቀሚስ አልለብስም። ሱሪ ከተደረገልኝ እሰራለሁ!! ደግሞ ቆይ ሴቶቹስ እግራቸውን ማንሳት ቢኖርባቸው በዛ ቀሚስ እንዴት ነው የሚሆኑት?»

«ሰውየው በሴት የመከበብ ልክፍት ስላለበት እንጂ አሁን ማን ይሙት አዲስአበባ ውስጥ እንዲህ ተከቦ የሚያስኬድ ስጋት ኖሮበት ነው? የሀብታም ነገር ብሩን የሚጥልበት ሲጨንቀው ነው።» አለኝ። ከቀናት በኋላ ሱሪ መልበስ እንደተፈቀደልኝ ነገረኝ እና ስራውን ጀመርኩ። ጀመርኩ እንደዋዛ አይደለም። ከሰውየው ጠባቂዎች ጋር ኢላማ ተፈትኜ…… መጀመሪያ ሰሞን በየሄደበት በር ጠባቂ ካደረገኝ በኋላ ….. ከሀገር ውጪ ሲወጣ ባዶ ቤት ክፍሎች ጠባቂ ከሆንኩ በኋላ ….. ከኪዳን ጋር የተሻለ ቤት ተከራይተን መኖር ከጀመርን በኋላ ……. የግል ትምህርት ቤት ካስገባሁት በኋላ …… የሆነ ጊዜ ደላላው ሲመጣ በር ጠባቂ መሆኔን ሲያይ

«አንቺ ከእነዚህ እሳት ሴቶች ጋር እየዋልሽ ዛሬም በር ላይ ነሽ? አትማሪም? ምንድነው እንዲህ ማካበድ? ይሄኔ ብታቀምሺው ስንት ሀገር አይተሽ ነበር! ያንቺ የተለየ ነው እንዴ ይሄን ያህል?» ሲለኝ እስከዛን ቀን ዙሪያዬ እየሆነ ያለውን አለማጤኔ ገባኝ። አትማሪም ወይ? አለኝ እንጂ ሴቶቹ ከእኔጋ ጊዜ ኖሯቸውም አያወሩ ቢኖራቸውም የእነርሱ ዓይነት አራዳ ስላልነበርኩ ትዝም አልላቸውም። በዛ ላይ ከሁለቱ ሀበሾች ውጪ በቋንቋም አልግባባም!! ደላላው ከሄደ በኋላ ነው ከእኔ ውጪ ሁሉም ሴቶች ባለመኪና የመሆናቸው ሚስጥር እኔ ቅርብ ስራ ጀማሪ መሆኔ ሳይሆን እነርሱ መቀመሳቸው መሆኑ የተገለጠልኝ። እስከዛን ቀን ድረስ ሴትነትን ወይም ድንግልናን አስቤው የማውቅ ባልሆንም ነገሩን አስቤው ዘገነነኝ። ሴትነትን ሳስብ ትዝ የሚለኝ መሬት ላይ ቀሚሷ ተገልቦ የተኛች እናቴ ናት!! ሴቶቹም ዘገነኑኝ!! ሴትነቴም ዘገነነኝ!! ለውጥ የልምድ ውጤት ነው አላልኳችሁም? ለዛን ሰዓት ከመኪናው እና ሴቶቹ ሲይዙ ከማያቸው ውድ ስልኮች እና ሲያደርጉ ከማያቸው ዘናጭ ቦርሳና ጫማዎች በላይ የከዳሁት ሴትነቴን ክብር ማስጠበቅ መረጥኩ!! በየሄደበት በር ላይ መቆሙን ቀጠልኩበት!!
HTML Embed Code:
2024/05/04 06:43:18
Back to Top