TG Telegram Group Link
Channel: መባቻ ©
Back to Bottom
ሰለሜ ሰለሜ
------------
#ሚካኤል_እንዳለ
.
.
ሐገር አለ ብለሽ ፥ ልታስረጂኝ ያኔ
እንደ ላስታ ፍልፍል
ልታለሰልሺኝ ፥ ልትቀርጪኝ በወኔ
ታሪክን ሀ ብለሽ
ስትነግሪኝ ያቆምቁሽ
ወዲያው ያቋረጥኩሽ
እሱ ድሮ ነበር
ነበር ባይሰበር
.  .  .  . ያልኩበትን ምክኒያት
እኔም በተራዬ ላስረዳሽ የኔ እናት
አይተሽው ከሆነ
አዙሮ እኛኑ ለመግረፍ ጠምዝዞ
ሁሌ ከፊት ባለ በሚነዳን ሹፌር አለንጋ ተይዞ
አጭር የሚያስረዝም ሰለሜ ሰለሜ ሆኗል የኛ ጉዞ
ንፋሱን አምጣልኝ
-----------

( ሚካኤል እንዳለ )

ውሃ ጠማኝ ብትይ
አባይን በጭልፋ ፥ ቀድቼ አመላለስኩ
እንጨት የለም ብትይ
በኤሊው ጉልበቴ ፥ ጫካውን ተሸከምኩ
ቅዝቃዜው በዝቶ ፥ አየሩ ቢበርድሽ
እሳቱን በእጄ ፥ ይዤ ቀረብኩልሽ
ደሞ በጣም ሞቀኝ ፥ ስትዪ ሰምቼ
እፍ ስልሽ አደርኩ እንቅልፌን አጥቼ !
-
ብቻ ምን አለፋሽ
አንቺ ስትልኪኝ ፥ ያልሽውን ሳመጣ
ሂድ ስትይኝ ስሄድ ፥ ና ስትይ ስመጣ
በጠቆምሽኝ ቁጥር ቁልቁለት ስጋልብ ተራራ ስወጣ
ደከመኝ ሰለቸኝ
ብዬ አላውቅም ነበር ላፍታ'ኳ 'ባሳቤ
ውጪ ውረጂበት ተረማመጂበት ደረጃሽ ነው ልቤ
-
ብዬ ትልቅ ስልጣን ብሰጥሽ ንግሥና
እንደ 'ባላባት ልጅ ፥ ትዛዝሽ በዛና
ንፋስ 'ፈልጋለው አባረህ አምጣልኝ
የገባበት ገብተህ ጨብጠህ ያዝልኝ
ያልሽውን ሰምቼ ፥ ተስፋዬን ቆረጥኩኝ
ንፋሱን ለመያዝ እርቄ ስሯሯጥ ልጨብጥ ስለፋ
መፈለግሽ ገባኝ ፥ ካይንሽ እንድጠፋ
-
አሁን ላይ ሳስበው
እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው
በሚለው መፈክር
ትዛዝሽን ከ 'ሀ' እስከ 'ፐ' ስቆጥረው
ስህተት የለብሽም ፥ ልክ ነሽ እላለው
ከሰለቸ ሰው ልብ ካሎደደ ጋር ከመቀጠል አብሮ
እጅጉን ይሻላል ንፋስን በመዳፍ መጨበጥ አባሮ

@ethio_art
@ethio_art
@mebacha
@mecacha
12/12/12
_____

ሚካኤል_እንዳለ
.
.
ቁጥሩም አንደ ነው ፥ መልኩም ተመሳሳይ
እዝባሩ ነው ድንበር በመኃል ተጋድሞ የሰውን ልጅ ነጣይ
በቅርጽና ባይነት
እንደ መርፌ ዐይን አንድ ሆኖ ተሰርቶ
እዝባር ከተውበት እንዴት ይተዛዘን ሰው ከሰው ተያይቶ
-
እን'ዳንድ እና ሁለት
በመካከላችን ሳይኖርብን ስፋት
አግድሞ ተቸንክሮ እንደ ደራሽ ውሃ ከፍሎ የለያየን
እዝባሩ ቢነሳ ፥ ሶስተኛ ዘር የለም ሴትና ወንድ ነን
-
አይ እዝባር ድንበሩ
ምናባዊ ክሩ
የሃሳብ መስመሩ
በአንተ መጋደም ፥ አይናችን እያየ
ስንቱ ቋያ በላው ፥ ስንቱ በሳት ጋየ
ስንቱ ሰው ተሰዋ ፥ ስንቱ ሰው ተለየ
-
ከ'ንግዲህ አብቅቶ በእዝባር ተከፍሎ የ'መለየት ነገር 
ላናየው ድጋሚ ላይመለስ ከቶ ልክ እንደዚ ቁጥር
አንድዬ ይቋጨው እንደ ዛሬዋ ቀን የሐገሬን ችግር
ማነው ደደቡ ?
--------------

እስኪ በጥያቄ ልጀምር ፡፡ የዚህ IQ ጥናት የተካሄደው በእንግዚዘኛ ቋንቋ ነው ወይስ በግዕዘኛ ? አንድ እንግሊዛዊ ታዳጊን እና አንድ ኢትዮጵያዊን ታዳጊ በእንግሊዘኛ ቋንቋ መዝነህ ኢትዮጵያዊውን ደደብ ካልከው ልክ ነህ፡፡ ምክኒያቱም በግዕዝ ወይም በአማርኛ ቋንቋ ብትመዝናቸው እንግዚዛዊውም ደደብ ስለሚሆን ፡፡ እውቀት አንጻራዊ ነው ፡፡

በሌላ መልኩ ላስረዳህ በምስሉ ላይ ከምታያቸው እናት እና ኒውክሊየርን ከፈጠረው አንስታይን ፤ በ IQ ማን ይበልጣል ? አየህ ነጩ አለም እሱ በሚያውቀው እና በተረዳው ክበብ ውስጥ ወስዶ ይመዝንህ እና ደደብ ይልሃል፡፡ አንተም በሜዳህ ምህዋር ፤ በሃገርህ እሴትና በመንፈሳዊ ልእልና መዝነህ እሱን ደደብ ማለት እየቻልክ በማታውቀው ሜዳ አውርዶ ባሰመረልህ እንቧለሌ ውስጥ ከቶ ሲመዝንህ ሚዛኑ ላይ ወጥተህ ከቆምክ እንደ ጥጥ ትቀላለህ፡፡ ያም ሆነ ይህ ቅሉ እድሜ ልኩን በማያውቀው ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በሞተ የትምህርት ፖሊሲ በዛም ላይ የሴራ ታሪክ ተቀምሞ የተጋተ ትውልድ በአለም ሁለተኛው ደደብ ቢባል አይገርምም የሚገርመው አንደኛ አለመሆኑ ነው፡፡

ዛሬም ቢሆን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እየኖርን በዘመናዊው አለም ደሃ ብንሆንም በመንፈሳዊው አለም ብልጹግ ነን፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ እሴት ለአይኪው መመዘኛነት አይበቃም፡፡ ለምን ብለህ ከጠየክ ነጩ አለም እሱ የሌለውን ነገር ሁሉ የማያስፈልግ አድርጎ የመቁጠር አባዜ ስላለው፡፡ አንተህ ኖሮህ እሱ የሌለው ነገር ካለ ፕሩፍ ያልተደረገ ብሎ ያጣጥልብሃል ፤ እሱ ኖሮት አንተ የሌለህ ነገር ካለ ለእሱ አንደኝነት እና የበላይነት ማስረጃ አድጎ ያቀርብልሃል፡፡ ሁሌ አንደኛ የሞሆን አባዜ የተጠናወተው ምእራቡ አለም በሰፈረው መስፈሪያ ደደብ ነኝ ብሎ የተቀበለው ህዝቤ ነው የሚያሳዝነኝ፡፡

አውሮፕላንም ስራ መንኮራኩር ሰውን እንድ ሰው ቆጥረህ ማሰብ እስካልጀመርክ ድረስ ያንተ ዘመናዊነት እና ምጥቀት ብቻ የአይኪው መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንም በማስረጃ ላበጅልህ ፤ አፍሪካ በኮሬላ ወረርሽኝ በአስር ሚሊዮኖትች እዝብ ባለቀባት ዘመን እርዳታ ጠፍቶ ያ ሁሉ ህዝብ የአፈር ሲሳይ በሆነበት በዛው ጊዜ በአሜሪካን አንድ ግዛት ለውሾች ፋሽን ሾው ፕሮግራም ከ አራት ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ያሶጣ ድግስ ተዘጋጅቶ እንድነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ እጅጉን ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው በአፍሪካ በኮሬላ በሽታ ያለቁትን  ህዝቦች ለማትረፍ ይፈለግ የነበረው ከ ሁለት ሚሊየን ዶላር በታች ነበር፡፡ ሁለት ሚሊየን ዶላር ለሰው ልጅ ህይወት ጠፍቶ አራት ሚሊየን ዶላር ለውሻ ፋሽን ሾው ያወጣ ማህበረሰብ ነው እንግዲ እኛን በአይኪው ሚዛን ደደብ ለማለት ጥናት ያጠናው፡፡

እኔ ብቻ ልኑር (survival of the fittest) እያለ የሰውን ዘር ከእንስሳ በታች የሚቆጥር እና አፍሪካዊ ሲሞት ዝንጀሮ ነው የሞተው እያለ ከሚያስብ የነጩ አለም የህዋ ሳይንስ ምጥቀት ይልቅ ፤ ለእንስሳ ጡት የሚያጠባ ሩሩህ ማህበረሰብ አይኪው ለእኔ እጅጉን ይገዝፍብኛል፡፡
.
#ሚካኤል እንዳለ
"መልካም አዲስ አመት" እስኪ ሙት በሉኝ 😂
_______________________

የጎመን ድስት ውጣ
የገንፎ ድስት ግባ ዘንድሮስ አይሉም
በባዶ ማድጋ ገንፎን አያለሙ ጎመንን አይጠሉም
፡፡፡፡፡፡፡
ቀኑ ሲቀያየር
ሲለዋወጥ ቁጥር
አዲስም ብትሉ አሮጌውም ቢባል
አመት ለውጥ የለው ያው ይመሽ ይነጋል
የዘመን ነው እንጂ
የሰው አዲስ ካየን ብዙ አመት ቆይቷል
፡፡፡፡፡፡፡፡
ስለዚ ባካቹ ተለወጠ አትበሉን
ወትሮም ሊለወጥ ነው መፈጠሩ ዘመን
እፅዋት ይመስል ሰው ነው ተቸክሎ አልቀየር ያለን
፡፡፡፡፡፡፡
ጊዜ ከቆጠረ
ከሽራፊ ሰከንድ ቀንን ከቀመረ
ምን አማራጭ አለው
መሄድ ነው ወደፊት የዘመን ግዴታው
ሰው ቢለወጥ ነበር
''አዲስ'' የሚለው ቃል መልካም የሚሆነው
.
( #ሚካኤል_እንዳለ )
.
መልካም ነገ ይሁንላቹ 😂 እንኳን አደረሳቹ ፡፡

@mebacha
#ከጉድ_ዘመን_ወደ_እዬዬ_ዘመን ...
_________________________
( #ሚካኤል_እንዳለ )
.
ገና ከጅምሩ ከመስከረም መባቻ እንዲህ ያለ ነገር መስማት ገጠመኝ ነው ለማለት ይከብዳል ፡፡ መልካም አዲስ አመት ምኞት እንጂ እውን መሆኑን ዘንድሮም እንጃ  ፡፡ ከማስመሰል ይልቅ አዲስ ሰውነት ከመንግስት ባለስልጣናት ጀምሮ እስካልመጣ ድረስ አዲስ አመት የለም ፡፡ የሰኔ እና ሰኞ መግጠም ላይ ሲያሾፉ የነበሩ ሰዎች ፤ ሰኔና ሰኞ ሲገጥም ምን እንደሚያመጣ ከተረት በላይ በተግባር አይተውታል፡፡ ለወትሮውኑ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ ይባል ነበር አሁን መስከረም ጠብቶም ጉድ እንደጉድ መደመጡን ቀጥሏል ፡፡
.
መስከረም ከመባቱ  በአንደኛው እለት ሚስቱን ጨምሮ አራት ሰዎችን የገደለው የፌደራል ፓሊስ አባል ዜና ሰምተን ሳንጨርስ ዛሬ ደሞ በቤንሻንጉል ጉምዝ የመተከል ዞን ጭፍጨፋን ሰማን ፡፡ ነገ ደግሞ ምን እንሰማ ይሆን ? ከነገ ወዲያ…? መንግስታችንም ችግኝ ስለሚተከል ሰው ቢነቀል ችግር የለውም ያለ ይመስላል፡፡ ሰው አቅፎ የማያውቅ ባለስልጣን ችግኝ አቅፎ ፎቶ ሲነሳ ይውላል፡፡ ባለስልጣን የተባለ ሁላ ቢሮውን ትቶ ፌስቡክ ላይ መዋል ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል ፡፡ እኛ ስራ የሌለን እንኳ የማንፓስተውን ያህል ፎቶ ባልስልጣናቱ ሲፓስቱት ይውላሉ፡፡ ስሰጥ እዩኝ ፤ ስረዳ እዩኝ ፤ ሳበላ እዩኝ ማለት እንደ ስራ ተቆጥሯል ፡፡ ትራምፕ ነው ወይስ ፑቲን ደሃ ሲረዳ የሚያሳይ ፎቶ ተነስቶ የሚፓስተው ፡፡ ህዝብን መርዳት እና ህዝብን የረዱ መምሰል ለየቅል ናቸው ፡፡ እየታዩ ከመስራት ሳይታዩ መስራት ፍሬ እንዳለው ተዘንግቷል፡፡ ሙያ በልብ ነው የሚለው የአባቶች ብሂል ለሰለጠነው ሐገር እንጂ ለእኛ ባዳ ሆኗል ፡፡ አንዳንድ ባለስልጣናትማ ፤ ይባስ ብለው የሚለብሱትን ልብስ ለማስተዋወቅ እስከሚመስል ድረስ በጥልፍ ባማረ ነጭ በነጭ ፏ ብለው መፓሰት ሁላ ጀምረዋል ፡፡ ሰው ሲያልቅ ህዝብ ሲጫረስ ግን ዝም ጭጭ ነው ፡፡ ለነሱ አመቱን ሙሉ አመት በዓል ነው፡፡ ለደሃው ህዝብ ግን አንድ ቀን ውሎ ማደር ጭንቅ ሆኗል፡፡ ህዝብ መውጫ መግቢያ ቸግሮት ሰው መሆኑን እስኪጠላ ድረስ መአት በሚሰማባት ሐገር ላይ የባለስልጣናቱ የፌስቡክ ላይ ውድድር እና ፋሽን ሾው ማብዛት ከግራም በላይ ሆኖብናል ፡፡ እኔን ማንም አይነካኝ በሚል እሳቤ የሚደረግ ጉዞ ''እውር እውርን እንደሚመራው '' መጨረሻው ገደል ነው፡፡ ምናገባኝ ማለት በኋላ የሚያመጣውን መዘዝ  አላስተዋሉት ይሆናል ፡፡ ትላንት ህዝብ ሲቸገር ምናገባኝ ያሉ ዛሬ የት እንዳሉ አይታችሁ ተማሩ፡፡ ፍርድ ከመለኮት እንጂ ከምድር ተገኝታ አታውቅም፡፡ የምታስቡት ስንት አመት መቀመጥ አለብኝ የምትለዋን ቀመር እንጂ የዜጎችን ስቃይ አይደለምና ፡፡ መንግስት ከመንግስት በደም የሚወርሰው በሽታ እስከሚመስል ድረስ ማስመሰል እና ሴራ ካንሰር ሆኖብናል፡፡
.
ከለውጡ በላይ የናፈቀን ነገር ቢኖር ''ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዋች እና መንግስት መቼ እንደሚተዋወቁ '' ማወቅ ብቻ ነው፡፡ ሚዲያው ሁሉ ዜና ሲሰራ '' ማንነታቸው ባልታወቁ '' ካላለ ዜና የሰራ አይመስለውም ፡፡ ግልጽነት እና ተጠያቂነት በሌለበት በዚህ አካሄዳችን ከቀጠልን ''ከሰማይ የመጡ ዩፎዎች አደጋ አድርሰው ሄዱ'' የሚል ዜና በቅርቡ መስማታችን አይቀርም፡፡ ከእንጀራ ጥያቄ ተላቆ ለህሊናው የሚሰራ የመንግስት አካል እንደ ምንሊክ ድኩላ ተመናምኗል፡፡ ሁሉም ዛሬን ከኖረ ነገንም የሚኖር ይመስለዋል፡፡ እከርማለው ብለህ ስራ እሞታለው ብለህ ኑር የተባለውን እረስቷል ፡፡ እከርማለው ብሎ የሚሰራ መሞቱን ስለሚያውቅ ህዝብን ስለ እውነት ያገለግላል ፡፡ እኖራለው ብሎ የሚያምን ግን መሞቱን ስለሚረሳ በህዝብ ላይ መከራ ሲያወርድ ይኖራል፡፡ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ ማየት ተባባሪነትን ያመጣል፡፡
ይህ ደግሞ የኖርንበት ነውና አዲስ የተባለውን ለውጥ አዲስነት ያጠራጥረዋል፡፡ ለሰው የሚታይ ፊትን ብቻ እየታጠቡ ገላዬ ንፁህ ነው ማለት አይቻልም፡፡ መንግስት ከወረዳ ጀምሮ እስከ አናቱ እራሱን ካላፀዳ የዚህች ሐገር ብልፅግና አንድ ወደ ፊት ሁለት ወደኋላ ይሆናል፡፡ ይህን እያዩ እንዳልዩ ዝም ማለት ወንዝ ወዶ ውሃ ልቅዳ እንዳለው ጨው ተሸርሽሮ ማለቅን ያስረሳል፡፡ቆርጠው የሚለኩ ባለሙያዎችን ይዞ መጓዙ ትርፉ ቁርጥራጭን ማብዛት ነው፡፡ ለክተው የሚቆርጡትን ብልሆች በሞሉባት ሐገር  የቆርጦ ቀጥል መዋቅርን ማፍረስ ካልተቻለ ሰላም አይኖርም፡፡
.
ወደ ክበባችን እንመለስና ስለተነሳንበት እርዕስ እናውጋ ፤ ዘመነ ዩሐንስ ሰማይ የተደፋብን ያክል ከብዶን አለፈ፡፡ ለማቴዎስም አስረክቦናል፡፡ ማቴዎስም ከጅምሩ ጉድ እያሰማን ነው፡፡ የአቡሻህር ሆነ የመርሐ እውራን ወይም የባህረ ሐሳብ እና የፍካሬ ከዋክብት ቀመር ሊቃውንት  እንደሚናገሩት ከሆነ በዘመነ ማቴዎስ ከረሃብ ይልቅ ጦርነት እጅጉን ይበዛል ፡፡  ይህንም ለማረጋገጥ የታላቁን ሊቅ (የሐሽማል ደራሲ) የማእበል ፈጠነን ገጽ መበርበር ብቻ በቂ ነው፡፡ በትንሹም ቢሆን ጠቁሞናል፡፡
.
መቼም ዘንድሮ ጸሎታችን እራሱ ካልተቀየረ ዋጋ የሚያስገኝ አሎነም፡፡ ስለ ጻድቃን ብለህ ሳይሆን ስለ ድንቁርናችን ብለህ ማረን ማለቱ ሳያዋጣ እንደማይቀር ዲያቆን ብርሐኑ አድማስ ጠቁሞናል ፡፡ በቃ እንደ እንስሣት ቁጠረን ማለቱ ሳይቀለን አይቀረም፡፡ እሱንም ከእንስሳቱ ከተሻልን ነው፡፡ ምክኒያቱም በጻድቃ ጸሎት መአቱን እናልፈው ዘንድ ገና ብቃቱ እራሱ የለንም ፡፡ አንዳንዴ እንደ ሎጥ የሚለመንለት ሰው መሆን እስካልቻልን ድረስ የማንም ጸሎት አያተርፈንም ፡፡ ሰዶምን በሚያክል የሐጢያት ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረው ሎጥ ፤ በሚሰማው እና በሚያየው ነገር እጅግ ነፍሱን ያስጨንቃት ነበር ፡፡ በዚህም ጭንቀቱ የተነሳ የአብርሃም ፀሎት አግዛው ከዞሐር ተራራ ተሸሽጎ ከሰዶም ጥፋት ዳነ፡፡ ዛሬስ ? ከሰዶም ዘመን ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ስንት መአት እና ውርጅብኝ እያየን ነፍሳችንን እናስጨንቅ ይሆን ? የሞት ዜና በሰማን በደቂቃ ልዩነት ቻናል ቀይረን በዘፈን አልጨፈርንም ? እና ታዲያ ምናችንን አይቶ በፃድቃን ፀሎት ይማረን ? ፡፡ እንደ ሰራጵታዋ ታላቅ ሴት ሊበረከት የሚችል ትንሽ የእምነት ዘይት እስካልያዝን ድረስ የእነ ኤልሳ በረከት ወደ እኛ ሊመጣ አይችልም ፡፡
.
ብቻ የመቋጫው ዘመን ሲደርስ ''እባክህ አምላኬ አትመራመረኝ
እንደ በላሄ ሰብ በጥቂት ውሃ ማረኝ '' ለማለት እንችል ዘንድ ጥቂት ውሃ'ኳን ብትሆን ከኛ ይፈለጋል ፡፡ በዜሮ ምግባር በጻድቃን ጸሎት ብቻ ማረኝ ማለት በራሱ ፈጣሪን መፈታተን ነው ፡፡ ጥቂት ጠብታ ሲኖር ብቻ ነው የእመቤታችን ፀሎት ተጨምሮ እንደ በላሄ ሰብ በህይወታችን ስራ የሚሰራው፡፡ አንድዬ ይህን ዓመት'ኳ ከእንደዚ አይነት ወሬ እናርፍ ዘንድ የእርሱ ፍቃድ ይሁን ፡፡ መልካም አዲስ አመትን ሳይሆን መልካም አዲስ ሰውነትን ያምጣልን፡፡ መሪዋቻችንም ቢሆኑ ታክቲካቸውንና  ልብሳቸውን ሳይሆን ህሊናቸውን የሚቀይሩበት ዘመን ያድግልን፡፡ ሌላ ምን ይባላል እዬዬም ሲደላ ነውና ፡፡ ቢያንስ ተሳቀን ሳይሆን ደልቶን እዬዬ የምንልበትን ቀን ያምጣልን፡፡    
ችርስ
____

ወይኑን እንዳይጠጣ የሚጥመውን
ህዝቡን አሰከሩት ፥ ግተው ጠላውን
በልኩ ቢሆንስ
የፍቅር ማጀቢያ ፥ ጠላም ባልተጠላ
አቆሰሉት እንጂ ባዶ ሆዳችንን ሞልተው በአተላ
ወሮትሮም በሰው ልፊያ
ገላጋይ አትራፊ ፥ በሆነባት ዓለም
የደሃዎች ግጭት ፥ ችርስ ነው ለሐብታም 
.
#ሚካኤል_እንዳለ

@mebacha
አፉማ የግልሽ ፥ ሰንደቋም የኔ ናት
ከንፈርሽ ይቅርብኝ ፥ ሐገሬን ልሳማት

(ሚካኤል እንዳለ)

@ethio_art
@mebacha
የፍጥረት ውሃ ልክ
--‐----------------
#ሚካኤል_እንዳለ
.
ከሴት ልጅ የፀዳች ፥ ዓለምን ፈጥሬ 
ዠርገግ ባልኩባት ፥ ባረፍኩባት ኖሬ
የምትል ቋጠሮ
ቤት መምቻ እሮሮ
. . . አስቤ ልገጥም
ለካስ ሴት ከሌለች እናትም አትኖርም !!
የሚል መደምደሚያ ከባድ ስንኝ ቢያንቀኝ
ሰረዝኩት ሃሳቤን ወንድ የሆንኩበት ሴትነት ቢገባኝ
. . .
እናማ ካዘለች
ፈትላ ካዋሃደች
ከተሰጣት ዘንዳ
መምሰል ጽጌሬዳ
እሾህን ከጣዕም በአድ ላይ ገምዳ
ካስተባበረችው ፥ በተፈጥሮ ፀጋ
መቻል ግዴታ ነው ማሯን እስከላሱ ንቢት ስትዋጋ
. . .
በሚለው እውነታ
ቁጭ አርገው ከግርጌ 'ካውድማው ጉብታ
እንዲ ብለው ነበር ሲመክሩኝ 'የኔታ . . .
ሃላፊውን ችለህ ለመኖር ከፈለክ ዘላለም አብረሀት
በፍጥረት ውሃ ልክ በ'ናትነት ይሁን ሴትን ስትለካት !!!

@mebacha
@mebacha
አንተን የሚያስንቁ ፥ 'ባይናችን ስላየን
ለስከዛሬው ሁሉ ሰይጣን ይቅር በለን
.
#ሚካኤል_እንዳለ
ያንተ ልጅ ሲበላ የኔ ልጅ ያለቅሳል
ያንተ ቤት ተከድኖ የኔ ቤት ያፈሳል
ያንተ መሬት ታርሶ የኔ ዳዋ ለብሷል
ወይ ካንተ ወይ ከኔ ያንዳችን ቀን ደርሷል
ጊዜ መሃንዲስ ነው ይሰራል ያፈርሳል
#አትማረኝ 🙏
---------------
#ሚካኤል_እንዳለ
.
ታመው የተነሱ
እግዜርን እረሱ
የሚል ተረት አለ ፥ እሱን ያስታወሰ
ከዕለታት አንድ ቀን ፥ በኔ ላይ ደረሰ
፡፡፡፡
ለ'ለታት ሰባት ቀን ፥ ህመም ተሸክሜ
ከቤቴ ወሳንሳ ለአንድ ሱባ'ዬ የጎን ተጋድሜ
በሞትና በህይወት
በመሄድ በመምጣት
በሁለት አቅጣጫ ፥ ሥጋዬ ሲገፋ
ከቤት ስላልወጣሁ ፥ ሃጢያት 'ካይኔ ጠፋ
፡፡፡፡
ወትሮም በደካሚ
በሌለበት ቋሚ
በዛ ዝለት ጊዜ ፥ ከጓዳው ተኝቶ
እንደ ባህታዊ ፥ በሩን ደጁን ዘግቶ
ከጊዚያዊ ታዛ ፥ ከዚህ ቅዘት ዓለም
እረፍትን ፍለጋ ፥ በዐቱን ለሚያልም
ገዳም እንደመግባት
ለነፍስ እፎይታዋ ፥ ነው ለካ መታመም !!
፡፡፡፡
ታዲያ ምን ያደርጋል
ተኝቼ አልተኛሁኝ
ቀርቼ አልቀረሁኝ
በሳምንቱ እራስጌ ፥ ከህመሜ ዳንኩኝ
ከደጄ እንደወጣው
በመንገድ ላይ ዳሌ ፥ 'ካለም ተዋወኩኝ
፡፡፡፡፡
ለዚህ ለዚህ ነበር
ከቤት ውስጥ መተኛት መታመም ጥቅሙ
እንደ ጥሩ መናኝ በርን አዘግቶ ይለያል 'ካለሙ
እናም ተመስገን ነው በደዌ ሲመቱ ሲታመሙ ማለት
ጉድጓድ እስካልገቡ እድሳት ነውና ህመም ለሰውነት
፡፡፡፡፡
እኔም ይሄን ይዤ
ሥጋዬን በድካም ክፉኛ ሰቅዤ
እንደ ጣናው ፃድቅ እንደ አባ አትማረኝ
በሽታዬ እንዳይድን ፥ ፈጣሪን ለመንኩኝ
ከዝሙት የሚያርቅ ህመም ምንኩስና መሆኑን አወቁኝ
.
#ሚካኤል_እንዳለ

@mebacha
ማን ይብላን ?
-----------

ስለጠፋ ታማኝ ተመራጭ የሰው ዘር
ጌታ ውረድና ፥ ምርጫ ተወዳደር
እኛም በዚው ይብቃን ትለፍ ይቺ ምድር
ተብሎ ቢፈረድ ማንም አይማርም
ስልጣን ያወራቸው
እረስተዋልና  ፥ መሬት ማለፏንም 

ብለን
አስተምረን
እውነትን ተናግረን
'ሚሰማ ብናጣ ፥ ነፍሳችንን ይዘን
ከጅብ አፍ ለመዳን ዛፍ ብኖጣም ሸሽተን
እጅጉን የጠማው ፥ ነብር ተቀበለን

ስለዚህ ማን ይብላን ? ሆኖብናል ምርጫው
ጅብም ቢሉ ነብር ፥ መንጋጋቸው ሥል ነው
በሁለቱም ቢሆኑ ፥ ለ'ኛ ሞት አንድ ነው

#ሚካኤል_እንዳለ
ለጉርሻ ተናንቀህ ፥ ለቅምሻ ስትለፋ
መሶቡ ተወስዶ ፥ 'ራብ እንዳይደፋህ
ወትሮም ተጋፊ ሰው ብርጭቆን ይመስላል
ቦታ እንደጠበበው ፥ አሥሬ ይጋጫል
እንግዲ ይፈታ ፥ ትርጉሙን እወቀው
ጉርሻው ዘረኝነት ፥ መሶቡም ሐገር ነው
.
#ሚካኤል_እንዳለ
.
ጉርሻ ሳይሆን መሶብ ያስረከቡህን አባቶች አስብ ፡፡
'ላምላኩ ሊታረድ ፥ በአባቱ ካራ
ይስሐቅ ሊሰዋ ፥ ሲወጣ ተራራ
አዘቅዝቆ ቢያየው
ያ እግዜር ጸፀተው
ሞቱን ላለማየት ፥ በበጉ ለወጠው
ይህው ዛሬ ደርሶ
ሰው ከበጎች አንሶ
በእግዜሩ ቦታ ፥ ተረኝነት ነግሶ
ከሰው ልጆች በላይ ግዑዛን ከበሩ እንስሶች ተለቁ
በግፈኞች ፍትህ በጎች ተቀምጠው ይሳቆች አለቁ
.
#ሚካኤል_እንዳለ


@MEBACHA
#ግጠምልኝ
------------------
.
ሚካኤል እንዳለ
.
ለመልክዐ መልክሽ ፥ እጅ መንሻ ቃላት
ለውዳሴ ገላ ፥ የሚሆን የቤት ምት
ከፊደላት ፈትለህ ፥ ግጠምልኝ ላልሽው
እንግዲያስ ያውልሽ ፥ ግጥሜን ቅመሽው
- - -
የጣና ዳር እንኮይ ቁመተ ለግላጋ
የገነት ቄጤማ ፥ የጊዮን ዳር ሎጋ
የገላሽ ንጣቱ ፥ እንደ ግምጃ አለላ
ከንፈርሽ እንጆሪ ፥ የስንዴ ራስ ዛላ
እያልኩኝ ጽፊያለው
ግጠም ብለሽኛል ይህው ገጥሜያለው
- - -
እንቡጥ ጽጌሬዳ ፥ የመሰለ ጉንጭሽ
ለቀመሰው ጣፋጭ ፥ እ'ዳገዳ ጥንቅሽ
የግንቦት ሰማይ ነው ፥ የቆዳሽ ጥራቱ
የጠረንሽ ነገር ፥ አልባስጥሮስ ሽቱ
እያልኩኝ ጽፊያለው
ግጠም ብለሽኛል ይህው ገጥሜያለው
- - -
ፀጉርሽ ጢስ አባይ
የምድር መቀነት ፥ ወርዶ እማያበቃ
አይንሽ ብሩህ ኮከብ የሚያስንቅ ጨረቃ
ብርቱካኑ ፊትሽ ፥ ቢታኘክ ቢመጥጥ
እንደ ኤደን አፍላግ ጥምን የሚቆርጥ
እያልኩኝ ጽፊያለው
ግጠም ብለሽኛል ይህው ገጥሜያለው
- - -
ግና ሳስታውስሽ
በስተመጨረሻ ይሄንም ልንገርሽ
እኔ ለዚህ ውበት ቃላት ስደረድር
እንደ ባለ ቅኔ ፥ ፊደላት ስከምር
እጅጉን አትሳቂ
በደስታ ፍልቅ'ልቅ ፥ ብለሽ አቱደቂ
ኋላ ለሚፈርሰው
ለአፈር መግጠሜ ፥ መሆኑን እወቂ
መርገጫ እየጠፋ ፥ ደም ሞልቶት መንገዱ
መርጦ አልቃሽ ይሉናል መርጠው እራረዱ
በቅን አሳላፊ ፥ በሃገሩ ጠፍቶ
ከኋላ ቀርተናል ፥ ደም'በኛ በርክቶ
ሲኦል ማነው ?
--------------------
ሰው በኃጢያት ግዞት
ተንኮል እንደ ጢሻ ሥጋ ነፍሱን አስሮት
ላይመለስ ዳግም አንዲቷን ሞት ሲሞት
ቅጣቱ መቃጠል
በርባሮስ ውስጥ መጣል
አንደ ነዌ መንደድ ከ'ቶን እሳት መሃል ?
የለም የለም
ሲኦል ማለት እሱ አይለም
ትርጉሙን አታርቀው
ፍካሬውንም እወቀው
:
ያኔ ስቀመጥ በማህጸን
ለ'ዝች አለም ስታጭ በሰውነት ስወጠን
ደሜን ከሄዋን አጠንፍፌ
ከ አዳም አጥንት አጥንቴን ቀፍፌ
በአካል በአዕምሮ ጎልብቼ
ለመወሰነ ስብቃ ውሃን ከእሳት ለይቼ
:
ቀስ በቀስ ስፈረጥም
ስሜቴ ሲፈላ ህሊናዬ ክፋት ሲያልም
ላም ባልዋለበት ኩበት አፈሳ
የተፈጠርኩበትን አላማ ስረሳ
:
ላፍታ ምቾት ስማልል
ከመቅደሱ ጠረን ከእጣኑ ጢስ ስኮበልል
እንደማይጠራ አሳማ ባ'ለም ጭቃ ስንከባለል
የመስቀሉን ዋጋ ትቼ
ለሥጋና ደም አድልቼ
በነፍስ እያለው በምድር ከእግዜር ከተለየ አይኔ
ሲኦል ማለት ይህ ነው ለኔ
.
(ሚካኤል እንዳለ)
HTML Embed Code:
2024/04/25 18:12:17
Back to Top