TG Telegram Group Link
Channel: ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan
Back to Bottom
††† እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት እና ለአቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት †††

††† በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::

በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን: ኒቆዲሞስን . ..) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::

በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6 ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ:: ለ6 ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ:: በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው::
"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ:: (ሉቃ. 7:18) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ:: ጌታም ከ72ቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: (ሉቃ. 10:17)

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል:: በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ72ቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም:: በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7 ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል:: 8ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት: ማሕደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ. 6:5)

አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት' ሲባል እንደዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ 'በራት ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለ 1 ዓመት ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ እሰፋ' አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው' ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት::

እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋየን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል (የመምሕሩ ርስት ነው) ሔደ:: ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ:: መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ መላእክትም ተሰማ:: ሕዝቡና ዻዻሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት:: እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ5 ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት:: ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው:: መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ አላት: አምላክ ለዚህ አድሏታልና:: እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ::

ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች:: በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት 17: ዕረፍቱ ጥር 1: ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም 15 ቀን ነው::

††† አቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ †††

††† ጻድቁ በ14ኛው ክ/ዘመን ከተነሱ አበው አንዱ ሲሆኑ ገዳማቸው ደብረ ሐንታ ወሎ ውስጥ ይገኛል:: አቡነ ገብረማርያም በተጋድሏቸው: በተአምራቸውና በወንጌል አገልግሎታቸው ይታወቃሉ:: ይልቁኑ ግን የሚታወቁት ለእመቤታችን በነበራቸው ፍቅር ነው:: ያንን ጥዑም ማሕሌተ ጽጌ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር ሆነው የደረሱ እርሳቸው ናቸውና:: በገዳማቸው ብርሃን እስኪበራ ድረስ በንጹሕ የማኅሌት አገልግሎታቸው ድንግል ማርያምንና ቸር ልጇን አስደስተው: በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

††† አባ ጴጥሮስ ዘጠራው †††

††† በደብረ ጠራው: ሠንሠለት ለብለው: ከእህል ተከልክለው: በጾምና ጸሎት ተወስነው ይኖሩ ነበር:: ፈጣሪን 24 ሰዓት "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ እያመሰገኑ ሲርባቸው ደረቅ ሣር ነጭተው ይበሉ ነበር:: ከብዙ ተጋድሎ በኋላም ያረፉት በዚህ ቀን ነው::

††† አምላከ ቅዱስ እስጢፋኖስ በረድኤት ይጐብኘን:: ከወዳጆቹ በረከትም ተካፋዮች ያድርገን::

††† መስከረም 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት(ፍልሠቱ)
2.አቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ
3.አባ ዼጥሮስ ዘሃገረ ጠራው
4.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ (ፍልሠቱ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና
††† "እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት::" †††
(ሐዋ. ፮፥፰-፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††


https://hottg.com/mahberememenan
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ መስከረም ፲፮ (16) ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለቅድስት ሃገር #ኢየሩሳሌም: ለቅዱስ #ጦቢት እና ለአባ #አጋቶን_ባሕታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ሕንጸታ_ለኢየሩሳሌም +"+

=>ኢየሩሳሌም በብሉይም: በሐዲስም ቅድስት ሃገረ
እግዚአብሔር ናት:: '#ኢየሩ' ማለት 'ሃገር' ማለት ሲሆን
'#ሳሌም' ደግሞ 'ሰላም' ማለት ነው:: ስለዚህ በቁሙ
'ሃገረ ሰላም': '#ሃገረ_ክርስቶስ' ማለት ነው::

+ኢየሩሳሌም የሚለው ቃል በቁሙ ቅድስት ሃገርን
ሲመለከት በምሥጢሩ ግን የቤተ ክርስቲያን: የመንግስተ
ሰማያት እና የአማናዊት ሃገረ ሰላም #ድንግል_ማርያም
መጠሪያ ነው:: ኢየሩሳሌምን በከተማ ደረጃ የመሠረታት
ታላቁ ካህን #መልከ_ጼዴቅ ሲሆን 'ንጉሠ ሳሌም'
ተብሎም ኑሮባታል::

+ይህች ቅድስት ሃገር በብሉይ ዘመን እግዚአብሔር
በረድኤት ቢገለጥባት: ጻድቃነ ብሊት ቢኖሩባት
ተቀድሳለች:: በሐዲስ ኪዳን ግን አምላካችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ 33 ዓመት ከ3 ወር ያህል
የድኅነ ትሥራውን ቢፈጽምባት: ለድንግል ማርያምና
ለብዙ ቅዱሳን ቤት ብትሆን የበለጠ ተቀድሳለች::

+ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በብዙ ድካምና
ወጪ ሊያዩዎት ይጉዋዛሉ:: የቀደመው ዘመን
አባቶቻችንም ይህችን ቅድስት ከተማ ለመሳለም እስከ
ደም ጠብታ ከፍለዋል::

+ወደ ዋናው ጉዳያችን እንለፍና የኢየሩሳሌምን መታነጽ
እንይ:: ኢየሩሳሌም በአሕዛብ እጅ ብዙ ጊዜ ፈርሳ
ታንጻለች:: እኛ ግን ዛሬ የምናከብረው የከተማዋን
መታነጽ ሳይሆን በከተማዋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ
መንገድ በአንድ ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት
መታነጻቸውን ነው:: ይሕስ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ከክርስቶስ ዕርገት 300 ዓመታት በሁዋላ ለቤተ
ክርስቲያን የተነሳችው #ቅድስት_ዕሌኒ በጐ ሃሳብ
በሕሊናዋ ተመላልሷልና ተነሳች::

#ጉባኤ_ኒቅያ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ልጇ ቆስጠንጢኖስ
በነገሠ በ20 ዓመቱ በ227 ዓ/ም አካባቢ ቅዱስ ዕጸ
መስቀሉን ትፈልግ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች::

+መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችበት ታሪክ ለነገ ይቆየንና
መስቀሉን ካገኘችው በሁዋላ በሙሉ ከተማዋ ላይ
አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ከልጇ ጋር ተስማማች::

+ለሕንጻው የሚሆን ብዙ ወርቅ: ብርና እንቁ ጭና
ማምጣቷን የተመለከቱት #አባ_መቃርስ (የኢየሩሳሌም
ሊቀ ዻዻስ ናቸው) "ልምከርሽ! ቤተ ክርስቲያኑን
በጠንካራ አለት ላይ ሥሪ:: ወርቅና ብሩን ግን ለነዳያን
በትኚ" ስላሏት በአካባቢው ላሉ ነዳያን ታላቅ ፌሽታ
ሆነ:: እጅግ ብዙ ሠራዊት: ብዙ ሺህ ሠራተኞች
ታጥቀው 80 አብያተ ክርስቲያናትን ያንጹ ጀመሩ::

+ሥራው ረቂቅና ብዙ ሥለ ነበረ እጅግ አድካሚ ነበር::
ቅድስት ዕሌኒ ሃገሪቷን በቤተ መቅደሶች መሸፈን ስለ
ፈለገች እንዲታነጽ ያዘዘችው የቤተ ክርስቲያን ቁጥር 80
ደረሰ:: እነዚህም ጌታ ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ
የረገጣቸውና #እመ_ብርሃን የረገጠቻቸው ቦታዎች
ናቸው::

+#ቤተ_ልሔም: #ዮርዳኖስ: #ደብረ_ሊባኖስ:
#ደብረ_ታቦር: #ደብረ_ዘይት: #ጐልጐታ: #ጌቴ_ሴማኒ:
#ቤተ_ሳይዳ: #ጽርሃ_ጽዮን ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
በአካባቢው ያሉ ነዳያን ሳይርባቸው: ሠራተኞችም ደሞዝ
ሳይቸግራቸው: 80ው አብያተ ክርስቲያናት በፈጣሪ
ረዳትነት: በ10 ዓመታት ታነጹ::

+ቀጥሎም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ በዓለም ያሉ
ታላላቅ ቅዱሳን ሊቃነ ዻዻሳትን ጠርቶ: ሁሉም እስከ
መስከረም 15 ቀን ወደ ኢየሩሳሌም በተሰበሰቡበት
የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ቤት በአንድ ላይ
ሲከበር ከዝማሬው ብዛት: ከአምላክ ጸጋ የተነሳ
በከተማዋ ታይቶ የማይታወቅ ሐሴት ተደረገ::

*ኢየሩሳሌም ፍጹም አጊጣ እስከ መከራ ቀን (አሕዛብ እስከ ተነሱበት) ቆይታለች::

+"+ #ቅዱስ_ጦቢት (ጻድቅ ነቢይ) "+

=>ከክርስቶስ ልደት በፊት እሥራኤላውያን ክፋትን
ሲያበዙ ጠላት መጥቶ ይማርካቸው: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ
በድንቅ ተአምር ይወጡ ነበር:: ሕዝቡ ሲማረክ ነቢያት
እረኞች ናቸውና ያለ ጥፋታቸው አብረው ይማረኩ ነበር::
በዚያም ሕዝቡን ያስተምራሉ: ያጽናናሉ::

+በተመሳሳይ እሥራኤላውያን ተማርከው ወደ #ነነዌ
በወረዱበት ወራት ጦቢት የሚሉት ደግ ሰው
በመካከላቸው ነበር:: ይህ ደግ ሰው ከምርኮ በፊት
መልካም አምልኮት የነበረው: አሥራቱን በኩራቱን
የሚያወጣ: ለነዳያን የሚራራ ነበር::

+ከተማረኩ በሁዋላም ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋራ ሲቀላቀሉ
እርሱ ንጽሕናውን ጠብቆ እግዚአብሔርን ያመልክ ነበር::
ቅዱስ ጦቢት በተለይ የሞተ ሰው ሲያገኝ ሳይቀብር
እህል አይቀምስም ነበር:: በዚህም ምክንያት የዘወትር
ጦመኛ ነበር::

+ይሕ ቅዱስ እድሜው 58 በሆነ ጊዜ ዓይኑ ጠፋ:: ብዙ
በመሰቃየቱም ሞቱን ለመነ:: በሌላ አቅጣጫ ደግሞ
#ሣራ 'አስማንድዮስ' የሚባል ጋኔን 7 ባሎቿን እየገደለ
አሳቅቁዋት ነበርና እርሷም ሞቷን ተመኘች::

+እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ: #ቅዱስ_ሩፋኤል
አዛርያን መስሎ የጦብያና የሣራን ጋብቻ ባርኩዋል::
ጋኔኑንም በጥልቁ አስጥሞታል:: በዓሣ ሐሞትም
የጦቢት ዓይኑ በርቶለት በእድሜው ላይ 100 ዓመታት
ተጨምረውለታል:: ቅዱስ ጦቢት ብዙ ሕብረ ትንቢቶችን
ተናግሮ በ158 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል::

+"+ #አባ_አጋቶን_ባሕታዊ +"+

=>ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው
ይኖራል ብየ አልገምትም:: እርሱ ታላቅ ጻድቅ: ገዳማዊና
የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል
ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል::

+ይህንን ቅዱስ #ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር
ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ:
አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት
ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያንን
ሰላምና ደስታ ያሳየን:: ከበዓላቱ ከሚገኘውም ጸጋ
በረከት አይለየን::

=>መስከረም 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ሕንጸታ ለኢየሩሳሌም
2.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
3.ቅዱስ ጦቢት ነቢይ
4.ቅዱሳን ጦብያና ሣራ
5.አባ አጋቶን ባሕታዊ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/
ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ
7.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

=>+"+ ወደ #እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ
ደስ አለኝ::
#ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ::
ኢየሩሳሌምስ እርስ በርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ
ተሠርታለች . . .
ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን
አልሁ::
ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ
መልካምነትሽን ፈለግሁ:: +"+ (መዝ. 121:1-9)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://hottg.com/mahberememenan
✝️✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✝️

✝️✞ እንኩዋን #ለብርሃነ_መስቀሉ እና #ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✝️

✝️#ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል✝️

=>ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ #ማርያም_እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ከግራ ቁመት:
¤ከገሃነመ እሳት:
¤ከሰይጣን ባርነት:
¤ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

=>+"+ እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ +"+ እንዳለ ሊቁ::

+ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ #ትዕምርተ_መስቀል ናት::

+እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. 4:15) ጀምሮ
¤#ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት (ዘፍ. 22:6):
¤#ቅዱስ_ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. 28:12):
¤ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ (ዘፍ. 48:14):
¤ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው #የሙሴ_በትር (ዘጸ. 14:15):
¤#የናሱ_ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት (ዘኁ. 21:8) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

+#ቅዱስ_ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: (መዝ. 59:4)

+በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "#መስቀል_ብርሃን_ለኩሉ_ዓለም: #መሠረተ_ቤተ_ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

+#ቅዱስ_ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: #ብርሃነ_ዓለም #ቅዱስ_ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: (1ቆሮ. 1:18, ገላ. 6:14)

+አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: #ኢየሱስ_ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

+ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

+በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::

+"+ #በዓለ_መስቀል +"+

=>#መድኃኔ_ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም::

+መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ270 ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ::

+ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት #እሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ #ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ #ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች::

+መስከረም 17 ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት 10 ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ10 ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም 17 ቀን ተቀድሷል::

+ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ #አፄ_ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ #አፄ_ዘርዓ_ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (#ግሸን_ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል::

+"+ #ቅዱስ_አውዶኪስ_ቀሲስ +"+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ #ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ (ሰማርያዊ) ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ #ጐልጐታ ነን" አሉት::

+እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

+ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

+አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::

+"+ #ቅድስት_ታኦግንስጣ +"+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ #ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ #ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

=>አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

=>መስከረም 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት
3.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
4.ቅዱስ መቃርስ ሊቀ ዻዻስ
5.ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ
6.ብጽዕት ታኦግንስጣ ሮማዊት
7.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: +"+ (1ቆሮ. 1:18-23)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://hottg.com/mahberememenan
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለአበው #ቅዱሳን_ኤዎስጣቴዎስ_አኖሬዎስና_ማር_ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ረባን ✞✞✞

=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው #ክርስቶስ_ሞዐ እና #ስነ_ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም #ማዕቀበ_እግዚእ (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::

+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ በመሆናቸውም የዘመኑ አበው 'ዳግማዊ እስጢፋኖስ' እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: 'ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው: ባርኩዋቸው ዐረገ::

+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት #ቀዳሚት_ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

+በመንገድም ወደ ባሕረ #ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: #ሚካኤል በቀኝ #ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::

+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ #መርምሕናም ተቀብረዋል:: ዛሬ #በኢትዮዽያ: #ኤርትራ: #ግብጽና #አርማንያ ይከብራሉ::

+"+ #አቡነ_አኖሬዎስ_ጻድቅ +"+

=>እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ 'ታላቁ አኖሬዎስ' ይባላሉ:: በዚህ ስም ከሚጠሩ አባቶች ዋነኛው እኒህ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት #ሙገር አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቻቸውም #ሰላማ እና #ክርስቶስ_ዘመዳ ይባላሉ::

+ጻድቁ ከአቡነ #ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ናቸው:: በወንጌል ትምሕርት ከመሞላታቸው ባሻገር ፍጹም መናኝ ስለ ነበሩ እጅግ ደፋር ነበሩ:: የትኛውንም ስሕተት ፊት ለፊት ይናገሩም ነበር::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ ጌታ "በአንተ ፈንታ አኖሬዎስ ቀሪ ጣዖት አምልኮን ያጠፋል" ብሎ ነግሯቸው ነበር:: ይኸውም አልቀረ ጻድቁ ከ12ቱ ንቡራነ እድ እንደ አንዱ በተመረጡ ጊዜ በደበቡ የሃገራችን አካባቢ ክርስትናን አስፋፍተዋል::

+#ደብረ_ጽጋጋ ገዳምንም የመሠረቱ እርሳቸው ናቸው:: ዛሬ '#ኑራ_ሑሴን' እየተባለ ታሪኩ ጠልሽቶ የሚነገርለት ዋሻ የጻድቁ በዓት ነው:: አቡነ አኖሬዎስ 2ቱን ነገሥታት (#ዓምደ_ጽዮንንና #ሰይፈ_አርእድን) በመገሰጻቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል:: ጻድቁ ብዙ ፍሬ አፍርተው በዚህ ቀን ዐርፈዋል::

+"+ #ማር_ያዕቆብ_ግብጻዊ +"+

=>በግብጽ ገዳማት ውስጥ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተነስተው ካበሩ ቅዱሳን አንዱ ማር ያዕቆብ ነው:: ቅዱሱ ከተባረከ ቤተሰብ ተወልዶ: በሥርዓቱ አድጐ ገና በልጅነቱ ከመምሕሩ ጋር መንኗል:: ከገድሉ ጽናት የተነሳ ሰይጣን በግልጽ ይፈታተነው ነበር::

+በተለይ ለ7 ዓመታት ያህል ይደበድበው: መሬት ላይ ይጐትተው: በጥፊ ይመታው ነበር:: እርሱ ግን በጸሎቱ መብረቅ አውርዶ አባርሮታል:: በበርሃው ምንም የሚበላ ነገር ባለ መኖሩ የዱር እንስሳትን ወተት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጠጣ ነበር::

+ቅዱሱ ሰማዕት ለመሆን ሞክሮም ነበር:: ማር ያዕቆብ ገድሉና ተአምራቱ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል:: እስኪ ጊዜውና እድሉ ካለዎት #መጽሐፈ_ስንክሳር ላይ የተጻፈውን ገድሉን እንዲያነቡ ልጋብዝዎት:: ጻድቁ ያረፈው በዚሁ ዕለት ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹ ካሉበት ጉባኤ እንደ ምሕረቱ ታላቀነት ያድርሰን:: በረከታቸውንም ይሙላልን::

=>መስከረም 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
5.ቅድስት እሌኒ ንግሠት
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ (ሰማዕት)
8.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
9.ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
10.አባ ፊልሞስ
11.ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
12.ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
13.ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
14.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
15.ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
16.አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
17.አባ ኖብ ባሕታዊ
18.አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
19."60" ሰማዕታት (ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ)
20.ሊቁ አባ ዳንኤል (ኢትዮጵያዊ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

=>" እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም #ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: " (ማቴ. 5:13-16)
=>+"+ እንኩዋን ለቅዱስ #ጐርጐርዮስ_ዘአርማንያ: ለአባ #ቂርቆስ እና ለቅድስት #ሮማነ_ወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+"+ #ቅዱስ_ጐርጐርዮስ_ዘአርማንያ +"+

=>ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይት ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነው::

+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት #ቅድስት_አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-

1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት

2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት

3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::

+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::

+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::

+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::

+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::

+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::

+ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው አካሉ እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙ ስቃይም አሰቃዩት::

+በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት ሽማግሌ ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ15 ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::

+አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::

+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት ቆፍረው አወጡት::
+አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::

+ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን ደረሰ:: ከ318ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ:: ዕረፍቱ ታሕሳስ 15 ቀን ሲሆን ዛሬ ከተቀበረበት የወጣበት ነው::

+"+ #ቅዱስ_ቂርቆስ_ገዳማዊ +"+

=>ቅዱሱ የ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ጻድቅ ሲሆን በዓለም ከመናፍቃን: በገዳም ደግሞ ከአጋንንት ብዙ መከራን ተቀብሏል:: በወቅቱ መለካውያን (የአሁኖቹ ካቶሊኮችና ምስራቅ ኦርቶዶክሶች) የተዋሕዶ አባቶችን ያሳድዱ ነበር:: ልክ #9ኙ_ቅዱሳን በዚህ ምክንያት ወደ #ኢትዮዽያ እንደመጡት ቅዱስ ቂርቆስም ወደ ግብጽ በርሃ ተሰደደ::

+በበርሃው ውሃም ሆነ ዛፍ ባለመኖሩ በረሃብና በጥም በመሰቃየቱ ወደ ፈጣሪ ለመነ:: ጌታም አንዲት አጋዘን ልኮለት ከእርሷ ወተትን አልቦ ጠጣ:: እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም ምግቡ ይሔው የአጋዘን ወተት ነበር:: በዚህ ምክንያት ይሔው ዛሬም ድረስ "ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ ዘሲሳዩ ሐሊበ ቶራ" እየተባለ ይጠራል::

+በበርሃው ውስጥ በኖረባቸው ዘመናትም አንድም ሰው አይቶ ካለማወቁ ባለፈ አጋንንት በገሃድ እየመጡ ያሰቃዩት ነበር:: ቅዱሱ ግን በትእግስት ኑሮ በዚህች ቀን ሲያርፍ ብዙ ተአምራት በበዓቱ ውስጥ ተገልጠዋል:: ይህንን ያዩት ደግሞ ከዻዻሱ ዘንድ ተልከው የቀበሩት አበው ናቸው::

+"+ #ቅድስት_ሮማነ_ወርቅ +"+

=>ይህቺ ቅድስት እናት ደግሞ ኢትዮዽያዊት ናት:: የነገሥታቱ ልጅ ስትሆን አባቷ #አፄ_ናዖድ: እናቷ ደግሞ #እሌኒ (ወለተ ማርያም) ይባላሉ:: ወንድሟ ደግሞ #አፄ_ልብነ_ድንግል ይባላሉ::

+በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም መንፈሳዊነቷ የገዳም ያህል ነበር:: ከተባረከ ትዳሯም #ቅዱስ_ላዕከ_ማርያምን አፍርታለች:: አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ባለፈ የነዳያን እናትም ነበረች:: በክርስትናዋ ፈጣሪዋን ደስ አሰኝታ በዚህ ቀን ዐርፋለች::

=>አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን አይንሳን:: ከወዳጆቹ በረከትም እንደ ቸርነቱ ያድለን::

=>መስከረም 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማርያ
2.ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ
3.ቅድስት ሮማነ ወርቅ
4.ቅዱስ ዕጸ መስቀል

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ #ጻድቃን ጮሁ: እግዚአብሔርም ሰማቸው::
ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው::
#እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው::
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል::
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው::
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል::
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: +"+ (መዝ. 33:17)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://hottg.com/mahberememenan
HTML Embed Code:
2024/09/28 22:59:19
Back to Top