TG Telegram Group Link
Channel: ማህበረ ቅዱሳን Mhbere kidusan
Back to Bottom
#ጥምቀት

" በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተላለፈ ያለውን የበዓል አከባበር ክልከላን የሚገልጹ የሐሰት ዜናዎች ቤተክርስቲያንን አይወክሉም " - ብፁዕ አቡነ አብርሃም

በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልእክቶች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲሆኑ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው በተለያዩ ቋንቋዎች ለተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቃለ መጠይቅና ምላሽ እንዲሰጡ ለተመረጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሰጡት አባታዊ መመሪያ የቅድስት ቤተክርስቲያን መልእክት የሚተላለፈው በማእከል በመሆኑ የማእከሉን መልእክት ብቻ እንዲያስተላልፉ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ከግል አስተያየት መቆጠብ እንደሚገባም አበክረው አሳስበዋል።

ቤተክርስቲያኗ የሰላም ሰባኪ እንደመሆኗ መጠን የቤተክርስቲያን መልእክት ሲተላለፍ ሰላም ላይ ማተኮርና በዓል ለማክበር የሚወጡ ምእመናን በዓሉ በሰላም አክብረው እንዲመለሱ መልእክት ማስተላለፍ እንደሚገባ ግልጽ መመሪያ ሰጥተዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያዊ ሁሉም ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ይህ በዓል የሚከበርባቸውን ቦታዎች ለማጽዳትና ሥርዓት ለማስከበር ጥረት እያደረጉ ያሉ የሌሎች ሃይማኖት አባላትን በአባትነት ያመሰገኑት ብፁዕነታቸው ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች የሚገኙ የሌሎች ቤተ እምነቶችን ማክበር እንደሚገባ ለሁሉም ካህናትና ምእመናን አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተላለፈ ያለውን የበዓል አከባበር ክልከላን የሚገልጹ የሐሰት ዜናዎች ቤተክርስቲያንን የማይወክሉና ቤተክርስቲያናችን በዓሉን በሰላም ለማክበር ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እያደረገች ያለውን ጥረት ከግንዛቤ ያላስገባ መሆኑን ብፁዕነታቸው አሳውቀዋል።

#EOTCTV

@tikvahethiopia
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከታቸው ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል !

ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)

+++

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከታቸው ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል !

የብፁዕነታቸው ሙሉ መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“ ወኪያነኒ ይእዜ ያድኅነነ በአርኣያሁ በጥምቀት ።” ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ አሁን ያድነናል ። 1ኛ ጴጥ 3፥ 21

በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንና ምእመናት
የሰላም አለቃ ፣ የዘለዓለም አባት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሰላም ጠብቆ ለ2016 ዓ.ም በዓለ ጥምቀት በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።

የጥምቀት በዓል ነጻነታችን የታወጀበት ፣ የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበት የባርነት ቀንበር የተሰበረበት ፣ የሚናፈቀው የእግዚአብሔር ድምፅ የተሰማበት ፣ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ፣ ልጅነትን የምንቀበልበት ጸጋ የተመሠረተበት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ድምቀት ይከበራል።

ይኸውም በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር እና ታላቁ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት በጃን ሜዳ ባሕረ ጥምቀት የሚከበረው በዓል እንደተጠበቀ ሆኖ በጠቅላላ በከተማዋ ውስጥ ከ78 ያላነሱ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሥፍራዎች ይገኛሉ። በዚህም መሠረት በዓሉ በተቀናጀ መልኩ ለማስኬድ ሲባል በእያንዳንዱ ክ/ከተማ ላይ ግብረ ኃይል በማደራጀት እና ተጠሪነታቸውንም ለሃገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በማድረግ በሰፊው ዝግጅት ተደርጓል በየባሕረ ጥምቀቱም በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን ይሳተፉበታል።

ሀገረ ስብከቱም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያካሄደውን ሰፊ ዝግጅት አጠናቅቋል።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት

ሰላም የጌታ ድንቅ ስጦታ እንደሆነና ደግሞም ማንም እንዳይወስድብን አጽንተን ልንይዘው የሚያስፈልገን የሁሉም መሠረት ነው ፣ ሰላም ከሌለ በዓላትን ማክበር ይቅርና ወጥቶ መግባት ፣ ሠርቶ መብላት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት በተግባር ያየነው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ እና ለሰላም ዘብ በመቆም ቀዳሚ መሆኗ ይታወቃል።

ከላይ እንደተገለጸው በሰላም አምላክ የተመሰረተን እና የተሰጠን ጸጋ ማስጠበቅ የእያንዳንዱ አማኝ ግዴታ ነው። እንዲሁም የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ሰላምን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ድርሻ በእያንዳንዳችን ላይ እንዳለ በመገንዘብ ሐዋርያዊት ፣ ብሔራዊት እና ዓለምአቀፋዊት ለሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚመጥን መልኩ በዓሉን ማክበር ያስፈልጋል።

ስለሆነም ይህንን በዓል በምናከብርበት ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ሰላም በመንከባከብ እና በመተግበር ፍፁም ክርስቲያናዊ በሆነ ሥነ ምግባር እና አካሄድ በዓላችንን ልናከብር ይገባናል።

ይህ በእንዲህ እያለ
1. መንፈሳዊ ሰልፋችን ከነአለባበሳችን የጉዞውን ቅደም ተከተል በጠበቀ መልኩ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማዕከል ያደረገ እና ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጥ እንዲሆን

2. ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚደረገው ጉዞ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ፤ ከልዕልና ወደ ትህትና መውረዱን የሚያሳይ መንፈሳዊ እሴት ያለበት እንደሆነ የታወቀ በመሆኑ በጉዞው ላይ የሚደረግ እያንዳንዱ ክንውን አስተማሪ ሊሆን ይገባል። ሰልፉም ውበትና መስመር እንዲኖረው ይጠበቃል። በመሆኑም የአምልኮ መርሐግብር እያከናወኑ ዋዛ ፈዛዛ በመከወን የሚደረግ ጉዞ ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ጋር ፈጽሞ የሚጣረስ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዚህ ረገድ ከካህናት አባቶች የሚሰጡ መመሪያዎችን በመቀበል የበዓሉን አከባበር በደመቀ መልኩ ማከናወን እንዲቻል እንዲደረግ።

3. ሰዓትን በተመለከተ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ታቦታተ ምሥዋዕ ከመንበረ ክብር ስለሚነሱበት ሰዓት በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ዋዜማ ስብሐተ እግዚአብሔር ይቆማል። በማስቀጠል 7 ሰዓት ሲሆን በመላዋ አዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ለ10 ደቂቃ የደወል ድምፅ ይሰማና መነሻ ሰዓት ይሆናል።

- የጥር 11 የጥምቀት በዓልና የጥር 12 የቃና ዘገሊላ በዓልን በተመለከተም መነሻ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት እንዲሆንና መድረሻውም ከ 7 - 10 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲሆን እያሳሰብን በዓሉ የትህትና እና የፍቅር እንደመሆኑ መጠን ከእኛ የሚጠበቁ ክንውኖችን በመፈፀም ለበዓሉ በድምቀት መከበር አስተዋጽኦ ልናደርግ ይገባል።

4. አገልግሎታችን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ መሆን ስለሚገባው አስፈላጊውን ግብዓት ከማቅረብ በቀር ከአበው ካህናት ውጭ በየትኛውም መልኩ በሌሎች አካላት የሚደረግ ማዕጠንት ተገቢነት የሌለው እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመሆኑ እንዳይፈፀም የሚመለከታቸው አካላትም ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም በማዕጠንት አገልግሎቱ በካህናት አባቶች በሰፊው እንዲሰጥ ይሁን።

5. በረከተ ጥምቀቱን የማድረስ እና የመርጨት ክንውን የሚፈጸመው በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በካህናት ብቻ መሆኑ ይታወቃል በዚሁ መሠረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ባለማወቅ ምክንያት ሥርዓቱ እንዳይፈርስ ወጣት ልጆቻችንም ይህን አውቃችሁ ሥርዓቱን እንድትጠብቁና አገልጋዮች ካህናትም ድርሻችሁን እንድትወጡና ሕዝቡን እንድታገለግሉ እናሳስባለን ።

6. ከልክ ያለፉ እና በተደጋጋሚ የተስተዋሉ ከሥርዓት ውጭ በሆነ መልክ ለታቦታቱ ክብር በማይመጥኑ ሥፍራዎች ላይ እንዲቆሙ የሚደረገው ልምድ እንዲታረምና ሁሉም በሕግና በሥርዓት እንዲመራ።

7. ምእመናን እንደተለመደው ራሳችሁን ከሁከትና አላስፈላጊ ነገሮች በማራቅ በትዕግሥት እና በሆደ ሰፊነት በዓሉን እንድናከብር እያሳሰብን ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተናበበ መልኩ እልባት እንዲሰጣቸው ሊደረግ ይገባል።

በመጨረሻም ፦

በዓለ ጥምቀትን ስናከብር በፍፁም ወንድማዊ ፍቅር የተራቡትን በማብላት ፣ የተጠሙትን በማጠጣት ፣ የታረዙትን በማልበስ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ፤ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትህትና አብነት በማድረግ በመተሳሰብና በመደጋገፍ እንዲሆን እናሳስባለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ አሜን

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
#AddisAbaba

ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደርገዋል።

የከተራና የጥምቀት በዓልን ተከትሎ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር ለትራፊክ ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በጥምቀት በዓል በርካታ ህዝብ ታቦታትን አጅቦ ከተለያዩ ቤተ-ክርስቲያናት ወደ ጥምቀተ ባህር የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ታቦታቱ በሚጓዙባቸው መንገዶች ተሽከርካሪዎችን ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓታት አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን በተለይም በርካታ ህዝብ በሚታደምበት በጃን ሜዳ ከጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ታቦታት ወደ መንበረ ክብራቸው እስኪመለሱ መንገዶቹ ለተሸከርካሪዎች ዝግ እንደሚደረጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ፡-

- ከ6ኪሎ አደባባይ እስከ 3ተኛ ሻለቃ ፈረንሳይ ለጋሲዬን መንገድ

- ከ3ኛ ሻለቃ አደባባይ በምንሊክ ሆስፒታል እስከ ቀበና አደባባይ

- ከምንሊክ ሆስፒታል እስከ 6 ኪሎ ታክሲ ተራ

- ከቅድስተ ማርያም ቤ/ክርስቲያን እስከ 6 ኪሎ፣

- ከ6ኪሎ እስከ መነን፣

- ከሀምሌ 19 እስከ ግብፅ ኢምባሲ፣

- ከቅድስተ ማሪያም መነጸር ተራ እስከ ጃንሜዳ፣

- ከግንፍሌ ድልድይ ምንሊክ ሆስፒታል ውስጥ ለውስጥ፣

- ከግንፍሌ መገንጠያ ምንሊክ ሆስፒታል ፊት ለፊት፣

- ከምንሊክ ሆስፒታል የኋላ በር እስከ ቤላ መገንጠያ ድረስ፣ መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ።

በዓሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጃን ሜዳና በዙሪያው ተሽከርካሪ አቆሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ፖሊስ እየገለፀ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ፖሊስ አባላትን ትእዛዝ በመቀበል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

#AddisAbabaPolice
#EOTC

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፤ ከዚህ ቀደም አውግዛ የለየቻቸው ግለሰቦች አሁንም በሕገወጥ እንቅስቃሴያቸው እንደገፉበት አመልክታ ግለሰቦቹን በፍርድ እንደምትጠይቅ አስታወቀች።

ግለሰቦቹን አሁንም አውግዛ ፤ ድርጊታቸውን ተቃውማለች።

የለበሱት ልብስም የቤተክርስቲያን በመሆኑ #እንዲያወልቁት እንደምታደርግ ገልጻለች።

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን " ሕገወጥ " ባለችው መንገድ በጵጵስና ተሹመናል ካሉት እና በኃላም በእርቅ ወደቤተክርስቲያን ሳይመለሱ ከቀሩት መካከል አባ ገብረማርያም ነጋሳን ጨምሮ 4 አባቶች ትላንት በሰጡት መግለጫ " የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተክህነት መንበረ ጴጥሮስ " አቋቁመናል ብለዋል።
ይህ በ2015 ዓ/ም ተቋቁሟል ላሉት የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንበር መሰየም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቋሚና ጊዜያዊ ፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወ/ኢየሱስ ሰይፉ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በዚህ መግለጫ ፤ " ግለሰቦቹ በሌላቸው ክህነት ነው መግለጫ እየሰጡ ያሉት " ብለዋል።

እነዚህን አካላት ያደረጉት ከቀኖና ውጭ ስለሆነ ዛሬም ቤተክርስቲያን አጥብቃ ታወግዛለች ሲሉ ተናግረዋል።

" ቤተክርስቲያን በሕግ በፍርድ ቤት ትጠይቃችለች ፤ በፍትህ መንፈሳዊ ከዚህ ቀደም እንዳወገዘችው አሁንም ህጌ፣ ስርዓቴ፣ ልብሴ ፣ ዶግማዬ ይከበር ትላለች " ሲሉ አክለዋል።

" ከዚህ ቀደም በፍ/ቤት ከቤተክርስቲያን እውቅና ውጭ የትም እንዳይንቀሳቀሱ ፣ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደው ነበር ያንን ተላልፈዋል ከዚህ በኃላ በፍርድ እንጠይቃቸዋለን፤ የለበሱት ልብስም የቤተክርስቲያን ስለሆነ እናስወልቃቸዋለን፤ ህገወጥ ናቸው " ብለዋል።

" ከዚህ ባለፈ ይህ የሕገወጥ የሹመት እንቅስቃሴ ጉዳይ ከኦሮሚያ ወገን የተነሱትን ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ወገን የተነሱትንም የሚመለከት ነው " ያሉ ሲሆን ሲመቱ ትክክለኛ አይደለም ቅዱስ ሲኖዶስም አይቀበለውም ብለዋል።

የቤተክርስቲያንን ውሳኔ ማስፈፀም የሚችል አካል ሌላ በመሆኑ እንዲያስፈፅም በትዕግስት እየጠበቅን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ኃላፊው ፤ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አባቶች በቤተክርስቲያን ጥሪ ተመልሰው መጥተው ፣ ከመንግሥት ጋር በተደረግው ውይይት ፣ ወደቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ ተደርጎ በስራ ላይ ናቸው ብለዋል።

አራቱ እንዳልተመለሱና በሕገወጥ እንቅስቃሴ መቀጠላቸውን ገልጸው " የቤተክርስቲያንን ስም ማንሳት አይችሉም ፣ ስሟን ማጠልሸት አይችሉም " ሲሉ አሳስበዋል።

" እራሱ ህገወጥ ቡድን የ ' 5 ኪሎ ህገወጥ ' እያለ መጥራቱ ትልቅ ድፍረት ነው " ያሉት ኃላፊው ፤ " ይህን ድፍረት የሰጣቸውም ወቅትና ጊዜውን እየዋጁ መነሳታቸው ነው ብለዋል።

" #ሃይማኖት እና #ፖለቲካም ተቀላቅሎባቸዋል " ሲሉ አክለዋል።

" የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ምዕመናኖቿ ይህንን ህገወጥ ተግባር አይቀበሉትም ፤ ስለተወገዛችሁም ምዕመኑንም ከእናተ መስቀል አይባረክም " ሲሉ አሳውቀዋል።

ከዚህ ባለፈ ቤተክርስቲያኗ አውግዤ የለየኋቸውን አካላት መግለጫ ልክ እንደ ህጋዊ እያደረጉ ያቀርባሉ ያለቻቸውን #ሚዲያዎች ' ከቤተክርስቲያን ላይ እጃችሁን ፣ ሚዲያችሁን አንሱ ' ስትል አስጠንቅቃለች።
ፎቶ፦ " አልታወቁም " በተባሉ የታጣቂ ኃይሎች በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፤ በቦሰት ወረዳ ቤተ ክህነት የመርቆ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መቃጠሉን የተዋሕዶ ሚዲያ አገልግሎት አሳውቋል።

" ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች  " ተፈፅሟል የተባለው ይህ የመቃጠል ተግባር ትናንት ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ መፈፀሙ ተመላክቷል።

" በቦታው ላይ የተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ጊዜ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርጉ ቆይቷል " ያለው ዘገባው ትላንንት ሙሉ በሙሉ ንዋዬ ቅድሳቱ የተቃጠለ ሲሆን የቤተ መቅደሱ የውስጥና የውጭ ክፍል ጉዳት ያደረሰ ከፍተኛ ቃጠሎ መድረሱ ተገልጿል።

ጉዳዩ ላይ ሀገረ ስብከቱ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ እየሠራ ይገኛል ተብሏል።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ አገር እንዳይገቡ ተከለከሉ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአሜሪካ የነበራቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጨርሰው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰምቷል።

ብፁዕነታቸው ከሳምንታት በፊት በቋሚ ሲኖዶስ እውቅና ወደ ሀገረ ስብከታቸው በመሄድ የአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ዓመታዊ በዓል፣ የከተራና የጥምቀት በዓላትን ከመንፈስ ልጆቻቸው ጋር ያከበሩ ሲሆን ለአዳጊ ሕጻናትም ማዕረገ ዲቁና መስጠታቸው ይታወቃል።

ብፁዕነታቸው በአሁኑ ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው እንደሚገኙ ታውቋል።
ዘወረደ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ነው። ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ነው። ትርጉሙም “ከሰማያት የወረደ” ማለት ነው። ቅድመ ዓለም ከአባቱ ከአብ የተወለደ ፣ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ ነው። ስም አጠራሩ  ያለና የነበረ፣ እግዚአብሔር፣ በፈቃዱ ዓለምን ለማዳን የመምጣቱን ምሥጢር የምንረዳበት ሳምንት ነው። ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋዕል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግዕዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

ጾሙ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብሎ ያሳስበናል፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ” ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። (መዝ.፪፥፲፩-፲፪) “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሐቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ወንድማችንንም እንውደድ” እንዲል። (ጾመ ድጓ)

በዘወረደ እሑድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን የጾምን ጸጋ የያዙ ናቸው።

“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” (ያዕ.፬፥፮-፲)

“በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” (ዕብ.፲፫፥፲፭-፲፮)

በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና።” (ዕብ.፲፫፥፱) ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንዲህ ይላል፡፡ ጾመ ድጓው አባቶቻችን ያገኙትን በረከት እንደምናገኝበት ሲገልጽ “የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሠልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምእመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርሕ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት   ያስተምራል፡፡ ” አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፤ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምውታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁ ፈቃድ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡" (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬)

ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው... ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውኃ በመከልከልና ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ ግን እዘንልን፤ ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ምንጣፍ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ፡፡” (መዝ. ፴፬/፴፭፥፲፫)

ጾም ከሥነ ምግባራት ሕግ አንዱ በመሆኑ እንኳንስ ያልተፈቀደውን የተፈቀደውም ቢሆን የማይጠቅም ከሆነ ፈጽሞ በመተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምናስመሰክርበት ምሥጢር ነው፡፡

ጾም ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተያያዘም በመሆኑ መብል ጊዜያዊ ስለሆነ ማለትም በዚህ ዓለም እስካለን ብቻ የምንገለገልበት እንጂ ዘለዓለማዊ ስላይደለ ለጊዜያዊ መብልና መጠጥ ምክንያት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር እንዳንወጣ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ሲመክሩ “መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ አይጠቅመንም፤ ብንተወውም አይጎዳንም” በማለት ሲመክሩን ቅዱስ ጳውሎስም የመብልና የሆድ ጊዜያዊነት አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስተምሯል፡፡ (፩ኛቆሮ.፰፥፰)

“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም፡፡ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳን አይሠለጥንብኝም፡፡ መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል”፤ (፩ኛቆሮ.፮፥፲፪-፲፫) “ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት ስለሚሆን ምግብ ሥሩ” እንደ ተባለ (ዮሐ. ፮፥፳፯) ካለን ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ በመስጠት ቢበሉት የማያስርበውን፣ ቢጠጡት የማያስጠማውን፣ የዘለዓለም ሕይወት የምናገኝበትን ሥጋ እና ደሙን ተቀብለን መንግሥቱን እንድንወርስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

ሥርዓት ቅዳሴ
ከሠራኢ ካህን፣
ቅዳሴ፡
ዘእግዚእነ
“ዘበእንቲኣነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ፡ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ፡ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር  ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡”

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬
የዕለቱ ምንባባት:-
•  በሠራኢ ዲያቆን (ዕብ.፲፫፥፯-፲፯)
•  በንፍቅ ዲያቆን (ያዕ.፬፥፮-ፍጻሜ)
•  በንፍቅ ካህን (የሐዋ. ፳፭፥፲፫-ፍጻሜ)

ምስባክ፡ “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር” (መዝ.፪፥፲፩)

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፤ እንድናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!
ደብረ ዘይት፡- ዳግም ምጽአት

ዘመነ ሥጋዌ የጌታችን መገለጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትንበት፣ ይህም ከሰማያት ወርዶ እኛን ለማዳን ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆን ዓለምን ያዳነበት ነው፡፡ እርሱ እንደ ሰው ተወልዶ፣ እንደ ሕፃናት በጨርቅ ተጠቅልሎ፣ ጡት ጠብቶ፣ በየጥቂቱ አድጎ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በእግር ተመላልሶ፣ እንደ ሰው ተርቦና ተጠምቶ፣ ኀዘን መከራን ተቀብሎ በፍጹም ፍቅሩ አድኖናል፡፡

ፈውሰ ነፍስ በሆኑት ትምህርቶቹ ዓለምን አጣፍቶ፣ አዳኝ በሆኑት እጆቹ ልምሾዎችን፣ ድዊዎችንና አንካሶችን አድኖ፣ ጎባጣን አቅንቶ፣ የዕውራንን ዓይን አብርቷል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑንም በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቀ መለኮት እጅ ተጠምቆ አስመስክራል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ በታየበት በደብረ ታቦር ተራራም አምላክነቱን ገልጧል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፫-፲፯፣፲፯፥፩-፰)

ይህን ሁሉ ያደረገው ሰዎች አምላክነቱን አውቀን፣ ከሰማየ ሰማያት የወረደውና መከራን ተቀብሎ በመስቀል ላይ የሞተው ለእኛ ድኅነት መሆኑን እንዲሁም ድንቅ ሥራውን የፈጸመበት ይህን ጥበቡን ተረድቶና፣ የእጁን ሥራ፣ የቃሉን ተእምራት ያመነውን ሁሉም እንደሚድነን ሲያበስረን ነው፡፡ በተጓዳኝም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ዳግም ምጽአቱና ምልክቶቹ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በዝርዝር በደቀ መዛምርቱ በኩል አሳውቆናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ (ማር.፲፫፥፫-፴፯)
“መቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራብም ትገረፋላችሁ፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።

በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።

በዚያን ጊዜም ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።ሰ ማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፤ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮህ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና፤ ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”

ወንድሞች ሆይ! ጊዜ ዋጋው የላቀ በመሆኑና የጌታችንንም የፍርድ ቀን የሚያውቅ አለመኖሩን በቅዱስ ወንጌል ስለተነገረን በበጎነት፣ በቅንነትና በእምነት ጽናት ሆነን በጸሎት እንዲሁም በጾም፣ በትጋትና በክርስቲያናዊ ምግባር በመታነጽ በሃይማኖት ልንኖር ይገባናል፡፡ ዘወትርም ለሕጉ በመገዛትና ትእዛዙን በመፈጸም እስከ መጨረሻው ጸንተን “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና” ልንባል ያስፈልጋል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬‐፴፮)

ዕድል ፈንታችን መንግሥተ ሰማያት መውረስ ይሆን ዘንድም በምድራዊ ሕይወታችን መከራ ሥቃይ ተቀብለንና ለነፍሳችን መሥዋዕት መክፈል ይገባል እንጂ “እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና” ከመባል ይሠውረን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፵፩‐፵፫)
የአምላካችን ቸርነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!
HTML Embed Code:
2024/06/08 07:27:32
Back to Top