TG Telegram Group Link
Channel: ኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል
Back to Bottom
‹‹የብዕር ጥበብ›› አስተዋይ ወጣት ለኢትዮጵያ አንድነት በሚል ርዕስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ተካሄደ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል ‹‹የብዕር ጥበብ›› አስተዋይ ወጣት ለኢትዮጵያ አንድነት በሚል ርዕስ ሚያዝያ 8/2014 ዓ/ም የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ደራሲ መሐመድ አሊ (ቡርሃን አዲስ) እና የጋሞ አባቶች በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሰው ልጆች የእድገት ሂደት ወጣትነት ከፍተኛ የፈጠራ፣ የጥበብና የማኅበራዊ እሴት ሥራዎች አቅም የሚያድግበትና የሚፈፀምበት የሕይወት ምዕራፍ መሆኑን ተናግረው ወጣቱን በጥበብና በግብረ ገብ መገንባት ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ሀገራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን እየተፈጠሩ ያሉት ክስተቶች የኢትዮጵያን አንድነት እና የሕዝቡን ዘመናት የተሻገረ አብሮነትና ወንድማማችነት እንዳይጎጉ በማንበብና ጥበብን በማሳደግ የሚገኝ የአስተሳሰብ ብስለት ወጣቱ ንቁና በአላስፈላጊ ቡድኖች በቀላሉ የማይመራ እንዲሆን እንደሚረዳው ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ መሰል የሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶችም ወጣቱ እርስ በእርሱ፣ የተሻለ ልምድ ካላቸውና ከማኅበረሰቡ ልምዶችንና አስተውሎቶችን በመጋራት የሚማማርበት ነው ብለዋል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ለተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ኢንደስትሪዎችን የሚያንቃሳቅስና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር የሀገራችን ትልቅ በረከት መሆኑን ጠቅሶ ይህን እውን ለማድረግ በጽናትና በአንድነት በመቆም በጉልበትና በዕውቀት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ተናግሯል፡፡

ደራሲ ዘነበ ሥነ ጽሑፍ የሚያበረክተውን ፋይዳ ሲገልጽ በዓባይ ውኃ ላይ ግብጾች 2,200 መጻሕፍት፣ ከ10,000 በላይ ምሳሌያዊ ንግግሮችና 1,500 ጥናታዊ ጽሑፎች አሏቸው ብሏል፡፡ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በየተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ በአስተዋይነት፣ በጥበብና የማንበብ ልምድን በማዳበር ለሀገራቸውም ሆነ ለዓለም የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ደራሲ መሐመድ አሊ (ቡርሃን አዲስ) በበኩሉ ሃይማኖት፣ ባህልና ቤተሰብ ሀገራት ለረዥም ዓመታት ጠንካራ ሆነው የቆዩባቸው ዕሴቶች መሆናቸውን ተናግሮ በአሁኑ ሰዓት ግን በተለይ በተማረው ማኅበረሰብ አካባቢ እነዚህ እሴቶች የኋላቀርነት መገለጫ ተደርገው እየታዩ ነው ብሏል፡፡ እሴቶቹ የማኅበረሰብ ሞራልና ምግባርን የሚጠብቁ፣ ለሌሎች መኖርና ኃላፊነት መውሰድን የሚያስተምሩ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ራሱን ሉዓላዊ አድርጎ እንዲቆይ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

የተዛነፈ አመለካከትና ዕይታ ያለው ማኅበረሰብ የተቃና ሀገር ሊኖረው አይችልም ያለው ደራሲ መሐመድ መሰል ዝግጅቶች በወጣቶች መሰናዳታቸው ሀገርን የሚረከብና አንድነቷን የሚያስጠብቅ ትውልድ እንዳለ ተስፋ የሚሰጥ እንዲሁም ወጣቶች ስለ ሀገራቸው ያገባናል እንዲሉና ከልዩነታችን ይልቅ አንድ የሚያደርገንን ነገር በማጉላት ለመጪው ትውልድ መልካም ተሞክሮዎችን ማስተላለፍ እንድንችል የሚረዳን ነው ብሏል፡፡
የጋሞ አባቶች ተወካይ አቶ ሰዲቃ ስሜ ወጣቶች በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለምና በብሔር ከመጋጨት ይልቅ ከጥላቻ ንግግሮች በመቆጠብ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት እንዲሠሩና የጀመሩትን መልካም ተሞክሮ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል ሰብሳቢ ተማሪ ኢብራሂም ካሴ እንደገለጸው ፕሮግራሙ በዋናነት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደ መሆኑ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሀገራዊና ሌሎች ይዘቶች ያላቸው አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ አስተዋይ ወጣት እንዲሆኑ ያለመ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ተማሪዎች እንደ አካዳሚክ ትምህርታቸው ሁሉ በንባብ ዕውቀታቸውን በማዳበር አስተሳሰባቸውን ይገነባል ብሏል፡፡

በዕለቱ ግጥሞች፣ ቴአትር፣ ሥነ ጽሑፍ እና በከተማው ኪነት ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችና ባህላዊ ጭፈራዎች ቀርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

#INFOKEN_BOOKS_AND_INFORMATION_CENTER
Join us @infokenamu
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን እያልን በዓሉ የሰላም የፍቅር የደስታ እንዲሆን ኢንፎክን ከልብ ይመኛል።
#ኢድ_ሙባረክ

#ኢንፎክን_የመጻሕፍት_እና_የመረጃ_ማዕከል
Join us @infokenamu
በቅርቡ በሞት ያጣናቸው ደራሲና ጋዜጠኛ እያሱ በካፋ 'የእያሱ በካፋ ወጎች' በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ እናት እና እናትነት የሚከተለውን አስፍረዋል።
===
ሁላችን እናቶች አሉን። ሁላችንም በእናቶቻችን ማህፀን ተፀንስን፣ ከምግባቸው ምግባቸውን፣ ከትንፋሽ ትንፋሻቸውን፣ ከደማቸው ደማቸውን፣ ከስጋው ስጋቸውን፣ ከነፍሳቸው ነፍሳቸውን ስጥተውን ዘጠኝ ወር በሙሉ ረቂቅ በሆነ የተፈጥሮ መስተጋብር ውስጥ አልፈን ተወልደናል።

ብዙዎቻችን እናቶቻችንን እማማ፣ እምዬ፣ እናታለም፣ ማሚ እያልን እንጠራለን። በአለም ውስጥ ካለው ሁሉ ነገር እንደ እናት ማን ከበረ? እናትነት ነፍስን ማካፈል ነው። እናትነት የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ፍቅር መስጠት ነው። እናትነት ከራስ ህልውና ይበልጥ ለልጅ ማሰብ ነው። እናትነት ፍፁም ወረት አልባ መሆን ነው። እናት ለልጇ ያላት ፍቅር አይነጥፍም፣ አይለወጥም። ለእናት ልጇ ሁሌም ልጇ ነው።

የድሃ ልጅ እናት፣ የከበርቴ ሰው እናት፣ የወረዳ ገዥ እናት፣ የቀበሌ አስተዳዳሪ እናት፣ የአብዮት ጥበቃ እናት፣ የደንብ አስከባሪ እናት፣ የሊስትሮ እናት፣ የቤት እመቤት እናት፣ የዘበኛ እናት፣ የቤት ሠራተኛ እናት፣ የገዳይ እናት፣ የተገዳይ እናት፣ የአሳሪ እናት፣ የታሳሪ እናት፣ የገራፊ እናት፣ የተገራፊ እናት፤ የጨቋኝ እናት፣ የተጨቋኝ እናት የሞሶሎኒ እናት፣ የሂትለር እናት፣ የአንስታይን እናት፣ የጠንቋይ እናት፣ የካህን እናት፤ የሼክ እናት፤ የሁሉ እናት እናቶች ሁሉም አንድ አይነት ናቸው።

ልጆቻቸው ሲያድጉ ሲጠግቡ፤ ሲለብሱ ይፈድቃሉ እናቶች፡፡ ልጆቻቸው ሲራቡ፣ ሲጠወልጉ፣ ሲገረፉ፣ ሲማስኑ ደግሞ ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ ገራፊው ልጃቸው ወይም ጨቋኝ ልጃቸው በአድራጎቱ ሕዝብ ሁሉ ሲጠላቸው 'ለምን ልጄን ጠሉብኝ' ብለው አሁንም እናቶች ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ። እናቶች እንዲህ ናቸው፣ ዘመን የማይሽረው ሁኔታ የማይለውጠው ፍቅር የእናት ፍቅር ነው፡፡

እናት ለልጇ ያላት ፍቅር ገደብ የለውም፡፡ ልጆችም ሁልጊዜ ከምንም በላይ የሚያፈቅሩት እናታቸውን ነው። ለዚህ ነው በብዙ የታሪክ ክስተቶች እናቶች አማላጅ የሚሆኑት ልጅ ምን ጨካኝ ቢሆን እናቱ ስትመክረው፣ ስታማልደው፣ ስትጠይቀው፣ ሆዱ መራራቱ አይቀርም። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መናገር ይቻላል። እናት የንፁህ ፍቅር ምሳሌ ናት። ብዙ ሃይማኖቶች ሰውን ሁሉ እንድናፈቅር ይሰብካሉ፣ ያስተምራሉ። በዚህ ምክንያት ይመስለኛል እግዚአብሔር በእናት በኩል በሴት በኩል እኛን ለማዳን የመጣው።

የእያሱ በካፉ ወጎች ቅፅ ፩

መልካም የእናቶች ቀን!

#INFOKEN_BOOKS_AND_INFORMATION_CENTER
Join us @infokenamu
#ጥቆማ
ነገ ቅዳሜ በብሔራዊ ቴአትር 7:00 ስዓት ሰኚሆክ ትውፊታዊ ቴአትር
ይታያል።

#ኢንፎክን_የመፅሐፍት_እና_የመረጃ_ማዕከል
JOIN US @infokenamu
ከ490 በላይ የተለያየ ይዘት ያላቸው መፅሀፍት አርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ለሚገኘው የኢንፎክን የመጽሐፍትና የመረጃ ማዕከል ገቢ ሆኑ!

#INFOKEN_BOOKS_AND_INFORMATION_CENTER

Join us @infokenamu
HTML Embed Code:
2024/04/29 05:18:23
Back to Top