TG Telegram Group Link
Channel: Ethio Muslim Apologetics
Back to Bottom

ስለ አይሁዳውያን ፥ ስለ ኆኖፌም እንዋቀስ!
◆◆◆
ስለ እውነት ፍጹምነት ብዙ የፍልስፍና ሆነ የነገረ መለኮት አፍታች (በተለየ ሁኔታ የምሥራቃውያን ነገረ መለኮት ሊቃውንት) የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። እውነት ማን ነው? ምንድነው?....የሚሉ አጨቃጫቂ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው። ይህ እውነት እመርታ ፣ ለውጥ ወይም ተሐድሶ አያደርግም ፤ ምክንያቱም ፍጽምናውን ጥያቄው ውስጥ ከማስገባቱ በላይ እውነትነቱንም ጥርጣሬ ውስጥ ስለሚከትም ጭምር።

ለአንድ ማሕበረሰብ በተመሠረተበት እውነት ፣ ዶግማ እና ትውፊት "ተመሥርቶ" የማያውቀውን አዲስ የተገለጠ ወይም መታደስን ያደረገ እውነት ይዤልህ መጥቻለሁና ተቀበል ቢባል ማሕበረሰቡም አሻፈረኝ ማለቱ አግባብ ይሆናል። ሐዳሲው አካልም ቅድምናቸውንም ያልታደሰው "እውነታቸው"ንም የሚያስረግጥ ከሆነ ነገሩን "ኑፋ*ቄ" ማለታቸው ደግ የሚያሰኝ ነው። ይሄን በቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች ዘመን ፣ በኢስላምም ሆነ በአይሁዳውያን ታሪኮች የምናየው ነገር ነው።

ታዲያ መዋቀሱን እዚህ ጋር ምናመጣው? የሚል ነገር ይነሳ ይሆናል። ይሄን ለመመለስ በሐዲስ ኪዳን ስለተገለጠው ሚሥጥረ ሥላሴ ማንሳት ወሳኝ ነጥብ ይሆናል። እንደምናውቀው ፥ የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንትም እንደሚነግሩን ነገረ ሥላሴ የኦሪት ሕግን ለሚከተሉት አይሁዳውያን እንግዳ ትምህርት ነው¹። የእግዚአብሔር አንድነት እንጂ ሦስትነት በብሉይ ኪዳን የተሰወረ ትምህርተ መለኮት ነበር²።አይሁድ ነብያት ሲሰብኩ እና ሲኖሩ ያዩትን በማንነቱ እና ምንነቱ አንድነት ያለበትን ለስሙ ካላቸው ክብር አንፃር (ሐሺም 'ያ ስም')የሚሉትን አንድ አምላክ ሲገዙ ኖረዋል። ሌላ አካል በማዳበላቸው ምክንያትም መሬት ተከፍታ እንደዋጠቻቸው ፣ እንደተቀጡም ያስቧል። ይህ ሕዝብ ወይም አማኝ በድንገት ስለተገለጠው ሌላ የአስተምህሮ ሕዳሴ አለመገዛታቸው እውነት አላቸውና ሊወቀሱ ወይም ሊኮነኑ አይገባም።

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴያቸው "እስማኤላውያን" ስለሚሏቸው ³፣ ዮሐንስ አፈወርቅ (ቅዱስ) በአንድምታ ትርጓሜው "ሐነፋዊ /ኆኖፌ ስለሚላቸው ቅድመ ክርስትና የነበሩና በአብርሃም እምነት እናምናለን⁴ ፥ አንድ አምላክንም እናመልካለን የሚሉ አረባውያንም እንዲሁ መና*ፍቅ መባላቸው ላይ ጥያቄ ማንሳት ያሻል። አነኚህ ሁለት አማኞች ሁለት ትላልቅ መስፈርቶችን አሟልተዋል።፩ኛው ሁሉም ለማረጋገጥ የሚለፋለትን ቅድምና ነው። በቅድምናቸው ነቃፊዎችም ቢሆን ይስማማሉ።

፪ኛው ነገር እውነት አላቸው። አሁንም እውነት እንዳላቸው ተቺዎቻቸው አይክዱም። ፍጥረት ከጀመረበት ጀምሮ በተገለጠው የአንድ አምላክ አስተምህሮ የሚክዱ አይደሉም። በብሉይ በተገለጠው አንድነቱ ላይ ሁለትነት እና ሦስትነት አለመጨመራቸው የነብያትን ኮቴ የመከተል ነውና ሊከሰሱ አይገባም። በ Dogmatic Progression አያምኑም። ፍጹማውያን ናቸውና።

እንደው የነገረ ሥላሴን አሳብ በብሉይ ያለመገለጥ አስመልክቶ ❝ ይህን ትምሕርት ያልገለጠው ከመረዳታቸው በላይ ስለሆነና ሦስት አማልክት አድርገው ወደ መረዳት እንዳይመጡ ነው❞ ⁵የሚል አሳብ ይሰጣሉ። እውነት ለመናገር ግን ይሄ ጭንቀቱ ከውስብስብ ግርምት እና ጥያቄ ባሻገር በሐዲስ ኪዳን ሕይወትም ይሄ ችግር መፈጠሩ አልቀረም።
፨ መለኮት በአካል ሦስት (Tritheism) የሚለው አሳብ በዮሐንስ ተዐቃቢ ስለመነጨ⁶ ፣ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድም ስለተነሳው "ማርያም እናቱ " እንቅስቃሴ ማንሳት ይቻላል።
፨ ሌላው የመረዳቱን ጉዳይ አሀንም እጅግ አዳጋች እንደሆነ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን አሳብ አንስቼ ፅሑፌን ልጨርስ ፥ ጭብጡን ለእናንተ ልተው...

📜አውግስጢኖስ (Augustine (Western St) የተባሉ የቤተክርስቲያን ሊቅ ሲናገሩ ፦
"He who has tried to understand the mystery fully will lose his mind; but he who would deny the Trinity will lose his soul."~ምስጢረ ሥላሴን "ተመራምሬ እደርስበታለሁ የሚል አዕምሮውን ያጣል"፡፡ አልፈልግም ብሎ የካደው ደግሞ ነፍሱን ያጣታል፡፡ ይላሉ።

📜 ቭላድሚር ሉስኪ (Vladimir lossky) የተባለ የምስራቃዊ ፀሐፊም ፦
❝ የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት ለሰብአዊው አስተሳሰብ " ለመሸከም የሚከብድ" መስቀል ነው⁷❞ ሲል ለመረዳትም አዳጋች መሆኑን ይገልጻል።

ስለዚህ አይሁዳውያንም ሆኑ ሐነፋዊ የሆኑ ሙስሊሞች በጉዳዩ ባለማመናቸው ሊከሰሱ ፣ ሊወቀሱ አይገባም፤ እንደውም አለማመናችን ለሕጉ ያለንን ቀናኢነት ያሳያልና ሊያጸድቀን ይገባል፥ አማኙ ግን ባይኮነን እንኳን አላስተዋለም።በዚሁም ከሳሹ ሸንጎ ይቀርብ ዘንድ ግን አሳብ አቀርባለሁ...

🖋 Khalid Yohannes

Saturday /May 21 /2022
____
ማጣቀሻ መፅሐፍት
___
⓵ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ ፣ ሕማማት ፣ገፅ 131

⓶ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ ፣ የብርሃን እናት ፣ ገፅ 216 ። ዶክተር ተስፋዬ ሮበሌ ፣ የትምሕርተ ሥላሴ መሠረታዊያን ፣ ገፅ 31

⓷መምህር ግርማ ባቱ ፥ የነገረ መለኮት መግቢያ ፥ ገፅ 37

⓸በአማን ነጸረ ፣ ተኀሥሦ ፣ ገፅ 13 እና 16

⓹ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ ፣ የብርሃን እናት ፣ ገፅ 216

⓺በአማን ነጸረ ጽንዐ ተዋሕዶ ላይ ፣ አቡነ ጎርጎሪዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ ፣ አለቃ ኅሩይ ፈንታ ፍኖተ እግዚአብሔር ላይ ፥ ስለ ዮሐንስ ተዐቃቢና 'ዘጠኝ መለኮት' በሰፊው ይብራራል።

⓻Vladimir Lossky , The Orthodox Way ,Bishop Kallistos ware ,SVS ,Page 28

hottg.com/comparativereligious
ያለፈው ትንሿ ጦማር ላይ ሐሳብ ለመጨመር ያኽል ከታላቁ የፊሎሎጂ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሐይሌ የሕይወት ታሪክ መፅሐፋቸው "በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንደፍታ ላውጋችሁ" ሲሉ ከሰየሙት ላይ ነው።

በምስሉ ከሚታየው ቀዳሚ ገፅ ላይ እንዲህ ይላሉ ፦
❝የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ (WCC) ሁለቱን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ፥ ማለት Oriental Orthodox Churches የምንባለውን ተዋሕዶዎችንና Eastern Orthodox Churches የሚባሉትን ኬልቄዶናውያንን ለማዋሐድ ብዙ ጥረት ተደርጓል።....የመጀመሪያ ልዩነታችን ምን እንደሆነና መቼ እንደተጀመረ መረመርን። የውዝግቡ መሠረት ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ናቸው።...❞

~አንዳፍታ ላውጋችሁ ገፅ 212 እና 213

ያለፈው ፅሑፍ ፦
ፌስቡክ 🔗
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=554133896332249&id=100052069306231

ቴሌግራም 🔗
hottg.com/comparativereligious
ሰዎች አንድ በሚያደርጋቸው እና በተለየ የቡድን ሕላዌ ውስጥ ቢከሰቱም ራሳቸውን ችለው በቆሙ ሐሳቦችና ምልከታዎች ውስጥ «አንድነት » ማለት "አንድ አይነትነት" እንዳልሆነ ነጣጥለው ሊረዱ ይገባል። ነጽሮት ፥ ነጻነት ፣ እመርታ እና ሕብር ከቃል ማበር ይጀምራል።

አሏህ ደግሞ እንዲህ ይላል ፦

❝ የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም፡፡ ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ በልቦቻችሁም መካከል አስማማ፡፡ በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ፡፡ በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ፡፡ ከእርስዋም አዳናችሁ፡፡ እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል፡፡❞

📜Al Imran , verses: 103

ኻሊድ ዮሐንስ
🧘‍♀️ ዮጋ 🧘‍♂️ ?

https://youtu.be/IY3WNYVMVbU

ስለ ዮጋ አውርተን ነበር መሠለኝ...። እ... ዮጋ ከአካላዊ እንቅስቃሴ(Physical Exercise) ጋርም ሆነ ከአእምሮ ግንባታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ይላል ፥ በቅርብ ጊዜያት የወጡ ሳይንሳዊ ጥናቶችን እንደ አባሪ ይጠቀማል ፤ ከዛም ባለፈ የዮጋን አካላዊ ጉዳት ያስቀምጣል ፤ ከሁሉም መሠረታዊ ስለሆነውም ሐይማኖታዊ አእማዶችን እንደሚንድ ያስረዳል.... ይሄን ሁሉ በ 5 ደቂቃ ቪድዮ ይተነትናል ። እዩት ወዳጆች ፥ ይተች ፣ ይተግበር።

N.B አረብኛ ለጊዜውም ዳገት የሚሆንብን እኛ ደግሞ ሰብታይትሏን አብርተን እያነበብን እንመልከተው።
አሠላሙ ዓለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካትሁ!


ሠሞኑን ከኤቴይስቶች ዘንድ የሚነሱ የፍልስፍና ጥያቄዎችን በአላህ ፍቃድ እንመታለን!


☑️ፍልስፍና ምንድን ነው?
☑️እውን ፈጣሪ አለን?
☑️እውን እርሱ ካለ መኖሩን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
☑️ይህስ አለም ድንገተኛ (by accident) የተገኘ ነው ወይስ በመለኮታዊ ኃይል "design" የተደረገ?
☑️የሠው ልጆች ነፃ ምርጫ አላቸው ወይስ ቀድሞውኑ የተወሰነ ነገር ነው?
.
.
.

እነዚህንና ሌሎች ሐሳቦችን በፍልስፍና መነጠር በአሏህ ፍቃድ የምናይ ይሆናል እስከዚያው ወዳጅ ዘመድዎን ወደዚህ ቻናል ይጋብዙ!

https://hottg.com/ewnet_lehulum
Audio
አሏሁ አክበር! አሏሁ አክበር!

በዛሬው እለት አንድ ወንድማችን ከክርስትና ኃይማኖት ወደ ተፈጠረበት ኢስላም ተመልሷል!



አልሓምዱሊላህ ዓላ ኒእመተል ኢስላም!


https://hottg.com/ewnet_lehulum
በዚህ መፅሐፍ ላይ የቀረበ ምልከታ እና አጭር ዳሠሣ
📌በዚህ ማስፈንጠሪያ ይሂዱ ፦ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=582391450173160&id=100052069306231&sfnsn=mo
ራስን መሆን ይውደም!

Don't be yourself
_+++_

በጉዳዩ ላይ ከመፃፌ ከብዙ ቀናት በፊት የተወሰኑ መፅሐፍቶችን ለማንበብ ፥ አንዳንድ ሌክቸሮችን ለማዳመጥ ሞክሬ ነበር። አንዳንድ የሐገራችን ግላዊነትን ወይም ራስን መሆንን ለማበረታታት የተፃፉ ፅሑፎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ነገሮች በመተረክ ሐሳባቸውን ይስታሉ፤ አንዳንድ ያልኩት በጉዳዩ መረዳት ይኖራቸዋል ብዬ ያሰብኳቸውን እንጂ ብዛታቸውስ የትዬለሌ ነው። ለአብነት ከባዶ ላይ ያዘገነን "ከባዶ ላይ መዝገን" የተባለው መፅሐፍ ማንሳት ይቻላል። ስምን መልአክ አወጣው መሠል..¿

ከመች ጀምሮ እንደሆነ ጠንካራ ትውፊት ወዳላቸው ሐይማኖቶች እንደገባ አላውቅም። ሰባኪው ፣ ዳዒው ራስን ስለመሆን ረጅም ስብከት ያካሄዳል። በእለት ተእለት የጥቅስ አጠቃቀማችን ውስጥ "Just be yourself , follow your own star ,Existence wants you to be you...ወዘተርፈ በመሰሉ አባባሎች ራሳችንን ለመቅረጽ ደፋ ቀና ማለት ከጀመርን ውለን ሰነበትን። በእርግጥ "ራስን መሆን" ከላይ መልካም ነገር ይመስል ይሆናል፤ በተለይ በጥቅስነት ድባቡ። ግን የተወሰኑ ጥያቄዎችን በመመለስ ስለጉዳዩ ጥቂት መንገድ ለመጥረግ ልሞክር ፤ ለምን ራስን መሆን መውደም አለበት?

፨ ራስን መሆን ምንድነው? ፨ ጥቅሙ ወይስ ጉዳቱ? ፨ እንደ እስልምና? ፨

🔑 ራስን መሆን ምን ማለት ነው ?

ራስን መሆን ማለት ነፃነት ማለት ነው በሌላ አማርኛ። ወይም ደግሞ በፍልስፍናዊ የቃል ፍቺው ግለሰባዊነት(Individualism) ማለት ይሆናል። ራስን መሆን ሌሎችን አለመሆን ማለትም ነው። ከሕላዊነት (Existentialism¹) ፍልስፍና ጋርም የተጋመደ ነው።² አንድነት ራስን ባለመሆን ውስጥ የሚጠነክር ነው። ልዩነት ደግሞ ራስን በመሆን ውስጥ። ብዙዎች ራስን መሆንን በመነጠል ከሚገኝ ስኬት ጋር ያገናኙታል። ያ የሐይማኖትም ምክር ነው። ግላዊነት እና ራስን መሆን የተነሳበት መንፈስ ግን ሌላ ነው።

እንዲህ የሚል ድምዳሜ ከተለያዩ ፀሐፊያን እና የሕላዊነት ፍልስፍና አቀንቃኞች መፅሐፍት እንጠቁም።ራስን መሆን፥ ራስን በራስ ሕግ መምራት ማለት ነው። ማለትም ማንም የበላይ አዛዥ በተለይም የሐይማኖት መሪ ወይም መምህር ሳያስፈልግ ልናደርጋቸው የምንፈልጋቸውን ነገሮች ኹሉ በራሳችን ሕግ ተመርተን ማድረግ እንችላለን። መሠረታዊ የሥነ ምግባር መርሕ የሚመነጨው ከማንም ሳይኾን ከራስ ወይም ከግለሰብ ብቻ ነው የሚል። ምላሹንም የሚያገኘው ከራሱ ብቻ ነው። ስለዚህም ድርጊቶቹ በራሱ ምርጫ ላይ የተደገፉና የራሱን ፍላጎትና ደስታ ብቻ የሚወስኑ ናቸው³።

ጉዳዩ እድገት ነበረው። መነነሻው ከፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ ነው።የአእማዶቹ (sola) ብቻዎች በዚህ የተቃኙ ነበሩ።በራስ መተርጎም ፣ የግል አዳኝነት...የመሰሉ እሳቤዎች ከዚህ ጋር የተገናኘ ገመድ አለው። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ በኋላ ግን እየተቀየረ ሄዶ "ሌላውን ሰው የማይጎዳ እስከኾነ ድረስ የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ መብት አለህ" ወደሚል አሳብ አደገ። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የፍልስፍና ሐሳቦች መወለዳቸውን ተከትሎም በሚመስል መልኩ ራስን መሆን ወይም "ግለሰባዊነት" ሌላ ትርጉም ይዞ መጣ። "ዓለም ሁላችንም በተለያየ መንገድ እንደምናያት አድርገን እንድንገልጻት መብት ይኑረን" ወደሚል።

ከጉዳዩ ጋር ስሙ የማይጠፋው ፈረንሳያዊው ፈላስፋ ዣን ፖሎ ሳርተር (Jean paul Sartre) እንዲህ ይላል ❝የሰው ልጅ መሠረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ በጥሩ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችለን አገላለጽ ሰው ማለት አምላክን (አሏል ፥ እግዚአብሔር )ን የመሆን ዓላማ ያለው ፍጡር ማለት ነው❞⁴ብሏል። ጇኬስም ያለፉትን የአምስት መቶ አመታት የምዕራባውያንን የአኗኗር ባሕል ወደ ኋላ መለስ ብሎ በጥንቃቄ ከቃኘ በኋላ የሰው ልጅ ትልቁ ዕውን ማድረግ የሚፈልገው ዓላማ ነጻ መውጣት ፣ ከኹሉም ዓይነት ቁጥጥር መላቀቅ ወይም ከማንኛውም የበላይ ሥልጣንና ፈቃድና ፍላጎት ውጭ መኾን ነው በማለት አስቀምጧል።⁵

ቀጣዮቹ ስንኞች አሜሪካዊው ባለቅኔ Walter Whitman "The Song of Myself በሚል ከፃፈው ግጥም ውስጥ የተወሰዱ ናቸው።
ግርጌ ላይ በአማርኛ ተሞክሯል እናንተም በተመቻችሁ መንገድ ተርጉሙት

«Do I contradict my self?
Very well then....I contradict myself;
I am large .... I contain multitudes »⁶

አሜሪካዊው ባለቅኔ Walter Whitman "Leaves of the Grass (1855) በሚለው መፅሀፉ ውስጥ " The Song of Myself" በተባለው ግጥም ግላዊነትን (Individualism) በሰፊው ይሰብካል።

በአጭሩም ግለሰባዊነት ትወይም ራስን መሆን ማለት ራስን በራስ ወይም በስሜት ሕግ መምራት ማለት ነው። ብዙም የማንሳት ሐሳቤ ባይሆንም የመፅሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ የግለሰባዊነት አራማጅ ነበር የሚሉ ብዙ አሉ። የቤተመቅደሱን መጋረጃ ቀድዶ እያንዳንዱ ሰው ከፈጣሪው ጋር አንድ ለአንድ (one to one ) እንዲገናኝ አድርጓል ይላሉ። የራሳቸው ጉዳይ...!

***

🔑ራስን መሆንና ግለሰባዊነት ጥቅሙ ወይንስ ጉዳቱ ?

ይሄን ጉዳይ ለማሣጠር ልሞክር። አንድ የተሳሳተ ሐሳብ ብዙውን ጊዜ ይነሳል። ግለሰባዊነት ማለት ብቻ ከመሆን ጋር እየተነሳ ለማወዛገብ መንገድ ይሆናል።ብቻ መሆን ማለት ራስን መሆን ማለት አይደለም። ሰው ለተፈኩር ስለተገለለ ፣ ብቻውን ኑሮውን ስለገፋ ራሱን እየሆነ ነው ፣ ነፃ ነው ነው ማለት ፤ የሕብረትን ትርጉም እና ቦታ አለማወቅ ነው።

ብቻ መሆን ጥቅም አለው። አንግሥ ማርቲን « በሕይወትህ እጅግ መልካም የሚባሉ ነገሮች የሚከሰቱልህ ብቻህን ስትሆን ነው» ትላለች። እውነት ነው። ግን ብቻ መሆንን መምረጥ ማለት ብቸኛ መሆን ማለት አይደለም። እንደውም ሳርተር «ለብቻህ ስትሆን ብቸኛ ከሆንክ መጥፎ ጀማ ውስጥ ነህ» ይላል። ብቻነት እና ብቸኝነትን ነጣጥለን ማየት አለብን። ግለሰባዊነት የሚፈጥረው ብቻነትን ሳይሆን ብቸኝነትን ነው። ኡመር ረ.ዐ የተባለ የነብዩ ባልደረባ እንዲህ ብሏል ''ከመጥፎ ሰዎች ከመቀላቀል ለብቻ መሆን እረፍት ነው'''።⁷ ዑመር በሕብረት ወይም በአንድነት ወይም በፍልስፍና አጠራሩ (Collectivism ) የሚያምን ታላቅ ሐዋርያ ነው። ሕብረት የግለሰባዊነት ፅንፍ ነው።

ታላላቅ አሳቢያን የሚስማሙበት ነገር ራስን መሆን(ግለሰባዊነት) የሚሰጠው ውጤት ራስን ማጣት(ቀውስ) ነው ወደሚል መንገድ ነው። ሕልም ተፈርቶ የሚል ብሒል ለሚያቀርብልኝ ሰው የምሰጠው «አያ በሬ ሆይ! ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ» የሚል ነው። የተቻለውን ያሕል ሐብት ማፍራትም እንዲሁ እንደ ግለሰባዊነት የነፃነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም ሳቢያ ነፃነት በፉክክር ላሸነፉት ብቻ የምትሰጥ ሽልማት ነች ማለት ነው። ሰው ባለው መጠን እንጂ በማንነቱ ብቻ ግለሰብነቱን የማይቀዳጅ ባርያ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው። አገኘሁ ብሎ መቀማት እንዲህ ካልሆነ...?!
❝competition is the law of animals cooperation the law of humans. And growth not gain must be his aim. What a man really has is what is in him. What is out side of him should be matter of no importance.❞ ⁸

በዘመናዊው ትውልድ የተከስቱ ውጤቶችን ኹሉ ሊገልጻቸው የሚችል አመለካከት ሕዝቡ ከሕጋዊ ከማኅበራዊ ወይም ከሥነ መንግሥትዊ ገደቦች ፍጹም ነጻ መኾን የመፈለግ ምኞትን ነው ። በግለኝነት ራስን በራስ የመምራት መብት በማኅበረሰብ ውስጥ የፈጠረው አንዱና ዋነኛው ችግር ትዳርንና ቤተሰባዊ ሕይወትን መናድ ነው። በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት በ'እኛነት' ላይ መኾኑ ቀርቶ በእኔነት ላይ ከተመሠረተ የጋራ ሕይወትና ቤተስብ መፍጠር አይቻልም። በመደጋገፍና በመቻቻል ተጠብቆ ያልቆየ ትዲርና ቤተሰብ በልዩነት ውስጥ አንድነትን የሚጠብቁ ፣ ከጥሎ ማለፍ ይልቅ መሸከምን የሚመርጡ፤ ከራሳቸው ይልቅ ለወገኖቻቸውና ለአገራቸው የሚኖሩ ልጆችን ማሳደግ አይችልም።

በፈረሰ ቤተሰባዊ ሕይወትና በደፈረሰ ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ተወልደው የሚያድጉ ልጆች አእምሮ ውስጥ ከሰብአዊ አብሮነትና ኅብረታዊ መደጋገፍ ይልቅ ወደ ትውልድ የሚሻገር መለያየት፣ ጥላቻና ግጭት እናወርሳለን።ዚህም ሳቢያ ሳይሆን ይቀራል ከጊዜያት በኋላ የመጡ የማንነት ቀውሶች የተከሰቱት። እና ሌሎችም ኪሳራዎች...

****

🔑 እንደ እስልምና

ጉዳዩን ከትርጉሙ በመኀየስ ይጀምራል።ልዩ ኢስላማዊ ባሕሪይ ይሄ ይመስለኛል። አይሸሸውም ይጋፈጠዋል። epistemological bias የሚል መፅሐፍ ላይ የፍልስፍና ስያሜዎቹን መንፈስ በማረም የሚታወቅ አንድ መፅሐፍ መጠቆም ቻልኩኝ ማለት ነው። individualism እና collectivism. በሚባሉ እሳቤዎች ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ይሞክራል። ኢስላም በግላዊ ማንነት ያምናል ። ለምሳሌ ነፍስን ያነሳሉ። ነፍስ የሚለው የአረቢኛው ቃል “ደሚሩል-ነፍሲያ” ማለትም ድርብ ተውላጠ-ስም”Rreflexive pronoun” ሲሆን ራስነት”self-hood”፣ ሁለንተናዊ ግላዊነት”own individuality” ያሳያል ይላሉ ሊቃውንት። በዚህም ነፍስ ተጠያቂው ወይም ተሸላሚው ራሱ ሰውየው ነው። ስለዚህ በግሉ ስለሚሰራው እና ስለሚያከናውነው ነገር ሕግን መሠረት አድርጎ ማድረጉን ያስቧል።

ሌላው ትልቁ የcollectivism ሐሳብ ቤተሰብ ፣ ሸሪዓዊ ሕግ ፣ ጓደኝነት ወይም ወዳጅነት ፣ አንድነት ፣ የአቋም መመሳሰል ሊነሳ ይችላል። ይህ እንደ ሐይማኖት ወይም ትውፊታዊ ኑሮ የሚታወቅበት መለያ ነው። በእርግጥ Communism , socialism ን የመሠሉ ርዕዮቶች እንዲሁ የኮሌክቲቪዝም ማሳያሊሆኑ ይችላሉ። እንደ "ነፃ ፍቃድ" እና የእውነት አንፃራዊ እና ፍፁማዊነት እሳቤዎች ሁለቱንም አዛንቆ እንደሚቀበለው በዚህም ጉዳይ እሳቤዎን አርሞ ሁለቱንም የማራመድ ሁኔታ አለ። ይበልጥ ከማጣቀሻዎቹ ስር ሁለት ክፍል ያለው "ኢስላም እና ግለሰባዊነት"ን የሚዳስስ ሊንክ አስቀምጣለሁ።

***
🖋 Khalid Yohannes
(ኻሊድ ዮሐንስ)
***
Sunday / July 10/ 2022 A.D
(እሁድ ፥ሐምሌ 3፥ 2014 ዓ.ል)
_

¦ ማጣቀሻዎች ፥ ማብራሪያዎች እና አባሪዎች ¦
_

❶Existentialism ወይም ሕላዊነት በአጭሩ ሌሎች አድርጉ ያሉትን ማድረግን ይቃወማል። ሕይወትን በራሳችን ቁጥጥር ስር እንድናደርግ የሚጠይቅ የፍልስፍና ዘርፍ ነው።

❷Thomas R. Flynn , Existentialism , Oxford university press , P 24

❸Oden ,After Modernity ,Pp 74 ,157

❹Jean Paul Satre , Existentialism and human emotions , Translated by Philip mairet ,London :...1955 , p 2930

❺ Jacques Barzun ,From down to Decadence :500 years of western cultural life 1500 to the present , new york , harper collins ,2000

❻ሱራፌል እንዲህ አድርጎ ተርጉሞታል ፦
«ራሴን ተቃረንኩ እንዴ?
እሰየሁ! እንኳን ተቃረንኩኝ
በማንነት ግዙፍ እልፍ ስለሆንኩኝ ።»
ፀሀፊው ግላዊነትን (Individualism) ከሚያራምዱት ከነ Edward Waldo Emerson, Mark Twain ተራ የሚመደብ ሲሆን ነፃ በሆነና ከማህበረሰብ ተፅኖ በተላቀቀ ግላዊ ምልከታ ሃሳቡን መመስረቱ ስራዎቹ ዛሬ ድረስ በያንዳንዱ የስነግጥም ወዳጅ አፍ ውስጥ እንዲላወሱ ሳያስችለው አልቀረም።

❼'Umar b. al-Khaṭṭaab said: "To be alone means you avoid bad company. But to have a true friend is better than being alone." • [الآداب الشرعية ٤/١٢٤]

❽The soul of man under socialism

__+++

🔗 ስለ ኢስላም እና ግለሰባዊነት ያለው አመለካከት በተመለከተ ዘለግ ያሉ የሁለት ክፍል ማብራሪያ ፦

ክፍል 1

https://youtu.be/JfKxtEnyyVg

ክፍል 2

https://youtu.be/VI2pCsMoEfw
'ነባሩን እንጠብቅ'

እንስሳትን የሚያጠቁት አዳኞቹ የአራዊት ነገሥታት የሆኑትን አናብስት ዒላማ ውስጥ እስኪያስገቡ ለሚዳቋ መከታ መሆናቸው አይቀርም። ቅድሚያ ትልቁን ገድሎ ያለ ሁካታ ሚዳቋን ሊያድኑ ግን አካሄዱ የተገባ ነው።

'ነባሩ' እያሉ በኩሸት ሙቀት ጎራ ስለከተቱህ ከሐሴትህ ይልቅ "ለምን?" ህ ቢቀድም ላንተው መልካም ፍኖት ነው። ነገ ይሄ ሙቀት ወላፈን ሆኖ እንዳያጠፋህ እኔ ወንድምህ ግን አስብልሃለሁ። ምክንያቱም በሊሏህ ገመድ አንድ ስለሆንን..! እኔ እና አንተ ነባርነትን በነሲሐ እንጂ በሴራ አንፈታውምና!

ታሪክህን እኔ አውቅልሃለሁ ፣ አብሬህ ልቁም የሚልህ የበፊት ባላንጣ ካጋጠመህ መጠርጠሩ መልካምም አይደል?! እንዲሁ ከመሬት የተነሳ ጥብቅና ምንጭ ከወዴት እንደሆነ ብታነፈንፍ የፈለቀው ከጥፋት ኩሬ ነው። ከተቻለህ ገድልህን አንተው ራስህ ፃፈው! አፍሪካውያን ጥሩ አባባል አላቸው። ይላሉ፦

❝አናብስቱ የራሳቸው ታሪክ ጸሐፊዎች ከሌሏቸው ፤ የአደኑ ትርክት ሁሌም አዳኞችን የሚያሞግሥ ይኾናል።~Until lions have their historians, tales of the hunt shall always Glorify the hunters.❞

ቁርኣን ማን አዳኝ እንደሆነ ከመንገሩ ሌላ መንሰፍሰፋቸው በራሱ ምስክር ነው።

Khalid Yohannes
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
አድዋ ላይ የማሸነፋችን ምሥጢር....በመምህር ፋንታሁን ዋቄ

እንደው ግን ይሄን «አጥንተውን..» ያለውን ጥናት የሚያቀብለኝ ይኖር ይሆን? ድሉን እንዲህ ከአመክንዮ ውጭ እንዴት ለአንድ ተቋም ብቻ ሊሰጡ ይችላሉ? የተዋጉት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን(ሙስሊሙ ፥ ዋቄ ፈታ ፥ ቅብዓቱ ፣ ጸጋው ፥ ኢ-አማኙ...) አልነበሩም ወይ? ይህ ድል በአፄ ሐይለ ሥላሴ ጊዜ ስለምን አልተደገመም?

እግረ መንገድ ለሐይማኖት መጋደል ከሞት ኋላ ላለው ሕይወት መልካምን ነገር የመጠበቅ እሳቤ ብሎ እነማን ናቸው? ቢባል ሁሉም Eschatologyን የሚቀበል ሁሉ በሚባል ደረጃ ያለ ተቋም መንገዱ መሆኑን በአንድም በሌላ ይታያል።

በአማን ነጸረ ነጽሮቱን ሲያስቀምጥ «የቅዱስ ቴዎፍሎስን ከልዩ ልዩ አምልኮዎችና አስተምሕሮዎች ምከታ ጋር የተገናኘ ''ጉልበትና መጽሐፍ" የተቀናጀበት ታሪክ ያነበበ ሰው የኤኛው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ይመስለኛል»¹ ይላል። የቴዎፍሎስን ቅድስና እንደ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጨከን ማለቱ አላጠፋውም ይልቁንም ከገድሎቹ እንደ አንዱ ተነሳ እንጂ። ክሱ ግን አሁንም ብዙ ስለተወራበት እና ትርጉሙ ስለተዛባበት ኢስላማዊው "ጂሐድ" ላይ የማይወርድ ቢሆንም።
____+++___

₁ ደብተራ እና የሕግ ጠበቃ በአማን ነጸረ ፤ ተሐሥሦ ገፅ 131

💊 አደራ ጥናቱን ማቀበሉን ግን አትርሱ
ሕይወት መነኮሳት ወመነኮሳይያት

ሰሞኑን ከብላቴን ጌታ ኅሩይ መፅሐፍ ጋር አሳለፍኩ። ወዳጄ ልቤና ሌሎች በሚለው ስራቸው ስለማውቃቸው ከፅሑፉ ሌሎችን ገፋ የማድረግ ነገር ይኖራል በሚል ሐሳብ ነበር የጀመርኩት።እንደገመትኩት አይደለም.....በእርሳቸ ሐሳብ የራሴን ነገር ለመስጠት ለጊዜው ልታቀብና እንደወረደ ላስቀምጠው ፦

«ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዶ በሥርዐት የሚኖር ከእግዚአብሔር የታዘዘ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈ ነውና ሚስት ያላገቡ መነኮሳት ሚስት ታገቡ ሰዎች ይልቅ የበለጠ ክብር ያገኛሉ ብለን በልባችን አናስብም በቃላችንም አንናገርም፡፡
ይልና ገፅ 181 ላይ

...በእውነተኛ አእምሮ ብንፈርደው ግን ከመነኮሳት ይልቅ ሚስት ያገቡ ሰዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ እነሆ አሁን በጦርነት ጊዜ መመስገን የሚገባው በሰልፉ ጸንቶ የተዋጋ ወታደር ነው እንጅ ሸሽቶ የሄደ ወታደር አይመሰገንም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ መንኩሶ በገዳም መኖር ከዚህ ዓለም መከራና ፈተና ሸሽቶ እንደመሄድ ነው፡፡ ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዶ በሕገ እግዚአብሔር ጸንቶ የእዚህን ዓለም መከራና ፈተና ታግሦ የሚኖር ሰው ግን በሠይፍ ጸንቶ እንደመዋጋት ነው፡፡»

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ፤ጎሀ ጽባሕ ፥ገጽ 182

🤷‍♂️
የወንጌላውያን ወጥመዶች -3
(የግለሰቡን የእምነት መሠረት መናድ)
..
❝..አላማየ ሙስሊሞችን ክርስቲያን ማድረግ አይደለም.❞
..
ጆርዳናዊው ዳዒ ፕሮፌሰር ኢያድ ቁነይቢ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 የገጠማቸውን ክስተት አስመልክቶ ሰፋ ያለ አርቲክል ጽፈው ነበር። በወቅቱ አንድ ወዳጃቸው አንድ በአሜሪካ የሚዘጋጅ መጽሔት ይሰጣቸዋል። የመጽሄቱን ይዘት ሲመለከቱት ግን በጣም ይገረማሉ። መጽሄቱ አንድ የተለያዩ ሚሽነሪዎችን የህይወት ተሞክሮ በተመለከተ ያዘጋጀው ዘገባ ነበር።
..
በመጽሄቱ ላይ ከተጠየቁ ሚሽነሪዎች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፦
..
ሙሉ ጹሁፉን በዚህ ሊንክ ማንበብ ይቀጥሉ፦

http://hidayacomparative.org/የወንጌላውያን-ወጥመዶች-3/
◉ ይህ▸ https://youtu.be/5YYX3k9Orho የኡስታዝ ኢልያህ ማሕሙድ ይፋዊ የዩቲዩብ ቻናል ነው። የተለያዩ ኢስላማዊ እና ንፅፅራዊ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ብቸኛው ገጹ ስለሆነ Subscribe/Like/Share በማድረግ ዳዕዋውን ለወገኖቻችን በፍጥነት ያድርሱ።

® Ustaz Eliyah Mahmoud Telegram Channel.
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም «በትምህርትና በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ አገዛዝ፤ በነፃነትና በእኩልነት ላይ ያልተመሰረተ የሕዝብ ስብስብ፤ በእድገትና መሻሻል ላይ ያልቆመ ኑሮ በየፈርጁና በየደረጃው መክሸፍ እንደሚጠብቀው ታሪካችን ያሳያል።» ብለው አዳፍኔ ላይ ከትበውልን ነበር። ይህ ሂደት አሁናዊ ውሳኔያችንንም የሚጠይቅ ነውና

1 ሰው ለ1 ተማሪ እንቅስቃሴ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል መሰረታዊ መማሪያ ቁሳቁስ ላጡ ተማሪዎች ተደራሽ በማድረግ የወደፊቷን ያልከሸፈች ኢትዮጵያ በቻለው መጠን ለመገንባት የበኩሉን እያበረከተ ያለ እንቅስቃሴ ነው።

የመማሪያ ቁሳቁሶቹን ገዝቶ ማቅረብ ለሚፈልግ
4 ኪሎ ኢኽላስ ህንፃ 2ኛ ፎቅ ሪሳላ ሴንተር ወይም ቄራ መስጅድ ኢቅራእ ላይብረሪ ማስረከብ ይችላል።

አሊያም በሚከተሉት የባንክ አካውንቶች አማራጩን መጠቀም ይቻላል።
ንግድ ባንክ 1000463057037
ሂጅራ ባንክ 1000030840001
ሪሳላ የወጣት ኢምፓወርመንት ሴንተር

ለበለጠ መረጃ ፡ +251921124823 / +251919426168
አሥ-ሠላሙ ዐለይኩም ያ ጀመዓህ
ወንድም ዩኑስ የሚባል የዩንቨርስቲ ተማሪ ሲሆን መጽሐፍ ጽፎ ግን ማሳተሚያው ውድ ሆኖበታል። መጽሐፉን ለማየት ሞክሬ ነበር፥ የማናውቃቸው አዳዲስ ነገሮች ይዘዋል። ማሻሏህ ዐለይሂ
ከቻልን ተጋግዘን እናሳትምለት! ይህንን ሊንክ አስፈንጥራችሁ ጎራ በሉ፦ https://hottg.com/+C75BYRr7yCI4ZDJk
HTML Embed Code:
2024/04/25 18:21:57
Back to Top